የጋራ ጥቅም ላይ ያነጣጠሩ መስሎ የግል ጥቅምን በጐን ማሳደድ ሊነቃበት የሚገባ ጨዋታ ነው፡፡ Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ)
የሚመጣውን ሁሉ ተዘጋጅቶ መጠበቅ ነው፡፡ጉዳዩን የሚያቅ፤ የበሰለ፣ ባለገድልና ባለታሪክ ሰዋችንን አንናቅ፡፡ምክር መቀበልና ማክበር ይገባል፡፡ አደጋ ላይ ሊጥል የሚችልን ነገር አስቀድሞ ማሰብ፣ ማውጠንጠንና መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ብዙ አደጋዎችን፣ ብዙ ችግሮችን፣ ብዙ ውጣ – ውረዶችን ያየችው አገራችን መከራዋን ትወጣው እንጂ አብዛኛዎቹ የተከሰቱት ምክር በማይሰሙ መሪዎች ነው፡፡ የተቋጠረውን እየፈታን፣ የተዘጋ የሚመስለውን እየከፈትን፣ አደባባዩን ምሽግ ያደረገውን እየደረመስን፣ ወመቴን ከአለሌ፣ ጨውን ከአሞሌ፣ ቱሪስቱን ከፒስኮር፣ ህንዱን ከባኒያን፣ ጭልፊቱን ከአሞራው፣ የፖለቲካ ነጋዴውን ከሀቀኛ መንገደኛው፤ ለይተንና አበጥረን መጓዝ ለሀገርና ለህዝብ የሚመች አጓጓዝ ነው፡፡
የታለፉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ አጋጣሚዎች ደግመን ማጣት ከእንግዲህ ብርቱ ዋጋ ያስከፍለናልና ጥንቅቅ ብለን ማሰብ ይገባናል፡፡ የድህነት ነገር ሆኖብን ሁሌ ሥራችንን በዘመቻ እንድንሠራ እንገደዳለን፡፡ አንድን ሥራ በነጥብ መብራት አተኩረን መሥራት ትልቅ ጉልበት በማከማቸት ግብ እንድንመታ ይረዳናል፡፡ ሆኖም ዘላቂና የኔነት ስሜት ያለው ሥራ እንድንሠራ በሙያዊ ብቃት፣ በሥራ ክፍፍልና በሙሉ ስሜት እንድንራመድ ካልሆነ ለብዙ ችግር እንጋለጣለን፡፡ ጦርነትም ቢሆን እንኳ በኃይል በኃይሉ፣ በክህሎት በክህሎቱ ሲሰደር ነው ለግብ ይበቃል የሚባለው፡፡ የጋራ ጥቅም ላይ ያነጣጠሩ መስሎ የግል ጥቅምን በጐን ማሳደድ ሊነቃበት የሚገባ ጨዋታ ነው፡፡
መቼም የሀገራችን ነገር አንዱ ሲወርድ አንዱ ሲወጣ ያለበት ነው፡፡ ከሥራውም ይልቅ ሰውዬውን ለሚያይ ዘላቂነት ያለውና ያለፈውን ስህተት ለማረም የቻለ ጉዞ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ የሠራተኛው፤ የፓርቲ አባሉ፣ የበታች ኃላፊው ሁሉ፣ ሁልጊዜ “እናቴን ያገባ ሁሉም አባቴ ነው” የሚልበት ዘመን ያከተመ ይመስላል፡፡ “ተሰናባች አይርገምህ፤ ተተኪው አይጥላህ” የሚለውን በጥንቃቄ ካዩት ትርጉም ያለው ቁምነገር ያስጨብጠናል። ተሰናባች በግፍ፣ በምቀኝነት ወይም በአድልዎ ተባሮ ከሆነ እርግማኑ ይደርስብኛል ብሎ ማሰብ የአባት ነው፡፡ ተተኪው በተንጋደደ ዐይን የሚያይ ከሆነና “ለዚያኛው ያልተኛ እኔን አይምረኝም” ብሎ ያሰበ ከሆነም ሲሰጉ መኖር ነው፡፡ ከዚህም ይሰውረን፡፡
የሚመጣውን ሁሉ ተዘጋጅቶ መጠበቅ ያለ ነው፡፡ ጣር መጣ ጦር መጣ እያሉ በጣም ያስፈራሩት ጀግና፤ በዝግታ እየተዘጋጀ፤ “ይምጣ ከመጣ ሞቼ ልጠብቀው እንዴ ልዘጋጅ እንጂ!!” አለ የሚባለውንም አንዘንጋ፡፡ ጉዳዩን የሚያቅ፤ የበሰለ፣ ባለገድልና ባለታሪክ ሰዋችንን አንናቅ፡፡ ከየቦታው ሰብስበን ሥራ ላይ እንዲቀመጥ እናድርግ፡፡ ልታይ ልታይ የሚለውንና የአደባባይ ጌጥ የሆነውን ትተን፤ ከልቡ ለሀገር የሚያስበውን እናስተውል፡፡
“ሰዎች የአስቸኳይ ጥቅምና ፍላጐታቸው ተገዢ ከመሆናቸው የተነሳ አታላይና አጭበርባሪ ሰው ከመጣ ለመታለልና ለመጭበርበር ዝግጁ ናቸው” ማኪያቬሊ