ዋ!….ያቺ ዓድዋ = እንኳን ለአንድ መቶ አስራ ዘጠነኛው የአድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሳችሁ!!

እንኳን ለአንድ መቶ አስራ ዘጠነኛው የአድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሳችሁ!!
ዋ!….ያቺ ዓድዋ
ዋ!….
ዓድዋ ሩቅዋ
የዓለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ
ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ
ዓድዋ….
ባንቺ ብቻ ሕልውና
በትዝታሽ ብፅዕና
በመሰዋዕት ክንድሽ ዜና
አበው ታደሙ እንደገና….
ዋ !
ዓድዋ የዘር ዐፅመ ርስትዋ
የደም ትቢያ መቀነትዋ
በሞት ከባርነት ሥርየት
በደም ለነፃነት ስለት
ዓድዋ
የኩሩ ትውልድ ቅርስርዋ
የኢትዩጵያነት ምሰክርዋ
ዓድዋ
የኩሩ ደም ባንቺ ጽዋ
ታድማ በመዘንበልዋ
ዐፅምሽ በትንሣኤ ነፋስ
ደምሽ በነፃነት ሕዋስ
ሲቀሰቀስ ትንሣኤዋ
ተግ ሲል ሲንር ትቢያዋ
ብር ትር ሲል ጥሪዋ
ድው -እልም ሲል ጋሻዋ
ሲያስተጋባ ከበሮዋ
ሲያስገመግም ዳኘው መድፍዋ
ያባ መቻል ያባ ዳኘው
ያባ ነፍሶ ያባ ቃኘው
ያባ በለው በለው ሲለው
በለው-በለው-በለው-በለው !
ዋ !…ዓድዋ…
ያንቺን ጽዋ ያንቺን አይጣል
ማስቻል ያለው አባ መቻል
በዳኘው ልብ በአባ መላው
በገበየሁ በአባ ጎራው
በአባ ነፍሶ በአባ ቃኘው
በለው ብሎ ፥ በለው -በለው !
ዋ !….ዓድዋ….
ዓድዋ የትላንትናዋ
ይኸው ባንቺ ሕልውና
በትዝታሽ ብፅዕና
በመስዋዕት ክንድሽ ዝና
በነፃነት ቅርስሽ ዜና
አበው ተነሡ እንደገና ።
….ዋ!….ያቺ ዓድዋ
ዓድዋ ሩቅዋ
የእለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ
ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ
ዓድዋ…..
የካቲት – (፲ ፱ ፻ ፷ ፬- ዓድዋ )
እሳት-ወይ-አበባ
ከጸጋዬ-ገብረ-መድኅን