ወያኔ ኢትዮጵያን እያቃጠለ ከኔ ጋር ብሩህ ተስፋ እያለ ያብዳል::


Minilik Salsawi – የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ እንከኖቻችን ጥቅል ውጤት ማስጨነቁና ማሳሰቡ የሀገርና የህዝብ ስሜት ላለው ሁሉ አይቀሬ ነው፡፡በሃገር ቤት ማናቸውንም የጥፋት ድርጊት የሚፈጽሙ ወገኖች ለሀገር እንደቆሙ፤ የህዝብ ልጆች እንደሆኑ አድርገው መጮሃቸውና ሀቀኛ መምሰላቸው፤ ሌላው እንዳይናገር በር ይዘጋል፡፡ በበፊት ስርአቶች የእጅእላፊ አሊያም ጉቦ እንዲሁም ብዝበዛ ይባል የነበረው የምዝበራና አገርን የማራቆት ተግባር፣ ዛሬ ሙስና የተባለውን ፤ በልማት እና ትራንስፍሮሜሽን ሲስተም ሃገር የሚያደማ እና የሚያቃጥል ሆኗል፡፡ አገር ትልቅ ለውጥ ላይ ናት፤ ከፍተኛ የትራንስፎርሜሽን ሂደት ላይ ነን እየተባለ፤ በተጭበረበረ የፖለቲካ እና በቅጥር ቁልል የኢኮኖሚ እድገት ፕሮፓጋንዳ እየማሉ በጐን የዝርፊያ የኮንትሮባንድ እና በአንድ ጀንበር ፎቅ ሠርቼ ልደር ዘመናዊ ምዝበራ ይታያል፡፡ ከፖለቲካ እና ፖለቲከኞች የተጠጋጉ ሁሉ በአንዴ ዘጋ/ዘጋች ዛሬ በኢትዮጵያ የተለመደ ቋንቋ ነው፡፡ እንደአንዳንድ የአፍሪካ ሃገሮች ዐይንያወጣ የቀን ተቀን ዘረፋ የሚመጣው ከላይ እስከታች እየተወሳሰበ ያለው ሙስና ፍፁም ወደፈጠጠ ደረጃ ሲደርስ ነው፡፡

አንድም ሙስናው በየአቅጣጫው መሆኑ፤ አንድም ደግሞ ቢሮክራሲያዊ መጠቅለያ መኖሩ እጅግ ሊፈታ በማይችልበት ደረጃ ውስብስብ አድርጎታል፡፡በዚህ ላይ የወያኔ ግለሰቦች አሻጥር ተደምሮበት፣ ከቁጥጥር ውጪ ወደሆነ ደረጃ ተሸጋግሯል፡፡ የኢትዮጵያውያን በሃስት ክስ በየእስር ቤቱ መታጎር፣ የመሬት አሰቃቂ አወሳሰድ፣ ከፍተኛ የኮሚሽንና የድለላ ሥራ፣ አደገኛ ወገናዊ አሠራር…በአስደንጋጭ የድህነት መቀመቅ ውስጥ ያለችውን አገር ከምትሸከመው በላይ ትከሻ አጉብጥ ሸክም ጭኖባታል፡፡ወያኔ ኢትዮጵያን እያቃጠለ ከኔ ጋር ብሩህ ተስፋ እያለ ያብዳል::በትንሹም በትልቁም ነገር ከማበድ ይሰውረን፡፡ የመሞቻ መሣሪያ ከማማረጥ ያድነን፡፡ያኔ በደርጉ ዘመን በሥራው አጋጣሚ በእጁ የገባውን የሕዝብ ገንዘብ ለግል ጥቅሙ በማዋሉ የሚለው የዜና ሐረግ ነበር ሬዲዮንና ቴሌቪዥን ያጣበበው፡፡ ዛሬ በወያኔው ስርአት ዳር እስከዳር በየሰው አፍ የሚወራ ነገር ሆኗል፡፡ ዝርፊያው ዓይነት በዓይነት ሆኗል፡፡ የአንድ ሰሞን ሕዝብ ማዘናጊያ እና ሆያሆዬ ዘገባ ተወርቶም በቀላሉ ይረሳል፡፡ለህዝብ የማይሳሳው የማይጨነቀው ወያኔ ለህብረተሰብ ቀጥተኛ መጥፊያ የሚሆኑ እንደመድሃኒት ያሉ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ባመቸው መንገድ ሁሉ ተበርዘው ከተባዙ፣ ምን ያህል አሰቃቂ የሆነ ዕልቂት እንደሚያስከትሉ መገመት አያዳግትም፡፡ የሚያስገኙት ገንዘብ የትየለሌ፣ የሚፈጁት ህዝብ የትየለሌ!!ይህንን ስርአት በማስወገድ ራሳችንን ነጻ አውጥተን ሃገርን እና ወገንን ማዳን የዜግነት ሃላፊነት መሆኑን ልናውቅ ይገባል::

ሃገራችን እና ወገናችን በጨለማ ውስጥ እየዳከረ ባለበት በዚህ የወያኔ አገዛዝ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በመረባረብ የዜግነት ግዴታውን አውቆ ለህዝቦች መብት እና ነጻነት መታገል አለበን። ሃገሪቷ በዚህ አደጋ ውስጥ ባለችበት ሰአት ላይ ህዝብ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ለኑሮ ውድነት ለሞት ለስደት እየተዳረገ ኢትዮጵያዊነት እየተዋረደ ከመሆኑም ባሻገር ኢትዮጵያን እያቃጠለ ከኔ ጋር ብሩህ ተስፋ እያለ የሚያጭበረብረውን ወያኔን ከስሩ መንግሎ በመጣል በመቃብሩ ላይ የህዝብን ነጻነት ማረጋገጥ አሌ የማይባልበት ወሳኝ ወቅት ላይ መሆናችንን በማወቅ ከትግሎ ጎን አቅማችን በሚችለው ሁሉ በመቆም ነጻነታችንን ማረጋገጥ ግድ ይለናል::