ስለ ህወሓት ልንሸማቀቅ ይገባል

ስለ ህወሓት ልንሸማቀቅ ይገባልጌታቸው ሺፈራውለአገር ግንባታ በርካቶች በወደቁበት፣ የውጭ አገር ወረራን ለመዋጋት እልፍ አልዓፍ ጀግኖች በተሰውበት፣ አድዋን የአዲስ አበባ ከንቲባ ተወካይ ለ10 ደቂቃ ንግግር አድርጎ ‹‹ተከበረ›› በሚባልበት፤ የዛሬዎቹ ገንጣዮች የዶለቱበት የመጀመሪያው ቀን በማይወዷት አገር ሀብት ለወራት ያህል እየተከበረ ነው፡፡ ገንጣዮቹ አሁንም ስማቸውን እንኳ ባልቀየሩበት ያደረጉት ጦርነት ‹‹የአገር ግንባታ፣ ለኢትዮጵያውያን ነጻነት….›› እየተባለ እየተሞካሸላቸው ነው፡፡ የህወሓትና የኢትዮጵያ እንቆቅልሽ ቀጥሏል! ህወሓት ከዓለም የተለየ ‹‹ገዥ›› ነው፡፡ እኛም በዓለም ልዩና አሳዛኝ ተገዥዎች ሆነናል፡፡
ደቡብ አሜሪካ፣ አፍሪካ፣ ኤሲያ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ታጣቂ ቡድኖች የተፈለፈሉባቸው አገራት ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ታጣቂ ቡድኖች ደግሞ አንድም ከጨቋኝ የአገራቸው መንግስት አሊያም ከቅኝ ገዥዎች ነጻ ለመውጣት የሚንቀሳቀሱ ነበሩ፡፡ በመሆኑም ከአላማቸውም ባሻገር ነጻ አውጭነታቸውን በስማቸውም ይገለጻሉ፡፡ ሆኖም አብዛኛዎቹ ‹‹ነጻነት፣ አርነት›› የሚል ስም ቢይዙም ነጻ የሚወጡት ከአውሮፓውያኑ ስለነበር ከአገራቸው ክብር ጋር የሚቃረን አልነበረም ወይም አይደለም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካ ውስጥ ገብተዋል የሚባሉ አገራት ይገኙ የነበሩት ፓርቲዎች ሳይቀር ይህን ተገንጣይ ስሞች ሳይሆን አገራዊ አንዳንዶቹ ደግሞ አህጉራዊ ስም ይዘው ነው የተዋጉት፡፡ የጥቂት ነጮች አገዛዝ ደቡብ አፍሪካዊያንን ነጭ፣ ህንዳዊ፣ ጥቁር ብሎ በተለያዩ ቡድኖች ከፋፍሎ በሚገዛበት ወቅት የእነ ማንዴላ የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንገረንስ ነበር ነጻ አውጭው፡፡ ሆኖም በጥቁሮች አሊያም በተወሰኑ ጎሳዎች ስም ‹‹ነጻ አውጭ ነን!›› አላሉም፡፡ ከዚህ ይልቅ ከደቡብ አፍሪካም አልፈው አህጉራዊ ስም ይዘው ነው የታገሉት፡፡
በተመሳሳይ በሞዛምቢክ፣ አንጎላ፣ ዚምባብዌ የነበሩ ታጣቂ ቡድኖችና ፓርቲዎች አገራዊ ከዚያም አልፎ አህጉራዊ ስሞችን ይዘው ነው የተነሱት፡፡ ነጻ አውጭዎች ቢሆኑም ከአገራቸው በላይ አፍሪካንም ነጻ ለማውጣት መነሳታቸውን የሚያሳይ ስም ነበራቸው/አላቸው፡፡ በሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ዩጋንዳ፣ ሱዳንና ኮንጎ የነበሩትና ያሉትም በተመሳሳይ አገራዊና አህጉራዊ የነጻ አውጭነት ሚናን የያዙ ስሞችን መጠሪያቸው አድርገዋል፡፡ ለአብነት ያህል በአሁኑ ወቅት ችግር ቢገጥመውም ደቡብ ሱዳንን ነጻ አገር ያደረገው የእነ ሳልቫኪር ፓርቲ ‹‹የሱዳን ህዝቦች ነጻ አውጭ ንቅናቄ›› ነው የሚባለው፡፡ ራሱን በደቡብ ሱዳን ብቻ እንኳ አላጠረም፡፡ አሊያም ከዚህ ወርዶ ራሱን ደቡብ ሱዳን ውስጥ በሚገኙ ጎሳዎች ስም አልጠራም፡፡
በዓለም ገዥ ፓርቲ ሆኖ ነጻ አውጭ ስም ያነገቡት ፓርቲዎች በእጅ የሚቆጠሩት ብቻ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል ቲሞር ውስጥ ለበርካታ ጊዜ ገዥ ፓርቲ የሆነው የምስራቅ ቲሞር ነጻነት አብዮታዊ ግንባር፣ የኢልሳቫዶሩ ፋራቡንዶ ማርቲ ብሄራዊ የነጻነት ግንባር፣ የዶሚኒካ ነጻነት ፓርቲ ይገኙበታል፡፡ የእነዚህ ፓርቲዎች ‹‹ነጻ አውጭነት›› አገራዊ እንጅ ወደ ጎጥ የወረደ አይደለም፡፡ የቲሞሩ ገዥ ፓርቲ መጀመሪያ እንደ ፓርቹጋል ካሉ ቅኝ ገዥዎች ጋር የተዋጋ ፓርቲ ነው፡፡ ይህ ፓርቲ በተለያዩ ጊዜያት በምርጫ ተሸንፎ ለተቃዋሚዎች ስልጣኑን በሰላማዊ መንገድ አስረክቧል፡፡ ለአብነት ያህል እ.አ.አ በ2007ና 2012 ስልጣኑን በሰላማዊ መንገድ አጥቷል፡፡ የኢልሳቫዶሩ ገዥ ፓርቲም ብቻውን ሳይሆን ከሌላኛው የአገሪቱ ፓርቲ ጋር ነው አብሮ እየሰራ የሚገኘው፡፡ ይህ ፓርቲ በአብዛኛው እያሸነፈ የሚገኘው ከ40ና ከ30 በታች ድምጽ ነው፡፡ የዶምኒካን ፓርቲ ማዕከላዊነቱና ሌሎች አንዳንድ ፖሊሲዎቹ ከኢህአዴግ ጋር የሚያመሳስሉት ቢሆኑም የጎሳ ነጻ አውጭ አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት ከህወሓት ውጭ በዓለም የጎሳ (ብሄር) ነጻ አውጭ ነኝ የሚል ‹‹ገዥ ፓርቲ›› አይገኝም፡፡
ሻዕቢያ ‹‹የኤርትራ ነጻ አውጭ›› ስሙን ጥሎ አገራዊ ስም ሲይዝ የቀድሞ አቋሙን በመቀየር ድል ሲቀናው ትግራይ ከኤርትራ በተሻለ ከኢትዮጵያ ጋር ታሪካዊ ትስስር አላት ብሎ ወደ ምኒሊክ ቤተ መንግስት ያቀናው የአሁኑ ገዥ ፓርቲ ነጻ አውጭነቱን እንደተሸከመ ነው፡፡ ይህ ነጻን ህዝብ ነጻ የማውጣት እንቆቅልሽ አሁንም እወክለዋለሁ የሚሉትን ህዝብ መያዧና ከሌላው ጋር የረባ ግንኙነትና አንድነት እንዳይኖረው ማጎሪያ መሆኑን የብዙዎቹ እምነት ነው፡፡
ከኢትዮጵያም በላይ የደህንነት ችግር ያለባቸው አገራት የሚገኙ ፓርቲዎች እንኳ ከህወሓት የተሻለ አገራዊ ስም ያላቸው መሆኔ የኢትዮጵያውን ‹‹ገዥ ፓርቲ›› ለመንግስት መንበር የማይበቃ መሆኑን እንረዳለን፡፡ እየተበጣበጠች በምትገኘው ደቡብ ሱዳን አንድም በጎሳ መሰረት ነጻ አውጭ ሆኖ የተቀመጠ ፓርቲ የለም፡፡ የሱዳን ህዝቦች ነጻ አውጭ ንቅናቄ፣ የተባበሩት ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ የደቡብ ሱዳን ዴሞክራሲያዊ መድረክ፣ የደቡብ ሱዳን ሌብራል ፓርቲ፣…… የመሳሰሉት ስሞች ነው ያላቸው ናቸው፡፡ የእርስ በእርስ ጦርነት በሚንጣት ሱዳንም ቢሆን ፓርቲዎች አገራዊ ስም የያዙ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ሌብራል ዴሞክራሲ ፓርቲ፣ ብሄራዊ ኮንግረንስ፣ የሱዳዝ ባዝ ፓርቲ፣ ዴሞክራሲያዊ የአንድነት ፓርቲ….. የመሳሰሉትን የሚይዝ ነው፡፡ ታጣቂ ቡድኖችም ጭምር ይህን ያህል ነጻ አውጭ ስም አልያዙም፡፡ ሰላም አስከባሪ የሚጠብቃት ላይቤሪያ ፓርቲዎች የአንድነት ፓርቲ፣ ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ጥምረት ለሰላምና ዴሞክራሲ…. የመሳሰሉትን ስሞች የሚጠቀሙ ናቸው፡፡
ህወሓት ይህንን የገንጣይ ስም በስያሜነት ሲጠቀም ጥቁር አሜሪካውያን ስለ ነጻነታቸው የሚታገሉበት ወቅት ነበር፡፡ ፓርቲው ይህን ስም ይዞ ሲመሰረት እነ ማርቱን ሉተር ኪንግና ሌሎችም የጥቁሮቹ መሪዎች ጥቁር አሜሪካውያን ከነጮች ጋር አንድ ካፍቴሪያ፣ ትምህርት ቤት፣ አውቶቡስና አገር ውስጥ እኩል እንዲገለገሉ ጥያቄ ያቀርቡበት የነበር ወቅት ነው፡፡ በአንድ ወቅት በአንድ አውቶቡስ ከነጮች ጋር መሄድ የማይፈቀድላቸው አሜሪካውያን ጥቁሮች አሁን እኩልነታቸው ተረጋግጧል፡፡ በትምህርት ቤት፣ አውቶቡስና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች አድሎና ጭቆና ይደርስባቸው የነበሩት ጥቁሮ አሁን ከአብራካቸው የወጣው ኦባማን ከአለም ትልቁ የስልጣን ማማ ላይ አስቀምጠዋል፡፡ በእርግጥ በዚህ ወቅት ነጭ አሜሪካውያን እንደሰው የማይቆጥሯቸው የነበሩት ጥቁር አሜሪካውያን ነጻ አውጭ ስምም ሆነ አላማ አልነበራቸውም፡፡ አሁንም ቢሆን አድሎና መገለል ሙሉ በሙሉ ከአሜሪካ ባይጠፋም ጥቁር አሜሪካውያን ግን ነጻ አውጭ አላስፈለጋቸውም፡፡ ምክንያቱም አገራዊ አላማ ይዞ እንደመታገል ያለ ሞራላዊ ጉዳይ ስለሌለ ነው፡፡
ለአሜሪካውያን ጥቁሮች ነጸነት ሲታገሉ በሞቱበት ወቅት ስሙን ‹‹ህወሓት›› ብሎ የሰየመው በጥቁሮች ዘንድ ነጻ ተደርጋ የምትወሰደው የኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ ግን እነ ኦባማ ስልጣን ላይ በወጡበት በአሁኑ ወቅትም በገንጣይ ስሙ ቀጥሏል፡፡ ህወሓት ራሱ ስልጣን በያዘበት ህዝብን ከማን ነው ነጻ የሚያወጣው? ከ90 በላይ የመከላከያ ሰራዊቱ አባል፣ የደህንነት መስሪያ ቤትና ሌሎቹም ተቋማት በእሱው ታጋዮች በተሞሉበት ህዝብን ከማን ነጻ ያወጣል? ኢትዮጵያ ማለት የአቶ መለስ ዜናዊ ታሪክና ዝና በእያንዳንዱ ተቋም አልፎ ቤት ለቤት እንዲዘመርባት የምትደርግ አገር ነች፡፡ ስፖርት፣ ጎዳና፣ ትምህርት ቤት፣ ……..ሁሉም በሟቹ የህወሓት አመራር ስም ተሰይመዋል፡፡ የህወሓት ባለስልጣናት፣ ካድሬዎች፣ ደህንነቶች፣ የመከላከያ አባላት በመላው የአገሪቱ ክፍል አዲስ ፊውዳል ሆነዋል፡፡ ታዲያ ማንን ከማን ነው ነጸ የሚያወጣው? ህወሓት ገዥ ፓርቲ እንደመሆኑ በውጭ ጉዳይ፣ በመከላከያ፣ በደህንነቱ፣ በአጠቃላይ በአገሪቱ በሚገኙት ስልጣኖች የትግራይን ህዝብ ሳይሆን ኢትዮጵያውያንን እያገለገልኩ ነው እያለን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ ብሎም መንግስትን በትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ስም መንግስት እየመራሁ ነው እያለን ነው፡፡ መሪው በሞቱ ወቅት ደግሞ መለስ ሶማሊም፣ አፋርም፣ አማራም፣ ወላይታም፣…….ብቻ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች አባል፣ ወኪልም ናቸው ብለውናል፡፡
እንዲህም ብለው ግን አሁንም ገንጣዮች ናቸው፣ አሁንም ‹‹አገር ገንቢዎች!›› ናቸው፣ አሁንም ‹‹ለሀገር አሳቢዎች›› ናቸው፣ አሁንም ዘራፊዎች ናቸው፡፡ አሁንም ገዥዎች ናቸው፡፡ ይህ እንቆቅልሽ በኢትዮጵያ ካልሆነ በስተቀር በየትኛውም አገር የለም፡፡ በፖለቲካም ነውር ይመስለኛል፡፡
‹‹ቅኝ ገዥ ነች፡፡›› ባለት ኢትዮጵያ ውስጥ ገዥ የሆነው ህወሓት ቢገድል፣ ቢዘርፍ፣ ቢያወዛግበን የሚገርም አይደለም፡፡ እሱን ሳያስበው እጁ ላይ የገባው ስልጣን ሞኝ (ጅል) አድርጎታል፡፡ የዓለም መሳቂያ! በእርግጥ እሱ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ለዓለምም የማይመጥን ገንጣይ ‹‹ገዥ›› ተሸክመን የዘለቅነው አሳዛኝ ተገዥዎች ልንሸማቀቅ፣ አንገት ልንደፋና ልናፍር ይገባል፡፡ ደግሞም የሚገድለው፣ የሚያስረው፣ የሚዘርፈው እኛውኑ ቢሆንም ‹‹የኢትዮጵያ መንግስት›› እየተባለ ነው፡፡ ጅል (ሞኝ ) ባያፍር በዚህ ኢትዮጵያም ዓለምም የማይመጥነውን ስርዓት በመሸከማችን ልና