ሲሉ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል -አርቲስቶችን ተናገሩ።
ጥር ፲፪(አስራ ሁለት ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ደብረጽዮን- ከአርቲስቶች ጋር ባደረጉት ዝግ ስበሰባ የተናገሩት ነገር ተቀርጾ በይፋ በማህበራዊ ሚዲያዎች የተለቀቀ ሲሆን፤ በንግግራቸው አርቲስቶችን ሲመክሩና፣ ሲያባብሉ እና ሲገስጹ ተሰምተዋል።
<<በፌስ ቡክ የሚነገረንን ነገር እንሰማለን፤አርቲስቶች ሆዳሞች እንደምትባሉ እናውቃለን!>> ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን፤ <<መለስን ሳይቀር የሚሳደቡ አሉ፤ መለስን ብቻ ሳይሆን ሁላችንንም ሲሰድቡን አይተናል>> ብለዋል።
<<እናንተም የፈለጋችሁትን ነገር ንገሩን፤ ስድብም ከፈለጋችሁ ህሊናችሁ ከፈቀደ ስደቡን>> በማለት ለአርቲስቶቹ የተናገሩት ዶክተር ደብረጽዮን፤ <<ዝም ብላችሁ ጥሩ ጥሩ ነገር ብቻ ብትናገሩን አንሰማችሁም፤እንደውም አጭበርባሪ ነው የምንላችሁ>>ብለዋቸዋል።
አክለውም፦<< እናንተ ባትነግሩንም ችግር እንዳለብን እኛ እናውቃለን፤ዝም ብሎ የሚቆልለንን ፊት ለፊቱ ባንናገረውም፤ ዞር ስንል ግን አጭበርባሪ ነው ማለታችን አይቀርም>> ሲሉ ገስጸዋቸዋል።
ህወሀት የተመሰረተበትን 40ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ወደ ደደቢት አቅንተው የነበሩ አርቲስቶች በሙሉ ህወሀትን ሲያወድሱና ሲያሞካሹ፤ አርቲስት አስቴር በዳኔ ብቻ ጠንካራና ሞጋች ጥያቄ ማንሳቷ ይታወቃል።
አርቲስቷ ከ ኢሳት ጋር ባደረገችው ቃለ-ምልልስ ፦ያን ጥያቄ ካነሳች በሁዋላ ባለስልጣናቱ ሲያበረታቱዋት፤ ሌሎቹ የሙያ አጋሮቿ ግን እርሷ ጋር ላለመታየት እንደሸሿት ገልጻለች።
በአርቲስቶች በደረሰባት መገለል የተከፋችው አስቴር በዳኔ፤ የሙያ ጓደኞቿ ያልሆኑን ከመሆን የአስመሳይነት ህይወት እንዲወጡ መክራለች።