የደቦ አባዜ በመስከረም አበራ

የሃገራችን ማህበረ-ፖለቲካዊ አውድ ከድሮ እስከ ዘንድሮ፣ ከግለሰባዊነት ይልቅ ማህበራዊነት ያጠላበት ነው፡፡ ብዙዎቻችን ስንወድ ስንጠላ፣ ስንደግፍ ስንቃወም የጀማውን አዝማሚያ አይተን ነው፡፡ በግላችን የምናቀርበው ክርክር በጀማው ዘንድ ተቀባይነት ካጣ፣ በግል እምነታችን ከመፅናት ይልቅ ተሸማቀን የምናፈገፍግበት ጊዜ ይበዛል፡፡ ትክክለኛነታችንን የምንለካው፣ በተከተለን መንጋ ብዛት እንጂ በአመክንዮአችን ጥንካሬ አይደለም፡፡

ይህ አንደህዝብ የምንጋራው በጎ ያልሆነ እሴታችን ነው፡፡ መንግስት ደግሞ የህዝብ ነፀብራቅ ነውና በተለያየ ወቅት ሃገራችንን የመሩ መንግስታትም ከዚህ የተዋጁ አይደሉም፡፡ ገዥዎቻችን፣ ብዙሃኑ ህዝብ ሰጥ ለጥ ብሎ እየተገዛላቸው፣ ጥቂት የተለየ ሃሳብ ያነሱ ዜጎችን ከምድር በታች ካላደረጉ እንቅልፍግ የማይወስዳቸው ለዚህ ነው፡፡ ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ሃገሬው “ስዩመ እግዚአብሄር” እያለ ይሰግድላቸው የነበሩት አፄ ኃ/ስላሴ፣ ገርማሜ ነዋይን የመሰለ ባለ አእምሮ የገመድ ራት ያደረጉት በዚህ አግባብ ነው፡፡ የነ ልጅ እያሱ፣ በላይ ዘለቀ፣ ጥላሁን ግዛው አሳዛኝ ፍፃሜ የዚሁ የንጉሱ በደቦ የመግዛት ፍላጎት ክፉ ውጤት ነው፡፡ ዱላ ተቀባዩ ወታደራዊው መንግስትም ኢትዮጵያ ትቅደም፣ የኢትዮጵያ ሶሻሊዝም፣ የእድገት በህብረት የእውቀት እና የስራ ዘመቻ፣ ሁሉም ነገር ወደጦር ግምባር፣ የቀይ ኮኮብ ዘመቻ ወዘተ እያለ በየጊዜው የሚያመጣቸው ግን ደግሞ እርሱ እራሱ በቅጡ ያልተረዳቸውን ፍልስፍናዎች በደቦ ያልደገፈውን ሁሉ ደም ከማፍሰስ ወደኋላ አይልም ነበር፡፡ የዚህ አካሄዱ ማጀቢያም “ከእኛ ጋር ያልሆነ ከጠላታችን ጋር ነው” የሚል የደመ-ነፍስ መርህ ነበር፡፡

ተተኪው ኢህአዴግም መውደድ መጥላቱን፣ አድናቆት ውግዘቱን ከዘጠና ሚሊዮኑም የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በደቦ ማድረግ ይፈልጋል፡፡ ከዚህ ያፈነገጠን ሁሉ የዲያቢሎስ አምሳያ የሃገር ጠላት አድርጎ ያብጠለጥላል፡፡ ይህን የደቦ አባዜውን፣ ከሃገሬው ህዝብ አልፎ እስከ ባህርማዶ የምዕራባዊያን ግለሰቦች እና ተቋማት ድረስ ያዘልቀዋል፡፡ ከሚያስተዳድረው ህዝብ አልፎ ባዕዳንም በደቦ የወደደውን እንዲወዱ የጠላውን እንዲያወግዙ ይፈልጋል፡፡

የፍቅር ደቦ -1

በ1977 ዓ.ም በሃገራችን ተከስቶ በነበረው ረሃብ ሰበብ፣ የምዕራባዊኑን ዶላር ጣዕም የቀመሰው ህወሃት የምዕራባዊያኑ ንዋይ የህይወት መስመሩን የሚያረዝም መሆኑን የተረዳው ገና ጫካ እያለ ነበር፡፡ ሸማቂው ቡድን፣ “ቆምኩለት” በሚለው ድሃው የትግራይ ህዝብ ስም የመጣውን የእርዳታ ገንዘብ አያሌ ድርሻ፤ በአቶ መለስ ፊታውራሪነት ለማሌሊት መመስረቻ እና ማጠናከሪያ እንዲውል እንደተደረገ፣ አልፎ ተርፎም ሱዳን ላይ ለድርጅቱ ትላልቅ የእርሻ መሬት ተገዝቶ ሰሊጥ እያመረቱ ይቸበችቡ እንደነበር በወቅቱ የድርጅቱ በጅሮንድ የነበሩት አቶ ገ/መድህን አርአያ፤ በአንድ ወቅት ከቪኦኤ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ተናግረዋል፡፡ይህ ተግባር አሳፋሪ ቢሆንም፣ በዚሁ መንገድ የመጣው ረብጣ ገንዘብ ሕወሓትን በወቅቱ ከነበሩ ሃብታም ሸማቂዎች መካከል እንዲመደብ አድርጎታል፡፡ ነገሩ ድርጅቱን ከምዕራባዊያኑ ጋር ከአንጀት ባይሆንም ከአንገት በላይ በሆነ ፍቅር እንዲወድቅ አድርጎታል፡፡ በመሆኑም የሸማቂነቱ ዘመን አብቅቶ መንግስት ሲሆን የምዕራባዊያኑን ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ፈለግ እንደሚከተል ይገልፅ ጀመር፡፡ በፖለቲካው ረገድ፣ በምዕራባዊያኑ ዲሞክራሲ ስም በመማል በመገዘት፣ በኢኮኖሚው በኩል ደግሞ “የምከተለው ነጭ ካፒታሊዝምን ነው” ሲል ያመሽ ያነጋ ነበር፡፡ ዓለም-አቀፍ የሰብዐዊ መብት አንቀፆችን የህገ-መንግስቱ አካል በማድረግ፣ ለምዕራባዊያኑ ሊብራሊዝም ፅንሰ-ሃሳብ እና አጠቃላይ ርዕዮተ-ዓለም ያለውን ታማኝነት ለማስመስከር ሞክሯል፡፡ የጣለውን የደርግ ስርዓት ያብጠለጥል የነበረውም የዜጎችን ሰብዐዊ መብት በመርገጥ እና ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማስፈን ባለመቻሉ ያጠፋቸውን ጥፋቶች በማነሳሳት ነበር፡፡ በዚህ ወቅት የምዕራባዊያኑ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ፈለግ፣ በኢሕአዴግ ዘንድ ብቸኛ የድኅነት መንገድ ተደርጎ ይወሰድ ነበርና ከዚህ ሃሳብ መለየት ለማንም አልተፈቀደም ነበር፡፡ የተለየ ሃሳብ አለኝ የሚል ቢገኝ እንኳ መጠሪያው የደርግ ርዥራዥ፣ “የዲሞክራሲ ጠላት” የሚል ይሆናል፡፡

የፍቅር ደቦ -2

ሕወሓት ከውልደቱ ጀምሮ በሻዕብያ ፍቅር ክፉኛ የተመታ ነበር፡፡ ይህ ጣራ የነካ ፍቅር በሚገርም ሁኔታ እናት ሃገርን ቅኝ ገዥ አድርጎ እስከማሰብ እና ቀኝ ተገዥዎችን ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት እናት ሃገርን እስከ መውጋት አድርሶታል፡፡ ህወሃት፤ ከሻዕብያ ጋር የወደቀበት ሃያል ፍቅር፣ ወዳጅ ጠላቱን ለመለየት ሳይቀር ዋና መለኪያው፣ ያ ወገን የኤርትራን ጉዳይ የሚረዳበትን መንገድ እስከ ማድረግ ደርሶ ነበር፡፡ ለምሳሌ ህወሃትን ከኢህአፓ ጋር ያቃቃረው፣ ኢህአፓ የኤርትራን ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው ለማለት ባለመድፈሩ ነበር፡፡ በተጨማሪም የህወሃት ፍቅር፣ ከራሳቸው ከኤርትራዊያኑ ታጋዮች የበለጠ ለኤርትራ ያገባኛል እንደማለት ስለሚሞክረው ለወሬ የማይመች የሚሆንበት ጊዜም ነበር፡፡ አቶ መለስ፣ ጫካ በነበሩበት ወቅት የትክክለኛ ኤርትራዊነትን መስፈርቶች እስከማውጣት ደርሰው እንደነበር የአስራት አብረሃም “ከሃገር በስተጀርባ” መፅሃፍ ያስረዳል፡፡ አቶ መለስ፣ በዚሁ መስፈርታቸው በኢትዮጵያዊነት ስር ሆኖ የኤርትራ ጥያቄ ይመለስ የሚሉ፣ ኢትዮጵያ የኤርትራ እናት ሃገር ነችና መገንጠሏን አንቀበልም የሚሉ፣ ከደርግ ጋር ተደራድረው ኤርትራን ለመገንጠል የሚደረገውን ትግል ለማስቆም የሚከጅሉ ኤርትራዊያን፤ ከኤርትራዊነት የጎደሉ እንደሆኑ አምርረው ይናገሩና ይፅፉ ነበር፡፡ በአቶ መለስ መስፈርቶች ከተሰፈሩ፣ አንድ ሁለት ጊዜ ከደርግ ጋር ለመደራደር መለስ ቀለስ ብለው የነበሩት ኢሳይያስ አፈወርቂ ራሳቸው ኤርትራዊነት የሚጎድላቸው ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነታቸውን የሚወዱት እውቁ ኤርትራዊ ምሁር ፕ/ር ተስፋፅዮን መዳኔ፣ ከኤርትራዊነት ፀዳል የጎደሉ እንደሆኑ አቶ መለስ “የኤርትራ ህዝብ ትግል የቁልቁሊት አይደፋም” የሚል መፅሃፍ እስከመፃፍ በደረሰ ሙግት ሲያስረዱ ነበር፡፡
ይህ ከጠዋቱ ህወሃትን የተጣባው የሻዕብያ ፍቅር፣ ሸማቂ ቡድኑ አድጎ ኢህአዴግ በሚል ሰፊ ድርጅታዊ ማዕቀፍ ውስጥ ገብቶም፣ የመንግስትነት ሰገነት ላይ ወጥቶም የሚብስ እንጅ የሚበርድ አልሆነም፡፡ ሸማቂ ቡድኑ፣ ወደ አዲስ አበባ በሚያደርገው ግስጋሴ ሁሉ ቆምኩለት ከሚለው ኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም እና ፍላጎት ይልቅ የሻዕብያ አመራሮችን ፍላጎት ያስቀድም ነበር፡፡ አዲስ አበባ ገብቶ የታላቋን ሃገር የኢትዮጵያን እጣ-ፋንታ አንድ ደረጃ ሳያደርስ፣ የኤርትራን መገንጠል በአስተማማኝ ሁኔታ ለማሳካት የተባበሩት መንግስታትን ሹማምንት እረፍት በነሳ ውትወታ ተጠምዶ ነበር፡፡ የመገንጠሉ ሂደት ሚጢጢዋን ኤርትራን ያለ አግባብ ባለ ሁለት ወደብ ሲያደርግ ኢህአዴግ ታገልኩላት የሚላትን ታላቋን ሃገራችንን ወደብ አልባ ማድረጉ፣ በኤርትራ ፍቅር አይነ-ልቦናው ለታወረው ህወሃት ነገሬ የሚባል ጉዳይ አልነበረም፡፡

ይህ ምንጩን ለማወቅ የሚያስቸግር ህወሃት የወደቀበት ሃያል ፍቅር፣ ወደ ሁሉም ኢትዮጵዊ በደቦ ሰርጎ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የኤርትራን ጉዳይ ቀዳሚ እንዲያደርግ የመፈለጉ ዝንባሌ ራሱ ከወደቀበት ፍቅር ብርታት የበለጠ የሚገርም ነበር፡፡በወቅቱ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ህወሃት የፈለገውን ያህል በኤርትራ ፍቅር ሊወድቅ ቀርቶ፣ የኤርትራን ሃገርነት ለመቀበልም እንኳ ዝግጁ አልነበረም፡፡ በተቃራኒው ህዝቡ ኤርትራ የተገነጠለችበትን ሪፈረንደም አግባብነት እና የኢትዮጵያ ሁለት ወደብ አስረክቦ ወደብ አልባ መሆን እያስቆጨው ነበር፡፡ ይህ የአብዛኛው ዜጋ እምነት ታዲያ ለህወሃት መሪዎች የደርግ ቅሪት፣ የነፍጠኛው ስርዓት ርዝራዥ፣ የነፃነት ጥያቄ የማይገባው ትምክህተኛ፣ የተስፋፊነት አባዜ የተጠናወተው፣ የጎረቤት ሃገር ሉአላዊነት የማይዋጥለት ጦረኛ …. የሚል መጠሪያ ይሰጠው ነበር፡፡ “ስለ ኤርትራ አንዳች ክፉ የሚናገር ቀድሞ የሚጣላው ከእኛ ጋር ነው” የሚለው የህወሃት አባባል፤ ሽርክናው ወደ መሸካከር ተቀይሮ፣ በሁለቱ ሃገራት መሃከል ከፍተኛ ደም መፋሰስ ከሆነ በኋላም የቀጠለ ነው፡፡

‘የኤርትራ መገንጠል የነፃነት ምልክት ነው ከተባለ ይሁንና የኤርትራ አካል ያልሆነው የአሰብ ወደብ እንኳን ለሃገራችን ይትረፍ’ ማለትም በህወሃት መንደር የሚያስቀስፍ ሃጢያት ነበር፡፡ የወደብ እጦቱ ድህነቱን ያባባሰበት የኢትዮጵያ ህዝብም የአሰብን ወደብ ያለአግባብ ለኤርትራ መሰጠቱን በደቦ እንዲቀበል አልፎ ተርፎም ህገ-መንግስቱ ያመጣው የነፃነት ትሩፋት ነው ብሎ እንዲያምን ይጠበቅበታል፡፡ ህወሃት፣ ኤርትራን በተመለከተ የያዘውን አስገራሚ አቋም እንዲይዝ ባደረገው ፍቅር የተለከፈበት በሚናገረውም ሆነ በማይናገረው የራሱ ምክንያት ሆኖ ሳለ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ያለ ምክንያት ተገቢ ያልሆነውን የሚቀበልበት እና ከህወሃት ጋር የፍቅር ደቦ ገብቶ ‘ከኤርትራ ያስቀድመኝ’ የሚልበት ምንም ምክንያት የለውም፡፡ ሆኖም ደቦ ወዳዱ ህወሃት፣ እርሱ በወደቀበት የኤርትራ ፍቅር የኢትዮጵያም ህዝብ እንዲወድቅ ይጠብቃልና የወደቡ አንሶ ቡናው፣ ጤፉ፣ ገብሱ፣ ስንዴው …. ወደ ኤርትራ ሲጋዝ ከልቡ ደስ እንዲለው ሲፈርድበት ኖሯል፡፡

የፍቅር ደቦ-3

የመገንጠል መብትን የህገ-መንግስቱ አካል ያደረገው ኢህአዴግ፣ ህገ-መንግስቱ በፀደቀ ማግስት የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ በደቦ በመገንጠል ፍቅር እንዲወድቅ፣ የመለያየት መዝሙር እንዲዘምር፣ ከሃገራዊነት ይልቅ ወንዘኝነቱን እንዲያጠብቅ፣ መገንጠልን የነፃነት ቁንጮ አድርጎ እንዲያስብ መፈለጉ አልቀረም፡፡ በሌላ በኩል በዘውዳዊው ስርዓትም ሆነ በወታደራዊው መንግስት ዘመን ለተቆጠሩ ረዥም አመታት በጋብቻ፣ በጉርብትና እና መሰል ማህበራዊ መስተጋብሮች አንድነቱ ሲያጠብቅ ለኖረው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ደግሞ ይህ በቀላሉ የሚዋጥ አልነበረም፡፡ ሆኖም ኢህአዴግ ከጠዋቱ የሃገር አንድነትን በነፍጠኛ አማሮች ብቻ የሚቀነቀን ክፉ አባዜ አድርጎ ይቆጥር ነበርና እርሱ በወደቀበት የመነጣጠል ፍቅር ያለመመታት፣ የትምክህተኝነት ምልክት ተደርጎ ይወገዛል፡፡ የሚገርመው ይህን የሚለው ኢህአዴግ መገንጠልን አልመው የሚንቀሳቀሱ የብሄር ፓርቲዎችንም በጠባብነት ይከሳል፡፡ በህወሃት/ኢህአዴግ አተያይ፣ የመገንጠል ጥያቄ የነፃነት ትግል የሚሆነውም የሚሳካውም ሻዕብያ ሲያነሳው ብቻ ነው፡፡ በተረፈ ስለመገንጠል ቀርቶ ስለአንድ ብሄር መብት ጥያቄ ማንሣት የጥበት ምልክት ነው፡፡ ይህን ግራ የተጋባ የገዥው ፓርቲ አቋም፣ በደቦ መከተል ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ግዴታ ነው፤ ካልሆነ የተለመደው ውግዘት ይከተለዋል፡፡

የፍቅር ደቦ – 4

ከ1997 ዓ.ም ወዲህ ‘ዲሞክራሲያዊነቱን ትቼ ልማታዊ ሆኛለሁ’ ያለው ኢህአዴግ፣ ይህን ሲል ወደስልጣን ከመጣ ጀምሮ እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ ሲዘምርለት የኖረውን የምዕራባዊያን ዲሞክራሲ በልማታዊ መንግስት ርዕዮት ተክቶ ነው፡፡ “ሩቅ አሳቢ” ሲል የጠራውን የልማታዊ መንግስት እሳቤ፣ ‘የእስያን ሃገሮች ኢኮኖሚ እንደ ነብር እንዲፈተለክ ያደረገ ብቸኛ መድህን ነው’ ሲል አወዳድሶ፤ ቀድሞ ሲያሞካሸው የነበረውን የምዕራባዊያኑን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ የርዕዮት አለም ዘይቤ ደግሞ፡- “በአሸናፊነት መንፈስ አለቅጥ የሰከረ፣ ለአፍሪካ ፈፅሞ የማይበጅ” ሲል አጣጥሎ ነው፡፡ የኒዮ ሊብራል ቀሳውስት ዶግማ የሚለውን የምዕራባዊያን የኢኮኖሚ ዘይቤ በተለይ “የዘበኛ መንግስት የመመስረት ህልም ያለው” ሲል ያራክሰዋል፡፡

በዚህ ቅፅበትም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሲዘምርለት የኖረውን የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ህልም ወዲያው ረስቶ፣ ከኢህአዴግ ጋር በቻይና ፖለቲካዊ ርዕዮት ፍቅር እንዲወድቅ፣ ስለሱው እንዲዘምር፣ በአንድ አውራ ፓርቲ ስር መሆንን ፀዳል ድንቅነት እንደያወድስ፣ ስለሰብዐዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶቹ አያያዝ ሁኔታ ትንፍሽ ሳይል ስለቁሳዊ እድገት እና እንዲሁ በደቦ የልማታዊ መንግስትን መስመር ተከትሎ ስለሱው ትሩፋቶች ብቻ እንዲነጋገር ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ የደቦ አስተሳሰብ የሚያፈነግጥ የልማት አደናቃፊ፣ የህዝብ ጠላት የሚሉ ተቀፅላዎች ይንጠለጠሉበትና ጉዞው ወደቃሊቲ ይሆናል፡፡

ከላይ ለማሳያነት የቀረቡት የኢህአዴግ የደቦ ጉዞ ፍላጎቶች፣ በምክንያታዊነት ለሚያምን እና የራሱ አተያይ ላለው ዜጋ ክፉ ፈተና የሚደቅን ነው፡፡ ሌላው የዚህ ከመንግስት በኩል የሚፈለገው የደቦ ጉዞ ችግር፣ ራሱ ለደቦ የሚጋብዝበትን ሃሳብ ይዞ የመሰንበት ዝንባሌው አናሳ መሆን ነው፡፡ ከላይ በመጠኑ ለማሳየት እንደተሞከረው ገዥው ፓርቲ ትናንት በፍቅር ወድቆለት ሌት ተቀን ሲያነሳሳው ህዝቡንም ለደቦ አድናቆት ሲጋብዝበት የነበረውን ርዕዮተ አለምም ሆነ መመሪያ፣ ከመቅፅበት ቀይሮት ጠላት ሲያደርገው ይስተዋላል፡፡ የምዕራባዊያኑ የዲሞክራሲ እና የሰብአዊ መብቶች አያያዝ እሳቤ፣ ከኤርትራ ጋር የነበረው ወዳጅነት፣ የመገንጠል ጥያቄን የሚያስተናግድበት ሁኔታ ወ.ዘ.ተ ለዚህ አባባል በማሣያነት ሊቀርቡ የሚችሉ አብነቶች ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳ የደቦ ጉዞውን ለመቀበል ለተዘጋጀ ሰውም ቢሆን የኢህአዴግ አካሄድ አስቸጋሪ እና ግራ አጋቢ መሆኑ አይቀርም፡፡ በዚህ ሁኔታ ለመያዝ ለመጨበጥ አስቸጋሪ የሆነው የኢህአዴግ አካሄድ አስቸጋሪ ሆኖ ሳለ፣ መንግስት ለፍቅሩ ብቻ ሳይሆን ለጠቡም ደቦ የመፈለጉ አካሄድ ደግሞ ሌላው ከባድ እና ግራ አጋቢ ጉዳይ ነው፡፡

የኢህአዴግ የፍቅርም ሆነ የጠብ ደቦ ፍለጋ፣ የዜጎችን እጣፈንታ የሚወስን እየሆነ መምጣቱ ይብስ አሳሳቢው ጉዳይ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ኢህአዴግ የወደደውን መውደድ የጠላውን መጥላት ብቻ ሳይሆን አብሮ ማውገዝ ከሁሉም በመንግስቱ ጥላ ስር የሚኖር ዜጋ ግዴታ ወደመምሰሉ እየሄደ መጥቷል፡፡ በዚህ የማይስማማ እጣ-ፈንታው ሁለት ነው ወይ ቃሊቲ መውረድ ወይ መሰደድ፡፡ እለት እለት እየጨመረ የመጣው የተሰዳጅ እና የታሳሪ ቁጥርም በአመዛኙ ከዚሁ ከኢህአዴግ የልብ ሃሳብ ጋር የመመሳሰል እና ያለመመሳሰል ጉዳይ ነው፡፡ ለፍቅርም ሆነ ለጠብ ከመንግስት ጋር እኩል ማሰብ ደግሞ ተፈጥሯዊም አይደለምና ለዜጎች ትልቅ ፈተና ነው፡፡ የፈተናውን ክብደት የሚያሳዩ የኢህአዴግ የጠብ ደቦ ፍላጎቶችን ለማሳየት ሳምንት እመለሳለሁ፡፡