ኢህአዴግአዊው ልማታዊ መንግስት ውስን ከሆነው ሀገራዊ ሀብት አኳያ ሲታይ በኤድመን ተስፋዬ

በምድራችን ላይ የሚገኘው ሀብት ውስን (አላቂ) መሆን እና በአንፃሩ የሰው ልጅ ፍላጎት ገደብ አልባነት፣ ማንኛውም ሰው የፈለገውን ነገር በፈለገበት ሰአት እና ቀን እንዳያገኝ ምክንያት ከመሆኑም በላይ ለየትኛውም ግለሰብም ሆነ ሀገር ትልቁ ፈተና ከእጥረት ጋር የተያያዘ እንዲሆን አድርጓል፡፡ በሌላ በኩልም አንድ ሰው የፈለገውን ነገር በፈለገበት ሰአት እና ቀን አለማግኘቱ የተገደበ (ውስን የሆነውን) ገቢውን፣ ሰአቱን እና ሀብቱን ቅድሚያ ለሚሰጣቸው መሰረታዊ ነገሮቹ እንዲያውል ይገደዳል፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት እንደ ሀገር ትልቁ የኢኮኖሚ ዳራ በዋነኛነት ከእጥረት ጋር የተገናኘ ቢሆንም፤ በአለም ላይ ያሉ ሀገራት የየራሳቸውን ባህል፣ ሀብት (ቁሳዊም ሆነ ሰዋዊ)፣ ታሪክ ወዘተ ያገናዘበ የኢኮኖሚ ስርአት በመከተል፤ ከእጥረት ጋር የተገናኘውን ኢኮኖሚያዊ ዳራ ለመወጣት እንደሞከሩ እና እንደሚሞክሩ የኢኮኖሚ ታሪክ ላይ ትኩረት ያደረጉ ኢኮኖሚስቶች ይናገራሉ፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ ኢኮኖሚስቶች አራት አይነት (ባህላዊ፣ የእዝ፣ የገበያ መር እና ድብልቅ) የኢኮኖሚ ስርአት እንዳለ ስምምነት ላይ ቢደርሱም፣ ከእጥረት ጋር በተገናኘ ያለውን የኢኮኖሚ ዳራ ከመፍታት እና ከመቀነስ አኳያ የትኛው የተሻለው ነው የሚለው ላይ አንድ አይነት አቋምም ሆነ ስምምነት የላቸውም፡፡ መንግስታት የህዝብን ኑሮ ለማሻሻል በሚል የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ሊመጣ የሚችለው የሚፈሰው ሀገራዊ ሀብት በአንድ በኩል ከወቅታዊው የሀገሪቷ ህዝብ ችግር አኳያ፣ ከዘለቄታዊ ጥቅሙ አኳያ በሌላ በኩል ለመጪው ትውልድ ከሚያስረክበው ተራፊ ሀገራዊ ሀብት አኳያ ከተገናዘበ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት የመምጣቱ ዋስትና በመንግስታዊ ስርአት ባህሪ ላይ የተንጠለጠለ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህም በእኔ እምነት ኢህአዴግ የሚለፍፍለትን የኢኮኖሚ እድገት በአንድ በኩል የኢኮኖሚ እድገቱ ማሳያ ተብለው የሚቀርቡትን የልማት እንቅስቃሴዎች እንደ ህዝብ ካለብን ድህነት እና የምግብ ዋስትና ማጣት አንፃር፣ ድህነታችንን በመቅረፍ የምግብ አንፃር ያላቸውን ፋይዳ፣ ዘለቄታዊ ጥቅማቸውን የሚፈስባቸውን ሀገራዊ ሀብት ማእከል ባደረገ መልኩ፤ ኢህአዲጋዊውን የልማታዊ መንግስት ስርአት መፈተሸ የሚቻል ይመስለኛል፡፡

በልማታዊ መንግስት ስርአት ውስጥ የህዝብ ሚና እስኬት ድረስ ነው?

የልማታዊ መንግስት ንድፈ ሀሳብ፣ በዋነኛነት ማእከል የሚያደርገው መንግስት በኢኮኖሚ ስርአቱ ላይ ባለው የቁጥጥር እና የተሳታፊነት ስፋት መጠን ላይ ብቻ ነው፡፡ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ማብቃት በኋላ የጃፓን እና የምስራቅ ኤሽያ ሀገራት መንግስታት በሀገራቸው ኢንደስትሪን ለማስፋፋት ኢኮኖሚ ስርአቱን ተከላካይ በሆነ መልኩ በመምራትም ሆነ በኢኮኖሚ ስርአቱ ላይ ተሳታፊ በመሆን የአንበሳውን ድርሻ ወስደዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1980 ዓ.ም የላቲን አሜሪካ ሀገራት የብድር ቀውስ እና ከ1997 ዓ.ም የምስራቅ ኤሽያ ሀገራት የገንዘብ ቀውስ፣

ከአለም- አቀፋዊነት መስፋፋት እንዲሁም ኢኮኖሚን ከማረጋጋት፣ ትምህርት፣ ጤና እና መሰረተ-ልማቶችን ከማስፋፋት አንፃር መንግስት የሚኖረውን ሚና በተመለከተ በዋሽንግተኑ መግባቢያ ሰነድ ላይ የርዕዮት አለም ልዩነት ከመፈጠሩ ጋር በተያያዘ የልማታዊ መንግስት ስርአት በ20ኛው ክፍለ ዘመን እውቅና አግኝቷል፡፡ በሌላ በኩል ከልማታዊ መንግስት ጋር አንድ አይነት የሆነ ስርአት፣ ሆላንድን የመሳሰሉ የአውሮፓ ሀገራት በ 17ኛው እና በ18ኛው ክፍለ-ዘመን ስለመተግበራቸው የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ ይህም የሚያሳየው ልማታዊ መንግስት በሀያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የተጀመረ፣ አንዳንዶች እንደሚሉት እና እንደሚያምኑት የልማታዊ መንግስትን ንድፈ ሀሳብ ኢህአዴግ የፈጠረው አለመሆኑን ነው፡፡ ‘እከሌ የሚባለው ሀገር በልማታዊ መንግስት መርህ ነው ያደገው፣ እከሌ ኒዮ-ሊበራሊስት ነው እከሌ ልማታዊ ነው’ የሚለውን የአላዋቂ ክርክር ወደጎን ትተን፣ በልማታዊ መንግስት መርህ ኢኮኖሚያቸውን በጠንካራ መሰረት ላይ በመገንባት ህዝባቸውን ከድህነት ያወጡ ሀገራትን ታሪክ እነዚህ አገራት ባህላቸውን፣ ታሪካቸውን፣ ሀብታቸውን መነሻ በማድረግ እና የፖለቲካ ልዩነትን ወደጎን በመተው አሳታፊ የሆነ ፖሊሲ በመቅረጽ ስለተንቀሳቀሱ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በዋነኝነት ግን ህዝባዊ ቅቡልነት ስለነበረው መሆኑ አይካድም፡፡

የአለም ሀገራት የኢኮኖሚ ታሪክ እንደሚያሳየን መንግስታዊ ስርአቱ አንባገነን መንግስት በኢኮኖሚው ላይ የሚያደርገው ጣልቃ-ገብነት፣ ውስን በሆነው ሀገራዊ ሀብት የሚከናወኑ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ተጠቃሚ የሚያደርጉት የመንግስቱን ባለሟሎች እና ከመንግስታዊው ስርአት ጋር ተለጣፊ የሆኑትን የግል ባለሀብቶችን ብቻ ይሆናል፡፡ የአንባገነኑ ሙጋቤን ሀገር ዚምባቡዌ እና የአንባገነኑ ፒኖቼ ሀገር ቺሊ (በፒኖቼ አመራር ስር በነበረችበት ወቅት) ተመክሮ ለዚህ በቂ ማሳያ ይመስለኛል፡፡ መንግስት፣ በኢኮኖሚው ውስጥ በሚሣተፍበት የልማታዊ መንግስት ስርዓት ስኬት እና ውድቀት፣ ልማታዊ መንግስቱ ለመድብለ ፓርቲ ስርዓትም ሆነ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሁም ነፃና ገለልተኛ ተቋማት እንዲኖሩ ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ የፖለቲካ ስርአቱን ለኢኮኖሚ እድገት አጋዥ ለማድረግ፣ ለመድብለ ፖርቲም ሆነ ለዲሞክራሲያዊ ስርአት፤ እንዲሁም ለነፃ እና ለገለልተኛ ተቋማት መኖር ከፍተኛ አስተዋፅዖ የሚያደርግ የልማታዊ መንግስት ስርአት፤ በአስተማማኝ የኢኮኖሚ እድገት የህዝቡን ኑሮ ከማሻሻል ባለፈ በፖለቲካ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያግዛል፡፡ የልማታዊ መንግስትን መርህ በሚከተሉ ፖርቲዎች አማካይነት አሁን ላሉበት የኢኮኖሚ ደረጃ የበቁትን የሆላንድን እና የጃፓንን ታሪክ በማሳያነት ማቅረብ ይቻላል፡፡

ኢህአዴግአዊው ልማታዊ መንግስትስ ?

ኢሕአዴጋዊው ልማታዊ መንግስት፣ ድህነትን ለመቅረፍ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ረጅም የስልጣን ዘመን የግድ ነው የሚለውን ሀሳብ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካ ስርዓት ጋር በመግመድ ብልፅግናን አመጣለሁ የሚል ስርዓት ነው፡፡ በእንደእኛ አይነቱ ደሀ ሀገር ከላይ በጠቀስኩት መልኩ ልማታዊ መንግስትነትን ለአንድ ፖርቲ ብቻ ተለቆ ቢቀጥል የሚቀነሰው የህዝቡ ድህነት ነው ወይስ የባለስልጣኖቹ እና ሸሪኮቻቸው ድህነት ነው? የሚል ጥያቄ በማንሳት ማየት ተገቢ ነው፡፡

አፍሪካ በኒዮ-ሊበራሊዝም አስተሳሰብ ኢኮኖሚዋ ከማደግ ይልቅ አዙሪት ውስጥ መግባቱን በመተንተን ከዚህ አዙሪት ለመውጣት አፍሪካ የኒዮሊበራሊዝም አስተሳሰብን አሽቀንጥራ በመጣል፣ የልማታዊ መንግስን ስርአት መከተል እንዳለባት፣ ልማታዊ መንግስት ህዝቦችን ከድህነት በማውጣት እና በማነቃቃት ድህነት ቀራፊ ፖሊሲ የሚነድፍ እና የሚተገብር፣ ለረዥም ጊዜ በስልጣን ላይ የሚቆይ ፓርቲ አስፈላጊ ስለመሆኑ በመግለፅ ይህ ለረዥም ጊዜ በስልጣን ላይ የሚቆየው ፓርቲ ረዥም ጊዜ በስልጣን ላይ ለመቆየት ዋስትናው በሀገሪቷ በየጊዜው የሚያስመዘግበው የኢኮኖሚ እድገት መሆኑን የኢህአዴግ ጭንቅላት የነበሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ “African Development the dead ends and the new beginning” በሚለው የዶክትሬት ዲግሪ ሟሟያ ጥናታዊ ፅሁፋቸው ላይ ያትታሉ፡፡ አቶ መለስ፣ ኢህአዴግ ለሚከተላቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ዋነኛው ነዳፊ እንደመሆናቸው መጠን ከላይ የጠቀስኩት ጥናታቸው የስርዓቱን የልማታዊ መንግስት ትርጓሜና አፈፃፀም በግልጽ ያሣያል፡፡

እውቁን ኢኮኖሚስት ፕሮፌሰር ማርክ ኦንልሰን፣ አንባገነን መንግስታት ለልማት በሚል የሚያፈሱት ሀገራዊ ሀብት ቅድሚያ ስሌቱ የህዝቡን ኑሮ ማሻሻል ሳይሆን ለስርአቱ ከሚያስገኘው ገቢ እና ለህልውናው ካለው ፋይዳ (ወተትን ለማግኘት እንጂ ለላሚቷ በማሰብ ሳር ከማይሰጣት ግለሰብ ጋር በተመሳሰለ መልኩ) አንፃር በመሆኑ አንባገነን መንግስታት የብዙሀኑን ህዝብ ኑሮ የሚያሻሽል አስተማማኝ የኢኮኖሚ እድገት ሊያመጡ አይችሉም’ ይላል፡፡ ይህን የኦንልሰን ንድፈ ሀሳብ መነሻ በማድረግ የሀገራችን ግብርና ዘርፍ ልማታዊ ነኝ የሚለው ኢህአዴግ፤ ከሀያ ሶስት አመት በሁአላም በሀገራችን ዋነኛ የግብርና ምርታማነት ግብአት የሆነው ማዳበሪያ ብቸኛ አቅራቢ እራሱ መሆኑ፣ ለግብርና ቴክኖሎጂዎች መስፋፋት የሚመድበው በጀት ሲታይ፣ የሚከተለው የመሬት ፖሊሲ ከገበሬው ይልቅ ሹመኞችን መጥቀሙ ወዘተ የኢህአዴግ ልማታዊ መንግስትነት ፋይዳው ለማን እንደሆነ የሚያመላክት ይመስለኛል፡፡
ኢህአዴግ፤ ‘ልማታዊ መንግስትነኝ’ ከማለቱ ጋር በተገናኘ ልማት በሚል የዳቦ ስም ሀገሪቷ ላይ የሚፈሰው የሀገሪቷ ሀብት፣ ከሀገሪቷ ህዝብ ወቅታዊም ችግርም ሆነ ከዘለቄታዊ ጥቅም አኳያ የህዝብ የምግብ ዋስትና በመሆኑ፣ ለግብርና ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ኢህአዴግ ለግብርና ትኩረት አለመስጠቱ ከላይ ከጠቀስኩት የግብርናችን ተግዳሮት በተጨማሪ የግብርና ምርቶች የዋጋ ንረት ማሳያ ይመስለኛል፡፡ ኢህአዴግ በሚመራዊ ኢኮኖሚ ስርአት ውስጥ የሚታየውን ፖሊሲ ከመሸጥ (ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ለግለሰቦች ማሳወቅ) እስከ ፖሊሲን ለሸሪኮች ማመቻቸት፤ ኢኮኖሚያዊ ስርአቱን ለፓርቲው ሰዎች ብቻ ምቹ ማድረግን እንዲሁም መንግስታዊ ሌብነትን መነሻ በማድረግ ከግብርና ውጪ ባሉ የኢኮኖሚ ክፍሎች ላይም የሚፈሰውን ሀገራዊ ሀብት ለህዝቡ ከሚያስገኘው ዘለቄታዊ ጥቅም አንፃር ሲታይ መንግስት በኢኮኖሚያዊ እድገት የብዙሀኑን ህዝብ ኑሮ ከማሻሻል ይልቅ የሀገሪቷ ሀብት በጥቂት ግለሰቦች እና ቡድኖች የሚዘውሩት የኢኮኖሚ ኢምፖየር እንዲገነባ አድርጓል፡፡