ስንቱን ጉድ እንሰማዋለን!? ‹‹አዜብ መስፍንም በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ እንጠይቃለን››

Image
ጌታቸው ሽፈራው
ያች ስለ መገንጠል የተዶለተባት ደደቢት በዓለም ቅርስነት ትመዝገብ እየተባለ ነው አሉ፡፡ አሜሪካኖች እርስ በእርስ ተዋግተው አገር ገንብተዋል፡፡ ጣሊያንና ጀርመኖች ደም ተፋስሰው አገር አቁመዋል፡፡ ምን አልባት እነዚህ አገራት ለአገር ግንባታ (አንድነት) ደም የፈሰሰባቸው ቦታዎች በራሳቸው ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ይሰጧቸው ይሆናል፡፡ እንጅ ዩኒስኮን መዝግብልን ብለው የተጃጃሉ አይመስለኝም፡፡ ኧረ እንዲያው ቢጠይቁስ ስለ አንድነት አጀንዳ የተነሳበት ቦታ (የግድ ከሆነ) ቅርስስ ቢሆን ምን አለበት?

ደደቢት የጠባብ ‹‹ብሄርተኝነት›› እንጅ የአገር ግንባታ መነሻ አይደለችም፡፡ የዓለም ህዝብ ከህወሓት አላማ ምን ሊማርበት ነው ደደቢትን ዓለም በቅርስነት የሚሸከመው? ከዚህ በተቃራኒ ቢቻል በዓለም አቀፍ ደረጃ ካልተቻለ ደግሞ በአፍሪካ ደረጃ አድዋ የሚከበርና የሚታወስ ቦታ ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ምክንያቱም የአፍሪካ የነጻነት ትግልም የሚፈነጥቀው ከዚህ ታሪካዊ ቦታ ነውና! ግን ይህ ኢትዮጵያና አፍሪካውያን እንጅ ህወሓት እንደ ቡድን ጥቅም አያገኝበትም፡፡ ከአላማው ጋርም ፍጹም የተለያዩ ናቸው፡፡

አሊያም ህወሓት ራሱ ተዋናይ የሆነበትን የሀውዜን ጭፍጨፋ በዓለም ከተደረጉ አስከፊ ጭፍጨፋዎች መዝገብ የሚባል ነገር ካለ ቢገባ ምክንያታዊ ይሆናል፡፡ ወይንም ደግሞ ከደርግ ጋር የተደረገውና በሁለቱም ወገን በርካታ ኢትዮጵያውያንን የጨረሰው የእርስ በእርስ ጦርነትን አስከፊነት ዓለም እንዲማርበት ቢደረግ ችግር ላይኖረው ይችላል፡፡ ቢያንስ ኢትዮጵያውያንም ሌላው ዓለምም ይማርበት ይሆናል፡፡

ደደቢት ምን ባይ ነች በዓለም ቅርስነት የምትመዘገበው? እንዲያው ፈረንጆቹን ‹‹ደደቢትን በዓለም ቅርስነት መዝግቡልን!›› ሲባሉ ምንድን ነው የሚሰማቸው? መቼስ ፈርዶብን በእነሱ ምክንያት ኢትዮጵያውያን ጅሎች ናቸው አይደለም የምንባለው? ሌላውን ነገር ለብቻቸው፤ ስድቡን ግን አብረን እንጋተዋለን፡፡ አይ አገር የመጋራት እዳው! ሞኝ ባያፍር የሞኝ ዘመድ ያፍር አይደለም የሚባለው?

እነዚህ ሰዎች በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ መለስ ዜናዊ የተቀመጡበት ባርጩማ፣ አልኮል የጠጡበት መለኪያ፣ የለበሱት ፒጃማ….በዚህ ከቀጠለም ሚስታቸው (አዜብ) ሳይቀሩ በዓለም ቅርስነት ይመዝገቡልን ብለው ወደ ዩኒስኮ መንከራተታቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ጋሻጃግሬም ይመዝገብ የሚል ድርጅታዊ ውሳኔ ከተላለፈ ደግሞ ለሰውዬው ቀኝ እጅ ሆነው ህዝብ ሲያስበዘብዙ የኖሩት እነ በረከት፣ አባዱላ፣ ሽፈራው ሽጉጡ….በቁማቸው የፖለቲካ ሉሲዎች መሆናቸው ነው፡፡ አይጣልኮነው!

እኔ በበኩሌ ከደደቢት ይልቅ ራሱ ህወሓት በ‹‹ቅርስነት›› ባይሆን ባንዳች አስገራሚ መዝገብ ላይ ቢሰፍር ምክንያታዊ ነው ባይ ነኝ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በዓለም ገዥ ሆኖ ገንጣይነቱን አንጠልጥሎ የሚዞር አስገራሚ ቡድን ህወሓት ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ ገዥ ሆኖ ተገንጣይ ዓለም አይታ አታውቅም ነበር፡፡ አሁን ግን ጉዱ ህወሓት አለላት፡፡ በመሆኑም አንድ ቀን ትውልድ አፉን ይዞ ይስቅበት ዘንድ በአንዳች አስገራሚ መዝገብ ጎላ ብሎ ቢጻፍ ክፋት የለውም፡፡

እስከዛው ግን እነ አዜብ የስራ ሂደት ባለቤት ተቋቁሞላቸው በዓለም ቅርስነት የሚመዘገቡበት ሁኔታ እንዲመቻች አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እየጠየቅን ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ያለ አንዳች ተቃውሞ! ያለ አንዳች ድምጽ ታቅቦ! በቃ የባለራዩ ሚስት አዜብ መስፍን በቅርስነት ይመዝገቡ! ከተጃጃሉና ካሰደቡን አይቀር እስከዚህ ድረስ ነው እንጅ!