ምርጫ ምልክት መውሰድ እጅግ ተራ እና ትንሽ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ምርጫን ለመሳተፍ ማረጋገጫም ተደርጎ ሊቀርብ አይችልም!

* ምርጫው ላይ ለመሳተፍ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠናል
* በምርጫው ልንሳተፍም ሆነ ላንሳተፍ ውሳኔ የምናሳልፈው እኛ ሳንሆን ሂደቱ ነው
ትንሽ ስለ አንዳንድ ጉዳዮች ማብራሪያ አቀርባለሁ ዮናታን ተስፋዬ ረጋሣ

ኢትዮጵያ ውስጥ በህጋዊ መንገድ ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ምርጫ ስላለመግባቱ እንጂ ምርጫ ስለመግባቱ ዜና ሲሆን በጣም ግራ ያጋባል፡፡ ምርጫን መሳተፍ አንዱ የትግል አካል የሆነውን ያህል አለመሳተፍ የራሱ የሆነ ፋይዳ አለው፡፡ ያን የሚወስነው ግን ሂደቱ እንጂ ፓርቲዎቹም ይሁኑ ምርጫ ቦርዱ አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር በሂደቱ ውስጥ አንድ ፓርቲ ወይም ፓርቲዎች አንሳተፍም ሊሉ ይችላሉ (ህጋዊነትም አለው)፡፡ ምክንያታቸውንም በዝርዝር አስቀምጠው መግለጫም ይሁን ሌላ ሌላ ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ያም ዜና ከመሆን ባለፈ ባጠቃላይ የህዝቡንም የዓለም አቀፍ ማሕበረሰቡንም ትኩረት ያገኛል፡፡
ከዚህ ውጪ ግን አንዱ ያለ ቅድመ ሁኔታ ምርጫ እሳተፋለሁ ስላለ እና ሌላው ደግሞ ሂደቱ እንዲወስን እድል ስለሰጠ ምርጫ ተሳታፊና ምርጫውን የማይሳተፍ ብሎ ማቅረቡ በራሱ አንድም ስህተት ነው ሲልም ከንቱ ራስ ማዋደጃ ፕሮፖጋንዳ ነው፡፡ ይህ ግልፅ ነገር እንዲገባው ያልፈለገ እና ህመም የሆነበት ማስታገሻ ወስዶ ቢያርፍ መልካም ነው፡፡
ጓደኞቼም ሆነ እኔ ኢሳትና ቪኦኤን ጨምሮ በብዙ መገናኛ ብዙኃን እና በዲፕሎማቶች በኩል በተደጋጋሚ በምርጫው ጉዳይ ላይ ሰማያዊ ፓርቲ የያዘውን አቋም በተጠየቅንበት ወቅት የሰጠነው የማያሻማ መልስ ከላይ ያሰፈርኩትን ነው (ሚዲያዎቹ ላይ ፈልጎ መስማት ይቻላል)፡፡ ‹‹ምርጫ ለመሳተፍም ሆነ ላለመሳተፍ አሁን የመወሰኛ ጊዜ አይደለም፤ ሂደቱ እንጂ እኛ(ተቃዋሚም ይሁን ኢህአዴግ) አሁን ልንወስነው የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡›› ይህ በግልፅ የሚያሳየው ነገር ሂደቱ ውስጥ ተሳታፊ እንደምንሆን ሲሆን ለመጨረሻው ውሳኔ ግን በወቅቱ የሚፈጠረው ሁናቴ እንደሚወስን ነው!
እንደ አንድ ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ የምርጫ ጉዳይ ኮሚቴና ጊዜውን መሰረት ባደረገ 70 ሰው ያቀፈ የምርጫ ግብረሃይል አቋቁመን፣ የዓመቱ እቅዳችንም በምርጫ ላይ ሆኖና በትብብሩም የጀመርነው ዘመቻ ‹‹ነፃነት ለፍትሓዊ ምርጫ›› እያለ ለምርጫ የማንዘጋጅ አስመስሎ ማቅረቡ ምንአልባት ከተሳሳተ ግንዛቤ አልያም ከተንኮል ያለፈ ሊሆን እንደማይችል ግልፅ ነው፡፡ የምርጫ ምልክትን መውሰድም የሂደቱ አካል እንጂ የመጨረሻው ውሳኔ አይደለም፡፡ ከዚህ ተነስቶም በእርግጠኛነት ምርጫ ይሳተፋሉ ብሎ መደምደም ተገቢ ነው ብዬ አላምንም! ባጠቃላይ ግን ለምርጫው ያስቀመጥናቸውን ቅድመ ሁኔዎች በሂደቱ የማይመለሱ ከሆነ ያኔ ውሳኔው ከነምክንያቱ ይፋ ይሆናል ማለት ነው፡፡
በግልፅ ቋንቋ ምርጫውን ለመሳተፋችንም ሆነ ላለመሳተፋችን አጠቃላይ ሂደቱ፣ በሂደቱ ውስጥም ያነሳናቸው ጥያቄዎችና ያስቀመጥናቸው ቅድመ ሁኔታዎች እንጂ ማናችንም ወሳኝ ልንሆን አንችልም! የምርጫ ምልክትም ስንወስድ መነሻችን ይኸው እውነታ እና ነባራዊ ሁኔታ ብቻ ነው! ይህ የኛ መንገድ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ያለ ቅድመ ሁኔታ ባለው የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ምርጫ እሳተፋለሁ ብለው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ምንም ይሁን ምንም፣ ሂደቱ ይመርም አይመርም ምርጫውን ለመሳተፍ ወስነው ወደ ስራ የገቡትን ውሳኔያቸውን አከብራለሁ፡፡
የመረጥነውን መንገድ መደገፍም መንቀፍም ያባት ነው፤ እየጠመዘዙ ሌላ መልክ እንዲይዝ ማድረግ ግን ራስን ከማስገመት ያለፈ ጥቅም ያለው መስሎ አይሰማኝም፡፡
(ይህ ርዕስ ከዚህ በላይ መወያያ ባይሆን ምኞቴ ነው!)
ሊንኩን በመጫን ለምርጫ ቦርድ የስገባውን ደብዳቤ እና ያስቀመጥናቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ይመልከቱ፡-
https://www.facebook.com/semayawiethio/ … =3&theater