ኢህአዴግ የታገለለት የቡድን መብት በተግባር የታለ!? – ድምፃችን ይሰማ

ኢህአዴግ የታገለለት የቡድን መብት በተግባር የታለ!?
ያቀረብነው ‹‹የሃይማኖት ነጻነት ይከበርልን›› ጥያቄ የዜግነትም የቡድንም መብት ቢሆንም ይኸው ሶስት ዓመት ሙሉ ምላሽ ተነፍጎታል!
ሰኞ ህዳር 29/2007

ሃገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ብሄር ብሄረሰቦች በጋራ የሚኖሩባት እንደመሆኗ መጠን ህብር የተላበሰ ማህበረሰብን አቅፋለች። በተመሳሳይም ብዝሃ ሃይማኖትን መርህ አርርጋ ሃይማቶችን ከጥንስሱ ጀምሮ ተቀብላ ያስተናገደችም ሃገር ነች። ይሁን እንጂ ብሄር ብሄረሰቦችም ይሁኑ ሃይማኖቶች በሃገሪቱ አስተዳዳሪዎች በእኩል የታዩበት እና እንደዜጋ በተመሳሳይ መልኩ የተዳደሩበት የታሪክ አጋጣሚ አናሳ ነው። ያም ሆኖ ማህበረሰባችን እንደ ህዝብ የሚደርሱበትን የበላይ ተጽዕኖዎች ተቋቁሞ ለዘመናት አብሮ ኖሯል።

የታሪካችን ዳራ የሚያሳየው አብይ መገለጫ ይህን ቢመስልም ቅሉ የነበሩትን የበደል እና ኢ-ፍትሃዊነት ፈተናዎች መቋቋም ሲሳናቸው ለአማራጭ መፍትሄ የተነሱበት አጋጣሚ በርካታ ነው። በሃገራችን በከፍተኛ ህዝብ ቁጥር የሚወከሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ከማህበረ-ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ህይወት በስልት እና በግዳጅ ሲገለሉ ማስተዋል የተለመደ የታሪካችን ገጽታ ነው። ስለዚህም ነው መንግስት ለብሄር ጥያቄም ይሁን የሃይማኖት ነጻነትን ለሚሹ የህብረተሰባችን ክፍሎች ተገቢ ምላሽ መስጠት የሚያሻው። ይህ ባልሆነበት ግን ሁለቱም ቢሆን መብታቸውን ለማስከበር መነሳታቸው አይቀሬ ነው። ይህም በሃገራችን የቅርብ ጊዜ ታሪክ የተስተዋለ እውነታ ነው። ከእነኚህ ተገፊ የህዝብ አካላት መካከል የተወሰኑ ብሄር ብሄረሰቦች እና ሃይማኖታዊ ቡድኖች ቀዳሚዎቹ ሲሆኑ በስርዓተ ጾታ ተጽዕኖ ስር የወደቁ የሃገራችን ሴቶችም ተመሳሳይ መድሎ እና መገለልን አስተናግደዋል።

ይህ ሲባል አንድ የሃገራችን ሴት በሴትነቷ ከሚደርስባት ጫና ባሻገር በምታምንበት ሃይማኖት፣ ብሎም በወከለችው ብሄረሰብ መገለል ምክንያት ድርብርብ ግፍን ልታስተናግድ የምትችልበት እድል ሰፊ ነው። በእርግጥም ከተለመደው የስርዓተ ጾታ ጫና ባለፈ መንግስት በወሰደው የሃይል እርምጃ እና የሒጃብ ማገድ ጸረ-ሴኩላሪዝም ዘመቻ ብዙ ሙስሊም ሴቶች ሰለባ መሆናቸው ቀጥሏል። በአንጻሩም የአንድ እምነት ተከታይ በሃይማኖቱ ሰበብ ከሚደርስበት መገፋት ባለፈ በብሄሩ ምክንያትም ለመገለል የሚዳረግበት አሰራር ለዘመናት ተስተውሏል። በመሆኑም ከብሄራቸው እና ቋንቋቸው ጋር የተዛመደ መድልዎን ሲቃወሙ ከብሄር ጉዳይ ጎን ለጎን የሃይማኖት ነጻነት ጥያቄን አብረው ያነገቡ ቡድኖችን ማግኘት የተለመደ ይሆናል። በብዙዎቹ የሃገራችን ክፍሎች እንደሚስተዋለው የአንድ ብሄር ተወላጆች በአንድም ይሁን በሌላ የታሪክ አጋጣሚ ሙሉ በሙሉ፣ አልያም በአብዛኛው የአንድ ሃይማኖት ተከታይ ሊሆኑ ይችላሉና። የሃገራችን ነባራዊ ገጽታ እንደሚያስረዳው ተገፊ የሆኑ የሃይማኖት እና የብሄር መገለጫዎች በአንድ የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ተነባብረው የመገኘት እድላቸው ሰፊ ነው። ስለሆነም መንግስት የብሄር መብትን ማስከበር የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ቢችል እንኳን የሃይማኖት እኩልነትን እስካላረጋገጠ ድረስ እነኚህ የሃገራችን ህዝቦች በበደል አዙሪት ውስጥ ይኖራሉ ማለት ነው። ከዚህ መሰል የበደል ድግግሞሽ ለመላቀቅ ሁለቱንም የቡድን መብቶች ያለምንም መሸራረፍ በህገ-መንግስቱ መርሆች መሰረት ማረጋገጥ ብቸኛ አማራጭ ሆኖ ይታያል።

ይሁን እንጂ የኢህአዴግ መንግስት ‹‹ሴኪውላር (ዓለማዊ) መንግስት በመመስረት አስከብሬዋለሁ›› የሚለውን የሃይማኖት እኩልነት አጀንዳ መልሶ በቀን ብርሃን ሲንደው ተስተውሏል። ‹‹መንግስታዊ ሃላፊነትን ከሃይማኖታዊ ሚና ነጥያለሁ›› ያለው መንግስት በሃይማኖታችን አዛዥ ናዛዥ ከነበሩት ቀደምት ሃይማኖታዊ መንግስታት መሪዎች በምንስ ተለየ? ሌሎች አካላትን ‹‹የአጼውን ስርዓት ናፋቂ›› ሲል የሚያወግዝበትስ አቅም ይኖረዋልን? ለቡድን መብት መከበር የታገለ እና በተግባርም እውን መሆኑን የሚሻ ቢሆን ኖሮ ሙስሊሙን ከሃገራችን ሁለገብ የህይወት ዘርፍ ማግለልን እና ሃይማኖታዊ የቡድን መብቱን በጠራራ ጸሃይ መግፈፍን ጀብዱ አድርጎ ሊቆጥር ባልቻለ ነበር። መንግስት ለቡድን መብት ዘብ በቆመ ኖሮ ባለፉት ሶስት የትግል ዓመታት ላነሳናቸው ህገ መንግስታዊ የእምነት ነጻነት ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ በህጋዊ መንገድ ሊሰጥ በቻለ ነበር። ቀደም ካሉት ዓመታት ጀምሮ የእምነት ተቋሞቻችንን በመቆጣጠር በሃይማኖታችን ላይ የተፈጸመው ደረቅ ጣልቃ ገብነት ከጅምሩ የሃይማኖት እኩልነት ጥያቄን ‹‹ጥያቄ ምልክት ውስጥ›› ባላስገባም ነበር።

ሙስሊሙን የማጥቃቱ ዘመቻ ሙስሊም ሴቶችን እና ወጣት ተማሪዎችን በስመ ሴኩላሪዝም ከትምህርት በማፈናቀል እየተተገበረ ይገኛል። በመሆኑም የኢህአዴግ መንግስት ረጅም ዘመን ትግል ለሃይማኖትም ሆነ ለጾታ እኩልነት ከወሬ ያለፈ ቁርጠኝነት እና ለመርህ ተገዥነት እንዳላሳየ ሙስሊሙ ላነሳቸው የመብት ጥያቄዎች ጆሮ ከመንፈጉ እና ከዚህ ሙስሊም ሴቶችን አነጣጥሮ ከሚያጠቃው መንግስታዊ መድሎ የበለጠ ሁነኛ ማሳያ የለም። በተለይ ደግሞ መንግስት በደነገገው መመሪያ ምክንያት በርካታ እህቶቻችን ጦሳቸውን እያዩበት ያለው ሒጃብ ኢህአዴግ ‹‹እኩልነትን አጎናጸፍኳቸው›› በሚላቸው ብሄሮችም ዘንድ እንደ ባህል መዘውተሩ አንድ እውነታ ነው። እነኚህ ብሄሮች ባህላቸው እና ቋንቋቸው እውቅና ከተቸረው አለባበሳቸውንም በነጻነት ሊተገብሩ የሚችሉበት አጋጣሚ በአመት አንዴ በጭፈራ በሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ብቻ ሊሆን አይገባም። የቡድን መብት የሆነው የብሄር እኩልነት እና የሃይማኖት ነጻነት ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ከሚውልበት ከዚህች የአንድ ቀን የሚዲያ ሽፋን ሊያልፍ ይገባል። በዓመት አንዴ የሚደረግ ጭፈራ የእኩልነት ማሳያ እና መለኪያ ፈጽሞ ሊሆን አለመቻሉን መንግስት ራሱ የሚገነዘበው እውነታ ነው። በብሄር ብሄረሰቦች በዓል ላይ ሂጃብ መልበስ መብት እና ባህል ተደርጎ በትምህርት ተቋማት ግን መታገዱ ማን የት ላይ እንዲኖር እንደተሳበ የሚያረጋግጥ ነው፡፡

በዚህ ረገድ መንግስት በ‹‹ልዩ ድጋፍ›› ወደዩኒቨርስቲ አመጣሁ የሚላቸውን የ‹‹ታዳጊ›› ክልል ተወላጅ ሴቶች በአለባበሳቸው ምክንያት ብቻ መልሶ ከዩኒቨርስቲው በሃይል እያባረረ ነው። እውን ታዲያ የታዳጊ ክልሎችን እና በውስጣቸው የሚኖሩ ብሄሮችን የወደፊት እጣ ፈንታ ሊቀይሩ የሚችሉ የተማሩ የሰው ሃይሎችን እያፈናቀሉ ‹‹በልዩ ድጋፍ የክልሎችን ዓቅም ገነባን፣ ሴቶችን አበቃን›› ለማለት ያስደፍራልን? ይህ የመንግስት መድሏዊ አሰራር የሴቶችን፣ ሙስሊሞችን፣ ብሄር ብሄረሰቦችን (ባህሎችን) እና የታዳጊ ክልሎችን ተዋጽዖ የሚፈታተን ከመሆኑም በላይ በየትኛውም መልኩ የቡድን መብት ለብሄሮችም ይሁን ለጾታዎች፣ እንዲሁም ለሃይማኖቶች እንዳልተረጋገጠ የሚያመላክት አብይ ተጨባጭ ነው። በተለይ ይህ እውነታ በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ ጎልቶ የሚታይ መሆኑ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ‹‹የመንግስት የቡድን መብት ማስከበር ሂደት ሆን ተብሎም ይሁን በቸልታ ለምን እኛን አይመለከትም? ለምንስ መድልዎ ይፈጸምብናል?›› የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ ይገፋል።

አዎን! የቡድን መብት አስከብራለሁ የሚለው መንግስት ከቃላት ጨዋታ ባለፈ በተግባር የታገዘ መሬት ላይ የሚወርድ መፍትሄ መሻት ግድ ይለዋል። በመርህም ይሁን በአፈጻጸም ረገድ የብሄር እና የእምነት ነጻነትን እና እኩልነትን ማረጋገጥ ያልቻለ መንግስት ህዝብን የማስተዳደር የሞራል ብቃት ሊኖረው አይችልም። በተለይም ለዘመናት ታገልኩለት ለሚለው እና ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ለሚደሰኩርለት የቡድን መብት ጥያቄ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሄ ሰጥቶ ለጉዳዩ መቋጫ ያላደረገ መንግስት እንደምንስ ‹‹ለቡድን መብት ታጋይ እና ጠበቃ ነኝ›› ሊል ይቻለዋል!? ለሃገራችን ግማሽ ህዝብ መሰረታዊ የህልውና ጉዳይ የሆነውን የእምነት መብት ገርስሶ ‹‹ለሃይማኖት እኩልነት ሰራሁ›› ቢል ማንስ ይሰማዋል!? ‹‹ንግግርህን እንዳልሰማ ተግባርህ ይጮህብኛል›› እንዲል ብሂሉ ከንግግር በላይ ጮሆ የሚናገረው እና ሰሚ ጆሮ የሚያገኘው ተግባሩ አይደለምን!!? የቡድንም ይሁን የተናጠል መብቶች በቃላት ሽንገላ፣ በአሰልቺ ፕሮፖጋንዳ እና በሚዲያ ልፈፋ ሊመሰረቱ አይችሉም። ይህ ሁሉ መሬት ላይ ጠብ የሚያደርገው ምንም ፋይዳ የለውምና!! ህዝብ በዕለት ተዕለት ህይወቱ ሊያስተውል የሚችለውን እውነተኛ እኩልነት እና የመብት ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ይሻል። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ግን መብትን ከመጠየቅ ይልቅ ከጠባቂነት ተላቆ ወደማስከበር ምዕራፍ ይሸጋገራል። ባለፉት ሶስት ዓመታት የተስተዋለው ህዝባዊ የመብት ማስከበር እንቅስቃሴ የሚያመላክተውም ይህንኑ ነው።

ዛሬ መንግስት ህዝብን ጆሮ ሰጥቶ ሊያደምጥ ግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ተደርሷል። ህዝብ በተራ ሽንገላ የሚታለልበት ዘመንም አልፏል። ከሌላው የዓለማችን ክፍሎች በተለየ የሰለጠነ አካሄድ ‹‹መብቴን አላስነጥቅም›› ማለትን መርሁ አድርጓል። ይህ ህዝብ ‹‹መሪዎቹ›› ለዘመናት ታገልንለት ቢሉም በተግባር ግን እውን ላላደረጉለት የቡድን መብትም ይሁን ግለሰባዊ ነጻነቶች መከበር በሰላማዊ መንገድ መትጋቱን ይቀጥላል። ከገባበት ‹‹የመብቴ ይከበር›› ትግልም ምንም አይመልሰውም – የመብቱ በእውን መረጋገጥ ሲቀር!!

ህዝብ መርህን ባማከለ መልኩ እንደሚፈልገው መኖርን እንጂ እንዲኖር በተደረገው መልኩ ማሰብን አይሻም። ላለፉት ሁለት ዓስርት ዓመታት የተሰበከውን ሁሉ ጠንቅቆ ተረድቶ አፍረጥርጦ መጠየቅን እና ‹‹ለምን?›› ማለትን ተለምዶው አድርጎታል። ይህ የህዝብን የብስለት ደረጃ አመላካች ነው። መብት እና ግዴታውን ለይቶ የተረዳ ህዝብን ፈጽሞ እያታለሉ መኖር የማይቻል ሆኗል። አልገዛም ባይነት እና ለጭቆና እምቢተኝነትን በስብዕናው የተላበሰ ዜጋ በግዳጅ አምባገነንነትን ሊጭኑበት አይፈቅድም። ያለው የህግ መርር እንዲተገበር በህጋዊ መንገድ መጠየቁም አይቀሬ ነው፤ ማስተካከል የማይችል የስልጣን ጥመኛ ሲገጥመው ግን መብት እና ፍላጎቱን የሚያሟላበትን እና የሚያሟላለትን አማራጭ ለመፈለግ ይገደዳልና።

በእውን የቡድን መብት መከበሩን ማረጋገጥ ካስፈለገ በማህበረ-ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ፣ እንዲሁም ሌሎች ተቋማዊ አሰራሮች የሁሉንም አቻ ተሳታፊነት በተግባር ማሳየት የግድ ነው። በማህበራዊ ግልጋሎት ተደራሽ ያልሆነን፣ በልማት ፖሊሲ ያልታቀፈን፣ በአግላይ ፖሊሲ የተገፋን፣ በህግ ስርዓቱ ተበዳይ የተደረገን አንኳር የህዝብ ክፍል ይዞ ‹‹የብሄሮችን እኩልነት አረጋገጥኩ›› ብሎ በየዓመቱ መዘመር የብሄሮች እና የሃይማኖቶች እኩልነትን ከወረቀት ባለፈ ሊያረጋግጥልን አይችልም። በማደግ ላይ ባለች ሃገር ውስጥ ‹‹ታዳጊ›› የሚባሉ በርካታ ክልሎች እና ብሄረሰቦች ባሉበት ሁነት የብሄሮች እኩልነትን መረጋገጥ የሚያሳይ ተጨባጭ አስረጂም አይገኝም። በተለይ ደግሞ እነኚህ ክልሎች እና ብሄሮች በብዛት የአንድ ሃይማኖት ተከታዮች መሆናቸው ግምት ውስጥ ሲገባ እና በሌሎች ክልሎች እንደሚገኙት የእምነት ወንድሞቻቸው ሁሉ እነሱም በእምነታቸው ምክንያት በደል እና የሃይማኖት መብት ጥሰት ማስተናገዳቸው የሃይማኖት እኩልነትም እንዳልተረጋገጠ በቂ ማሳያ ነው።በመሆኑም እውነተኛ ፍትህ እና እኩልነት የሰፈነበት ሁለንተናዊ ህይወት በሃገራችን ላሉት ሁሉም ብሄሮች እና ብሄረሰቦች፣ እንዲሁም እምነቶች (ሃይማኖቶች) እንዲረጋገጥ ማድረግ ለነገ የማይባል አጣዳፊ የመንግስት ግዴታ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

መንግስት ወደራሱ ዞር ብሎ የሚናገረውን እና የሚፈጽመውን ተዛምዷዊነት ፈትሾ በግልጽ ተግባሩን እንደ ቃሉ ማድረግ መጀመር ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ካልፈቀደ ደግሞ ህዝብን ተግባር አልባ በሆነ ጮሌ ምላስ ለመሸንገል መታገሉን ትቶ በአዋጅ የመንግስት ፖለቲካዊ ማዕዘናትና እኩልነት ጽንሰ ሐሳቦች መፍረሳቸውን ሊያውጅ ይገባል!! ያኔ ህዝብም የ‹‹ህግ ይከበርልን›› ጥያቄውን ፍትህ እስኪሰፍን እና መብቱ እስኪከበርለት በቁርጠኝነት ይገፋበታል፤ አልያም ‹‹ፈጽሞውኑ ህግ የለም!›› ሲል ስለ ህጋዊነት ይሰብካል!!

ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምፃችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!

Image