” መንግስት ለ23 ዓመታት ሙስሊሙን ማህበረሰብ በቀበሌ ምርጫ እያካሄደ ጨፍልቋል፥ አሁንም ለመጨፍለቅ ነው፥ ከጨፍላቂዎቹ አንዱ ደግሞ አ/ቶ ሪደዋን ሁሴን ናቸው” ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
የፍርድ ቤት ሙሉና የተጣራ ዘገባ በቂሊንጦ ልሳን
የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅና የፋክት መፅሄት ዓምደኛ እውቁ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እና ኡስታዝ ያሲን ኑሩ ለኮሚቴዎቻችን አስደናቂና አስደማሚ ምስክርነታቸውን ሰጡ።
⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄
★የቂሊንጦ ልሳን
(የኢትዬጲያዊያን ሙስሊሞች ድምፅ)
⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄⇄
ህዳር 25/2007 ዕለተ ሃሙስ
በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ታስረው ጉዳያቸውን CMC ከዲቦራ ት/ቤት አጠገብ በሚገኝው በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት እየተከታተሉ የሚገኙት የህዝበ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎቻችንና ወንድሞቻችን በዛሬው እለት እውቁ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን አቅርበው አስደናቂ የመከላከያ ምስክርነት ቃሉን እንደሰጠ ተገለፀ።
እንደሚታወሰው ትላንት ህዳር 24/2007 ዕለተ ረቡዕ በዋለው ችሎት የቲሞች አባት የሆኑትና በነኡስታዝ አቡበክር አህመድ የክስ መዝገብ 12ተኛ ተከሳሽ የሆኑት ኡስታዝ ኑሩ ቱርኪ ለ9ኛ ተከሳሽ ለሆኑት ለኡስታዝ አህመድ ሙስጠፋ ሲሆን በተለይም በጭብጡ ላይ ማዕከላዊ ተብሎ በሚጠራው እስር ቤት የደረሰባቸውን የህግ ጥሰትና ኢ-ሰብዓዊ ድብደባና እንግልቶችን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። በማያያዝም ቃሉን በሃይል እንደሰጠና አካላዊ ድብደባው አሁን ድረስ ምልክቱ እንደሚታይ ገልፀዋል።
በፍርድ ቤቱ ቀነ ቀጠሮ መሰረትም መሪዎቻችንና የሰላም አምባሳደሮቻችን በችሎት የቀረቡ ሲሆን ለተከታታይ ጊዜያት ዳኞች እንዲቀርብ ትዕዛዝ ቢሰጡም በማረሚያ ቤቱ ያረባ ምክንያት የተነሳ ያልቀረበው፥ ህዳር 17/2007 ለመጨረሻ ጊዜ ዛሬ እንዲቀርብ በታዘዘው መሰረት ትላንት አመሻሹ ላይ ከታሰረበት ከዝዋይ ማረሚያ ቤት ወደቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የመጣው የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅና የፋክት መፅሄት ዓምደኛ እውቁ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ አስደናቂና አስደማሚ የመከላከያ ምስክርነቱን ለኮሚቴዎቻቻንና ለወንድሞቻችን ሰጥቷል።
እንደሚታወቀው የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅና የፋክት መፅሄት ዓምደኛ እውቁ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 9ኛ ወንጀል ችሎት፣ ጥቅምት17 ቀን 2007 በህገ መንግስቱ የተፈቀደውን የመፃፍና የመናገር መብት በመጣስ የፌደራሉ አቃቤ ህግ ካቀረባቸው 3ት ክሶች ውስጥ የወንጀል ህግ 257(ሀ)ን በመተላለፍ የተመለከተውን "በፍትህ ጋዜጣ ላይ አመፅ የሚቀሰቅሱ ጽሑፎችን በራሱና በሌሎች አመንጭነት እንዲታተሙ ማድረግ" በሚለው በአንዱ ክስ ብቻ የ3ት አመት ፅኑ እስራት እንደፈረደበት ይታወቃል።
ዛሬ ህዳር 25/2007 ዕለተ ሃሙስ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በማረሚያ ቤት የፖሊስ አባላት ታጅቦ በፍርድ ቤት ቀርቦ የመከላከያ ምስክርነቱን የሰጠ ሲሆን ያስረዳውም ጥር 11/2004 በታላቁ አወሊያ መስጂድ ቅጥር ጊቢ እንደተገኝ በመግለፅ ሶስቱን ጥያቄዎች ህዝቡ እንደጠየቀ፣ ምርጫው ፍፁም ሰላማዊ ና ህዝባዊ እንደነበር፣ የጥያቄው መነሻ ህዝበ ሙስሊሙ እንደሆነ፣ ኡስታዝ ከሚል ሸምሱ ለህዝቡ ጥያቆዎቻችሁን አቅርቡ ብሎ በመድረኩ ተናግሮ ህዝቡም በወረቀት እየፃፈ እንደሰጠ፣ በአጠቀላይ ምርጫው ፍትሃዊ እንደነበረና ኮሚቴዎቹም በህዝብ እንደተመረጡ አስረድቷል።
በመቀጠልም ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጥር 11/2004 ላይ ጥር 18/2004 እንገናኝ ብለው ቀጠሮ በሰጡት መሰረት በአወሊያ እንደነበር በመግለፅ በውቅቱም ከህዝቡ የመጡትን ጥያቄዎች ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጠቢያ እና ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዳደረሱ በመድረክ መግለፃቸውን አስረድቷል። የሙስሊሙን ማህበረሰብ ጥያቄዎችና የኮሚቴውን ሂደትም በሚያዘጋጀው ጋዜጣ ላይ እንዳወጣውምገልፆዓል።
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ሃምሌ 9/2004 የህግ አዋቂውን ኡስታዝ ካሚል ሸምሱን፣ ኡስታዝ አቡበክር አህመድን፣ ኡስታዝ አህመድ ሙስጠፋን፣ የታሪክ ሙሁሩን ኡስታዝ አህመዲን ጀበልን ቃለ መጠይቅ ማድረጉን በመግለፅ በቃላ መጠይቁ ላይም በዋናነት የሚያጠነጥነው ጥያቄዎቻቸው እንዳልተመለሱና ጥያቄውም እስኪመለስ ድረስ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንደሚቀጥሉ እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።
ተመስገን ደሳለኝ አያይዞም የመንግስት ባለስልጣን የሆኑት አ/ቶ ሪድዋን ሁሴን በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ በመቅረብ "ኮሚቴው አላማው ኢስላማዊ መንግስት ማቋቋም ነው" ብለው መግለጫ ሲሰጡ ማየቱንና ኡስታዝ አቡበክርን ስለሁኔታው ጠይቆት በጭራሽ አላማቸው እንዳልሆነ መግለፁን አስረድቷል፤ ተመስገን ጨምሮም በወርሃ መስከረም የተካሄደው የመጅሊስ ምርጫ መንግስት በቀበሌ ይሁን ያለው " መንግስት ለ23 ዓመታት ሙስሊሙን ማህበረሰብ በቀበሌ ምርጫ እያካሄደ ጨፍልቋል፥ አሁንም ለመጨፍለቅ ነው፥ ከጨፍላቂዎቹ አንዱ ደግሞ አ/ቶ ሪደዋን ሁሴን ናቸው" ብሎ አስደማሚ ንግግር አርግቷል።�
በቀጣይም ኡስታዝ ያሲን ኑሩ በነአቡበክር አህመድ መዝገብ ለተካተቱት ለኡስታዝ ሙራድ ሽኩር የመሰከሩ ሲሆን በተለይም ማዕከላዊ እስር ቤት በተለምዶ ሳይቤሪያ ተብሎ በሚጠራው ክፍል ውስጥ አብረው እንደነበሩ በመግለፅ የተፈፀመበትን የመብት ጥሰትና ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ አጋልጠዋል።
ኡስታዝ ሙራድ ሽኩር ኮሚቴው ኢስላማዊ መንግስት ሊያቋቁም አቅዷል፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶቹ ከአልቃዒዳ ጋር ግንኙነት አላቸው…ወዘተ እያሉ እየደበደቡና መስክር እያሉት እንደነበር ኡስታ ያሲን ገልፆዓል።
በማያያዝም ለኡስታዝ ሙራድ ሽኩር "ያሲን ጋር አብረን አንድ ክፍል ውስጥ ለምን እንዳረግንህ ታውቃለህ? አይተከዋል አይደል እንዴት ጨርቅ እንዳረግነው? ከእሱ እንድትማር ነው አንድ ክፍል ላይ ያስገባንህ" ይሉት እንደነበር ለፍርድ ቤቱ ገልፆዓል።
እውቁ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እና ኡስታዝ ያሲን ኑሩ የመከላከያ ምስክርነታቸውን ከሰጡ በሁዋላ በፌደራሉ አቃቤ ህግ የቀረበላቸውን መስቀለኛ ጥያቄዎች በአስደናቂ ሁኔታ መልሰው ችሎቱ ተጠናቋል።
የፍርድ ሂደቱ ነገም ይቀጥላል።
ፍትህ ለኮሚቴዎቻችን!
ፍትህ ፍትህን ለተነፈጉ!
ሰላምና መረጋጋት ለኢትዮጲያ ህዝብ!
የጊዜ፣ የገንዘብ፣ የዕውቀት…መስዋዕትነት ተከፍሎባቸው የሚሰሩ ዘገባዎችን ሼር እና ኮፒ በማድረግ እንዲሁም በየሰሌዳን፣ በየጉረፑ፣ በየፔጁ በመለጠፍ መረጃውን ለሰፊው ማህበረሰባችን በማሰራጨት ኢስላማዊ ግዴታዎን ይወጡ!!!! ይጠቀማሉ!!! ኢንሻ አላህ