የአብዮት ነገር…

Eyasped Tesfaye…….(የግል ዕይታ)
‹‹……ሪቮሉሽን የአዳራሽ ዙሪያ አመፅ አይደለም፤ የሰፊው ህዝብ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ሰፊው ህዝብ ካልተሳተፈበት፣ ካልደገፈው፣ አይሆንም፤ አይፀናምም፡፡ የጥቂቶች አመፅ በሌሎች ጥቂቶች አመፅ ይገለበጣል፡፡ መሰረታዊ ለውጥ፣ በሰፊው ህዝብና በጨቋኝ መደቦች መካከል የሚካሄደው የትግል ፍሬ ነው፡፡….››ዴሞክራሲያ ቅፅ1 ቁ15
የኢትዮጲያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ያሳተመው አማርኛ መዝገበ ቃላት አብዮት የሚለውን ቃል ‹‹በአንድ ነገር ክስተት ወይም ሂደት ውስጥ ያሉ ቅራኔዎች ተካረው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርሱ የሚፈጠር መሰረታዊ ለውጥ፤ አዲስ ከፍተኛና የተሻለ ነገር፤ ክስተትና ሂደት ወይም አስተሳሰብና እውቀት የሚከሰትበት፡፡›› የሚል ትርጓሜ ይሰጠዋል፡፡
አብዮት በተለያየ የታሪክ ወቅት እንዲሁም በተለያየ ቦታ ተከስቷል፣ እየተከሰተ ነው፤ ወደፊትም ይከሰታል፡፡ ከፈረንሳይ አብዮት እስከ ሩሲያው አቢዮት፤ ከላቲን አሜሪካ ሀገሮች እስከ ሩቅ ምስራቅ እስያ ብሎም እስከ አረቡ አብዮት፤ የአብዮት ንፋስ ያልነፈሰበት የአለማችን ክፍል የለም፡፡ በተለያዩ ቦታዎች የተካሄዱ አብዮቶች እንደወቅቱ እና እንደቦታው የራሳቸው የሆኑ መለያዎች ያሏቸው ይሁን እንጂ ሁሉም የሚጋሯቸው የወል የሆኑ ባህርያትም አሏቸው፡፡ ይኸውም ሁሉም አብዮቶች በጭቆና ማህፀን ውስጥ ተፀንሰው መወለዳቸው ነው፡፡
አብዮቶች ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ አሊያም ኢኮኖሚያዊ መነሾ ምክንያቶች ሊኖሯቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ታሪካዊውን የፈረንሳይ አብዮት ያየን እንደሆነ ሶስቱም መነሾ ምክንያቶች እንደነበሩት እንረዳለን፡፡ የፈረንሳይ ህዝብ በፈላጭ ቆራጭ ንጉሳዊ አስተዳደር ስር ሆኖ መብቶቹን መገፈፉ የአብዮቱ ፖለቲካዊ መነሾ ሲሆን፤ በፈረንሳይ ህዝብ መካከል የነበረው የመደብ ልዩነት በተለይም አብዛኛው የፈረንሳይ የህብረተሰብ ክፍል በድህነት የሚማቅቅበት እና መብቱን የተነፈገበት ሶተኛው መደብ ውስጥ መካተቱ የአብዮቱ ማህበራዊ መነሾ ሆኗል፡፡ እንዲሁም ደግሞ በወቅቱ ፈረንሳይ በከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት ውስጥ መገኘቷ እና በዜጎች ላይም ያለው የግብር ጫና ከፍተኛ መሆኑ የአብዮቱ ኢኮኖሚያዊ መነሾ ሆኗል፡፡
አብዮቶች አብዛኛውን ጊዜ በገዢው መደብ በኩል ሳይጠበቅ የሚከሰት ክስተት ነው፡፡ ለዚህም ነው የሩቁ የፈረንሳይ አብዮትም ሆነ የቅርብ ግዜው የአረቡ አለም አብዮት አለምን ያስደነቀው፡፡ አንዳንድ አብዮቶችን ትልልቅ የስለላ ተቋማት(ሲ.አይ.ኤ፤ ኬጂቢ) ሳይቀር ያልጠበቁት ክስተት እንደነበር ታሪክ ያስገነዝበናል(መሀመድ ሬዛን ያስወገደውን የኢራኑን አብዮት ልብ ይሏል)፡፡ ይህ የሚሆንበትን ምክንያት ቲሙር ኩራን የተሰኘው ፀሀፊ ‹‹sparks and praire fires: a theory of unanticipated political revolution›› በተሰኘው ፅሁፉ ላይ በአለማችን ላይ የተከሰቱትን ሶስት ዋና ዋና አብዮቶችን እንደምሳሌ በማንሳት ህዝብ የተቃውሞው ወገን እስኪጠናከር ድረስ በገዢው ወገን ላይ ያለውን ጥላቻ በውስጡ ደብቆ መያዙ አብዛኛውን ግዜ ገዚዎችን እንዲዘናጉ እንደሚያደርጋቸው ገልፆ አብዮቱ አንድ ግዜ ከፈነዳ በኋላ ለማስቆም አስቸጋሪ የሚያደርገውም በህዝብ ዘንድ ስር የሰደደ እና የቆየ ጥላች እና ቅራኔ መኖሩ እንደሆነ ያስረዳል፡፡
ለአብዮት መነሳት ምክንያቱ ከላይ የዘረዘርናቸው ቅራኔዎች(ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ) ቢሆኑም ከእነዚህ ሁሉ ቀድሞ የሚመጣው ግን የህብረተሰቡ የንቃተ ህሊና(enlightenment) ጉዳይ ነው፡፡ በላቲን አሜሪካ የተካሄዱት አብዮቶች ላይ ጥናት ያካሄዱት እንደ ዴቪድ ክሎስ ያሉ ምሁራኖች ለአብዮቱ መነሳት ዋና ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡት የህብረተሰቡ ንቃተ ህሊና መዳበሩን እና በሌሎች ሀገራት የተካሄዱትን አብዮቶች ከራሱ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ጋር ማስተያየት እና ማገናዘብ መቻሉ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
በሀገራችን በኢትዮጲያም ተከስቶ የነበረውን የ66ቱን አብዮት ያየን እንደሆነ በአለም ዙሪያ የነበረው ሁኔታ በወቅቱ የነበሩትን ወጣቶች ላይ ተፅእኖ ማሳደር መቻሉ እና የወጣቱ ንቃተ ህሊና የዳበረ መሆኑ ከነበረው ጭቆና ባሻገር ለአብዮቱ መነሳት አበይት ምክንያት ነበር፡፡
እነዚህን ከላይ የዘረዘርናቸውን የአብዮት መነሾዎች ይዘን የሀገራችን ነባራዊ ሁናቴ ካጤንን በኢኮኖሚው በፖለቲካውም ሆነ በማህበራዊው ዘርፍ ያለው ከፍተኛ የሆነ ምስቅልቅል እና ብሶት ለአብዮቱ መነሳት በቂ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ነገር ግን መረጃ የማግኘት መብቱን የተነፈገው ሰፊው የህብረተሰብ ክፍል መብቱን በማስከበር ዙሪያ ላይ ያለው የንቃተ ህሊና መዳበር በጥያቄ ውስጥ ያለ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡
የቡርኪና ፋሶው የአብዮት ንፋስ በፍጥነት ወደ ቶጎ እና ጋቦን ተዛምቶ አምባገነን መንግስታትን ሲያንቀጠቅጥ ይህንን ጀብዱ የሰማው የኢትዮጲያ ህዝብ ምን ያህል ነው; ሰምቶስ ወስጡን የኮረኮረው እና መንፈሳዊ ቅናት ያደረበት ስንቱ ነው; የሚለው ጉዳይ ያሳስበኛል፡፡
በእኛ ሀገር አብዮት እንዲነሳ ካስፈለገ አብዮቱ መሪ ያሻዋል፡፡ በቡርኪና ፋሶም ሆነ አሁን በቶጎ እና በጋቦን የተነሳው ከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው እየመሩት ያሉት፡፡ በእኛም ሀገር ባለው ተጨባጭ ሁናቴ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች አስተባባሪነት ውጪ በአሁኑ ሰዓት በራሱ የሚፈነዳ አብዮት ይኖራል ብሎ መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ ነገር ግን ተቃዋሚዎች
1ኛ፡- ለህዝብ ወቅታዊ መረጃዎችን በማቀበል እና በመተንተን የህዝብን ንቃተ ህሊና የሚያሳድጉበትን መንገድ መቀየስ ይኖርባቸዋል፡፡
2ኛ፡- በህዝብ ዘንድ ያላቸውን ቅቡልነት በማሳደግ የሚሞትላቸው ድርጅቶች መሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡
Image