በአዲስ አበባ የታክሲዎች የስራ ማቆም አድማ ይደረጋል የሚል ፍራቻ ተከስቷል።
– የወያኔ ልማታዊ ዲሞክራሲ የህዝብን መጉላላት እንደጨመረ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አማረሩ።
– አዳማ ናዝሬት ውጥረቱ የነገሰ ሲሆን ሕዝባዊ ተቃውሞ ይፈነዳል ተብሎ ተፈርቷል።
– ሕዝቡ ለታክሲዎች የስራ ማቆም አድማ በመተባበር ለህግ የበላይነት እና ልእልና እንዲነሳ ተጠይቋል ።
– በአዳማ ናዝሬት የባጃጅ ባለቤቶች ሊያደርጉት የነበረው የስራ ማቆም አድማ አስተላለፉት። – የታክሲ ባለንብረቶች ከትላንትና ጀምረው ቁጣቸውን እየገለጹ ነው።
Minilik Salsawi
በወያኔው መንግስት አዲሱ የልማት ስታራቴጂ በሚል በታክሲዎች እና በሕብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ እንግልት እየደረሰ እንደሆን ነዋሪዎች በመግለጽ ላይ መሆናቸው ታወቀ ። ከትላንትና ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ በከተማው ትራፊኮች እየተካሄዱ ያሉ ድርጊቶች በከፍተኛ ሁኔታ ህዝብን ወደ ተቃውሞ የታክሲ ባለንብረቶችንም ወደ ስራ ማቆም አድማ የሚመራ ነው ሲሉ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የታክሲዎች የስራ ማቆም አድማ ልንጠራ እንችላለን ሲሉ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የታክሲዎች ባለንብረቶች ማህበር አባል የገለጹ ሲሆን የታክሲዎች የስራ ማቆም አድማ ከበፊትም የታሰበበትና በሂደት የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶበት እንደሚካሄድ ሲገልጹ ሕዝቡም ለዚሁ ያለውን ትብብር እንዲገልጽ በማለት ሲናገሩ ሕዝቡ ለታክሲዎች የስራ ማቆም አድማ በመተባበር ለህግ የበላይነት እና ልእልና እንዲነሳ ጠይቀዋል ።
የታክሲዎች የስራ ማቆም አድማ መታየት አለበት በሚለው ሃሳብ የሚስማሙ ሹፌሮች እንዳሉት ከዚህ ቀደም በተለያዩ የከተማዋ ቦታዎች የነበሩት የታክሲ መጫኛዎች እንዲቀሩ የተደረጉ ሲሆን ወደተለያዩ ቦታዎች በመበታተናቸው የህዝቡ እንግልት ከመጨመሩም በላይ ሹፌሮችም ይህንን ተከትሎ በመንገድ ላይ እንዳይጭኑ ከጫኑ ከባድ ቅጣት እየተጣለባቸው ስለሆነ ከልማታዊው የትራፊክ ህግ ጋር ተስማምተው ሊሄዱ እንዳልቻሉ ገልጸዋል። የታክሲ ባለንብረቶችም ይሁኑ ሹፌሮች እና ረዳቶቻቸው በልማታዊው የትራፊክ እኩይ ህግ የተበሳጩ ሲሆን ቁጣቸውን በመግለጽ ወደ ስራ ማቆም አድማ ጥሪ ለማድርግ እያመሩ መሆኑን ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዳማ ከትላንትና ጀምሮ ከፍተኛ ውጥረት እንደተከሰተ ነዋሪዎች ተናግረዋል። ሕዝባዊ ተቃውሞ ይፈነዳል በሚል በነገሰው ውጥረት የባጃጅ ባለንብረቶች ባጃጆቻቸው ወደ ከተማው እንዳይወጡ ይዘዋቸው የነበረ ቢሆንም ፖሊስ ውጥረት እንዳሌለ እና ስራwቸን እንዲጀምሩ ሲያስገዲዳቸው ውሏል።
ስራቸውን እንዲጀምሩ ቢያስገድዳቸውም የባጃጅ ሹፌሮች ስራ ለማቆም ያስነሱት ተቃውሞ በፖሊስ የከሸ መሆኑንም ተያይዞ የመጣው ዜና ይገልጻል። ሹፌሮቹ በመንግስት ትራፊኮች ከፍተኛ የአስተዳደር በደል እና ዘረፋ ይፈጸምብናል በማለት ሲናገሩ የነበረ ሲሆን ከትላንት ጀምረው አዳማን ፖሊሶች በአጥለቅልቀዋታል ሲሉ ምንጮቹ ገልጸዋል።በአዳማ ናዝሬት ከሁለት አመት በፊት በተደረገ የስራ ማቆም አድማ ባጃጆች እና ሹፌሮቻቸው በመንግስት ላይ ተቃውሞ አሰምተው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው ሲሉ ምንጮቹ አስታውስዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዜና በቅርብ ቀናቶች ውስጥ ህዝቡ በንቃት እንዲከታተል እና በአዳማ ናዝሪት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ሁሉ የስራ ማቆም ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ የባጃጅ ሹፌሮች በላኩት ቃላቸው ገልጸዋል።