ጦማርያነና ጋዜጠኞች ፍርድ ቤት ቀረቡ።ችሎቱና 2 ዳኞች ተቀይረዋል።ለህዳር 3 ቀጠሮ ተሰቷል። የዋስትና ጉዳይ ለነገ ተቀጥሯል።
የበፍቃዱ ሃይሉ ወንድም በፎቶ ማንሳት ሙከራ ተይዟል።የዋስትና ጉዳይ ለነገ ተቀጥሯል።
Minilik Salsawi
193 ቀናት ካለምንም ማስረጃ ሃሳባቸውን በነጻነት በመግለጻቸው ብቻ ለእስር የተዳረጉት የዞን ዘጠኝ ጦማርያን እና ሶስት ጋዜጠኞች በዛሬው እለት በልደታ ፍርድ ቤት ተገኝተዋል ። ነጭ በመልበስ ሰላማዊነታቸውን ያሳዩት ጦማርያኑ እና ጋዜጠኞቹ በልደታ ፍርድ ቤት ሲደርሱ ፎቶግራፍ ለማንሳት ሞክሯል የተባለ የጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ ወንድም በወያኔ ፖሊሶች ቁጥጥር ስር ውሏል።
ፍርድ ቤቱ ለህዳር 3 2007 ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን ማህሌት እና ኤዶም ያቀረቡትን የማረሚያ ቤቱ የሚደርስባቸውን በደል በተመለከተ ሃላፊዎቹ ቀርበው እንዲያስረዱ ት እዛዝ ሰቷል።ዛሬ ጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም በልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ለ10ኛ ጊዜ ችሎት የቀረቡት የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ሶስቱ ጋዜጠኞች ለሳምንት (ህዳር 3/2007 ዓ.ም) ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠባቸው፡፡
ፍርድ ቤቱ ዛሬ በጦማርያንና በጋዜጠኞቹ ቀደም ሲል የቀረበውን የክስ ማሻሻያ አቤቱታ መርምሮ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም፣ ምርመራው አላለቀም በሚል ምክንያት አጭር ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በዛሬው ችሎት ላይ ከተሰየሙት ዳኞች መካከል ሁለቱ አዲሶች በመሆናቸው ምክንያት ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱን ጠበቃ አምሃ መኮንን ገልጸዋል፡፡ ዳኞች ብቻ ሳይሆን ችሎት ክፍሉም በመቀየሩ ክፍሉ ጠባብ ነው በሚል፣ የተከሳሽ ቤተሰቦችና ጋዜጠኞች ችሎት መግባት አለመቻላቸውም ታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በነገው ዕለት ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተከሳሾች ዋስትና ጉዳይ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ መያዙን አቶ አምሃ ጨምረው አስረድተዋል፡፡
በተከሳሾች በኩል ደግሞ፣ ሁለቱ ሴት ተከሳሾች (ኤዶም ካሳዬ እና ማህሌት ፋንታሁን) በቃሊቲ ማረሚያ ላይ ያነሱትን የመብት ጥሰት አቤቱታ በተመለከተ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር በቀጣይ ቀጠሮ ድጋሚ ቀርቦ እንዲያስረዳ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ሁለቱ ተከሳሾች በቀን ለ10 ደቂቃ ብቻ ስማቸው ቀድሞ በተመዘገቡ ሰዎች ብቻ እየተጎበኙ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡