«የኤርትራ ጉዳይ የቅኝ ግዛት ችግር ነው የሚለው አመለካከታችን ዳግም መፈተሽ አለበት። የአገዛዝ ችግር እንጂ የቅኝ ግዛት አልነበረም።» ስብሓት ነጋ በቪኦኤ የትግርኛ ፕሮግራም

ስብሓት ነጋና የኤርትራ ጉዳይ
ስብሓት ነጋ በቪኦኤ የትግርኛ ፕሮግራም ላይ የሚከተለውን ብሏል (ግርድፍ ትርጉም ነው፤ ሙሉ ዝግጅቱ ሲቀርብ ወደ አማርኛ እንመልሰው ይሆናል) ፥
«የኤርትራ ጉዳይ የቅኝ ግዛት ችግር ነው የሚለው አመለካከታችን ዳግም መፈተሽ አለበት። የአገዛዝ ችግር እንጂ የቅኝ ግዛት አልነበረም።»
ለምን አሁን???
«የኤርትራ ህዝብ ለነፃነት ከነበረው ጉጉትና ከደረሰበት ግፍ አንፃር፤ ነፃነቱን «በመረጠው መንገድ» መቀዳጀቱ ባያስቆጨንም፤ ችግሩ «የቅኝ ግዛት ችግር» ነበር የሚለው አመለካከታችን መስተካከል ያለበት ይመስለኛል።»
አሁንም በድጋሚ፤ ለምን አሁን???
የኤርትራ ጉዳይ የቅኝ ግዛት ነበር የሚል አመለካከት የህውሓትና የሻዕቢያ ብቻ እንጂ የማንም እንዳልነበር ግልፅ ነው። (የኤርትራ ህዝብ ሳይቀር ከኢትዮጵያ ጋር በአብሮነት መቀጠል እንደሚፈልግ ቀደም ሲል በጥናት የተረጋገጠ መሆኑን በዘውዴ ረታ መፅሃፍ ላይ «የኤርትራ ጉዳይ» ያነበብኩ መሰለኝ። ) ሟች መለስ እስከ ግብአተ መሬቱ ፍፃሜ ድረስ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ተገዢ እንደነበረች ሲያውጅ ኖሯል። ችግራቸው የአስተዳደር እንጂ የቅኝ ተገዢነት አይደለም ያሉ ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል፤ ታስረዋል፤ ተሳደዋል፤ ወዘተ። ችግሩ የቅኝ ግዛት ነው፤ ጥያቄውም የነፃነት ጥያቄ ተብሎ፤ ያለ ህዝበ ውሳኔ መፍትሄ ተሰጥቶበታል። መፍትሄውም ጦስና ግሳንግሱን በሁለቱ ህዝብ መሃል አራግፎ፤ ኤርትራን ህዝብ አልባ ዋሻ አድርጓታል። ስንት ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በነሱ ምክንያት አልቀዋል።
ይሄ የአገሪቱ ብቸኛ «ሉዓላዊ ግለሰብ»፤ ይህ አመለካከታቸው ዛሬ መታረም እንዳለበት የሚነግረን ለምን ይሆን? ምን ተንኮል አስቦ ነው??