በፕሮፓጋንዳ አብዮት ተወጥረን እስከመቼ?
ነገም እኛ ከሕዝብ ጥያቄ እንደማናመልጥ ልናውቅ ግድ ይለናል!!!
Minilik Salsawi
እውነትን ብንውጣት ምናለ? በሃሰት ሕዝብን እያታለልን እስከመቼ እንኖራለን ? እስከመቼ ያልሆነ እንደሆነ ያልተደረገ እንደተደረገ እስከመቼ እየተደበቀ እየተሹለከለከ። የሕዝብን የነጻነት እና የመብት ጥማትን ተገን አድርገን በማይረቡ ወንፊቶች ስር ተሸሽገን የተሸሸግን መስሎን እየታየን ለምን ? የማያዛልቅ ጸሎት …. ባለፉት አመታቶች እኮ እያየን ነው ምንም ውጤት የለም አላየንም አልሰማንም የምንልበት ደረጃ ላይ ነን ያለነው። ታዲያ ምንን እንመን ? ማን እውነትን ይዟል እንበል? በፕሮፓጋንዳ አብዮት ተወጥረን እስከመቼ?
ያሌለ ነገር እንዳለ ያልተሰራ እንደተሰራ አይ አንቺ መሬት !! አዎን ያው እውነትን እንያዝ ለህዝብ ከህዝብ በህዝብ የሆነ ስኬታማ ትግል እናድርግ በማለታችን ምናልባት ልንሰደብ ልንዋረድ ልንዘረጥጥ እንችላለን ለምን በፕሮፓጋንዳ የሞሉን እውነትን መዋጥ ስለሚከብዳቸው መግቢያ ሲጠፋ ግለሰቦች ላይ ይዘምታሉ። ግለሰቦችን ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት ውጪ ይሳደባሉ ያዋርዳሉ ይወነጅላሉ። ትላንትና ምን አሉ? ዛሬ ምን አሉ? ነገ ምን ይላሉ ? በትግል ላይ ነን እያሉን መስመሩ አያዋጣም ያሉ ሰዎችንስ እንዴት አስዋጡ ? እያንዳንዱን መለስ ቀለስ እያልን በፖለቲካ እና አገራዊ ህዝባዊ ምንዛሬ ላይ ካጤነው መጭውን ጊዜ ለመወሰን አንገታችንን የሚያስደፋን ነገር አፍንጫችን ስር ይወተፋል።
በግልጽ መውጣት ሲገባን ለሌላ የተለመደ ፕሮፓጋንዳ መስመር እና ስልት ቀይረን ስንመጣ ቀን ጠብቆ ከህዝብ ጥያቄ ማምለጥ እንደማይቻል ለመናገር እንደፍራለን። አለማቀፍ ድርጅቶች እና ሚዲያዎች የእሚነግሩን ሌላ መሬት ላይ ያለው ሌላ ፕሮፓጋንዳው የሚነግረን ሌላ ታዲያ የነጻነት ጥማታችንን እንዴት እንወጣ። ያለን የመጨረሻ እድል ሕዝቡ ሆ ብሎ አደባባይ እንዲወጣ ከማድረግ ውጪ አለ አለን በሚሉት ላይ መተማመኑ እንደማያዋጣ ሊሰመርበት ይገባል እኔም እንደ ዜግነቴ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል አውቅልሃልሁ የሚል የህሰት ፕሮፓጋንዳ አንገሽግሾናል ። ነጻነት በጃችን ነውና ራሳችንን ነጻ እናውጣ ።