የአገራችን የፖለቲካ ሰማይ ያረገዘው ጥላቻ፣ጽንፈኝነትና ቂም በቀል መጽዳት አለበት።

Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ)

እርስ በርስ መካሰስ፣ መጠላላት፣ መበላላት፣ የሌላውን ታሪክ ማጉደፍ፣ የሌሎችን ሰብዓዊ ክብር መንካትና ማዋረድ እንደ ጀብዱና አሸናፊነት በሚቆጠርበት፣ ጥላቻ፣ ጽንፈኝነትና መለያየት የአገራችን ፖለቲካ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞቻችን ልዩ መለያ ሆኖአል፡፡

ኢትዮጵያን ወደ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ያሻግራል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ተማሪ፣ ገበሬ፣ ወታደር፣ ምሑር፣ወዘተ በነቂስ ሆ ብሎ የተሳተፈበት አብዮት በአገራችን ላይ ጥሎት ያለፈው ጠባሳ እጅግ ከባድና መራር ነበር፡፡ እስከ አሁንም ድረስ በዚያን ዘመን ትውልድ አባላት ለውጥ አራማጆች ላይ የፈጠረው የልዩነት ገደል፣ ጥላቻና መራርነት ሳይናድ እዚህ ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡

የትናንት ትውልድ አባል የሆኑት አብዛኛው የዛሬዎቹ ፖለቲከኞቻችን የብዙ ወገኖቻቸውን ክቡር ሕይወት የቀጠፈውንና አገሪቷን ወደ አሰቃቂ እልቂትና ፍጅት የመራውን ፖለቲካዊ ቀውስ አስመልክቶ ይቅር ለመባባልና እርቅ ለማውረድ ከወሬ ባለፈ ተግባራዊ የሆነ እንቅስቃሴ ለማድረግ አልደፈሩም፡፡ ዛሬም ቢሆን ትናንት በአገራችን ላይ ለተከሰተው ሰብዓዊ እልቂት፣ ኢኮኖሚያዊ ውድመትና ማኅበራዊ ምስቅልቅል አንዱ አንዱን ተጠያቂ የማድረግ አባዜ ነው ጎልቶ የሚታየው፡፡

የፍቅርን፣ የሰላምንና የዕርቅን ባንዲራ ከፍ አድርጎ በማውለብለብ የኢትዮጵያችንን የዘመናት ፖለቲካዊ ስብራቷንና እያመረቀዘ ያስቸገራትን የቂም በቀልና የጥላቻ ቁስሏ ይሽር ዘንድ የፍቅርንና የይቅርታን ዘይት የሚያፈስላት እንደ ማንዴላ ያለ ብሔራዊ የፍቅር ጀግና ለማግኘት ገና አልታደለችም፡፡ እናም ያልሻረ ቁስሏን፣ ያልተፈወሰ ሕመሟንና ያልተጠገነ ስብሯቷን ይዛ በማንከስ እናት ኢትዮጵያ በእኛም ዘመን ወንድም ወንድሙን ትናንት በተፈጸመ ታሪክ ለበቀልና ለሞት የሚፈላለጉባት ምድር ሆና ዘልቃለች፡፡

በጥላቻ፣ በቂም በቀለኝነትና በጽንፈኝነት እግረ ሙቅ ውስጥ ለወደቀው የአገራችን ፖለቲካ መፍትሔው ከልብ የሆነና ከፍቅር የመነጨ ብሔራዊ እርቅ፣ መግባባትና በግልጽ መነጋገር እንደሆነ በግሌ በእጅጉ አምናለሁ፡፡ ይህን ጹሑፍ ለመጻፍ የተነሳሁበት ዋነኛው ምክንያትም በገዢው ፓርቲም ሆነ በተቃዋሚ ፖለቲከኞቻችን መካከል ተቀራርቦ በመግባባት መነጋገር ይቻል ዘንድ፣የአንድ አገር ልጆች በሐሳብ ልዩነትና ፖለቲካዊ አመለካከት ምክንያት በጠላትነት የምንፈራረጅበት የጨለማው ታሪክ ዘመናችን ያበቃ ዘንድ በመመኘት ነው፡፡

አሁንም ድረስ የአገራችን ፖለቲካ በጥላቻና በጽንፈኝት ሥር ወድቆ የሚማቅቅ መሆኑን ከበቂ በላይ የሆኑ ማሰረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዕርቅና በፍቅር መንገድ ሊነሱ ቀና ቀና ያሉትንም ባለ ራዕዮች ከጠላቶቻቸው ቀድመው ወዳጆቻቸው ነን የሚሉት ራዕያቸውን አምክነው፣ ተስፋቸውን አድብዝዘው ከትግሉ መድረክ ገፍተዋቸዋል፡፡ እናም ዛሬም ድረስ የአገራችን የፖለቲካ ሰማይ ካረገዘው ከጥላቻ፣ ከጽንፈኝነትና ከቂም በቀል የጸዳ ለማድረግ ገና ከፊታችን እልህ አስጨራሽ የሆነ ረጅም ጉዞ የሚቀረን ይመስለኛል፡፡