የአዲሱ የአዲስ አበባ ኤርፖርት ተርሚናል የዲዛይን ስራ ተጠናቀቀ

airport new design.jpgአዲስ አበባ ፣ መጋቢት 27 ፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) ከሁለት ወራት በኋላ ግንባታው የሚጀመረው አዲሱ የኤርፖርት ተርሚናል የዲዛይን ስራ ተጠናቀቀ።

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት እንዳለው በ225 ሚሊዮን ዶላር የሚገነባው ተርሚናል 22 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል ነው።

የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድም ተክሉ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ለተርሚናሉ ግንባታ የሚውለው ገንዘብ ከቻይናው ኤግዚም ባንክ በብድር የተገኘ ነው።

የብድር ስምምነቱ በትላንትናው ዕለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀ ሲሆን የተርሚናሉ የዲዛይን ስራ ሲ.ፒ.ጂ በተሰኘ የሲንጋፖር ኩባንያ ተዘጋጅቶ ዛሬ ለድርጅቱ ቀርቧል።

ግዙፍና ዘመናዊ ነው የተባለለት የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል የእንግዳ ሳሎን፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽና ኢንተርኔት ካፌን በውስጡ አካቷል።

በኤርፖርቱ በስተምስራቅ በኩል የሚያርፈው ይህ ዘመናዊ ተርሚናል ከሁለት ወራት በኋላ በቻይናው ሲ.ሲ.ሲ.ሲ ኩባንያ የግንባታ ስራው ይጀመራል።

አቶ ወንድም ድርጅቱ ከዚሁ ፕሮጀክት ጋር የሚያያዝ የአውሮፕላን ማረፊያ ሜዳ የማስፋፊያ ስራም አማከናወኑንና ይህም ቀድሞ 19 አውሮፕላኖችን ብቻ ይይዝ የነበረው የማረፊያ ሜዳ 45 ግዙፍ አውሮፕላኖችን እንዲያስተናግድ አስችሎታል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።