“አንድ ግደል፤ አሥር ሺህዎችን አሸብር” የወያኔ መፈክር ( by Lemlem Kebede)

የወያኔ መንግሥት አክራሪነትን እና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ሽፋን ከተከተለው የኢትዮዽያን ህዝብ የማሸበር ዒላማ ያደረገ ፖሊሲና ይህን ፖሊሲ ለማስፈፀም ከሚሠራቸው በርካታ ፀረ ህዝብ ስራዎች አንድ ነገር መናገር ይቻላል፡፡ ገዢው ፓርቲ ኢትዮጵያውያን ወደ ሁከትና ብጥብጥ፣ ብሎም ወደ ለስልጣኑ የሚያሰጋው ከሆነ እስከ መበታተን የሚደርስ እንደ እስሥት እራሱን እየቀያየረ የዘረኛ መርዙን ለ22 ዓመት ሲረጭብት ኖርዋል፡፡ ይህ የፀረ ሽብር አዋጅ ( ነፃነቱንና መብቱን የሚጠይቅ የሚታፈንበት ህግ) በህዝበ ላይ እንዲፈጠር በማድረግና በማስፈራራት “የዓለም አቀፉ ፀረ ሽብር ጦርነት” አጋርነቱን ማደስ፣ በዚህም ከአሜሪካና ከምዕራብ አውሮፓ አገራት የማያቋርጥ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የዲፕሎማሲ ድጋፎችን ማግኘት ይፈልጋል፡፡ ያለፉት 22 ዓመታት ታሪክ የሚያሳየው፣ ገዥው ህወሓት/ኢህአዴግ ስለመብት መከበር የቆሙትን ሁሉ በየተራ ለማንበርከክ በፈጠራ ክሰ መወንጀል፣ ማሰርና ማሳደድ ብሎም መግደል ዋነኛ ስልቶቹ ሆነው መቆየታቸውን ነው። ይህንን የጥፋት አካሄድ ህጋዊ ለማስመሰልም ሰፊ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ሥራ መስራቱ የተለመደ ነው። በአገር ውስጥ ለሚወስዳቸው ዴሞክራሲን የማቀጨጭ፣ነፃነትን የመገደብ፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ያለመቻል ችግሮች፣ በአጠቃላይም በአገሪቱ ውስጥ የሕግ የበላይነት አለመኖርን “በፀረ ሽብር ትግሉ አስገዳጅነት የተፈጠሩ” አስመስሎ ለማቅረብ ይፈልጋል፡፡ የሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች እና የነፃነት ገደቦችን ሁሉ “የህዝብን ሰላም ለመጠበቅ ሲባል በህጋዊ መንገድ የተጣሉ ገደቦች” የማስመሰል ፍላጎት እንዳለው ባለፉት ዓመታት ከወሰዳቸው ፖለቲካዊ እርምጃዎች እና እርምጃዎቹን ተገቢ ለማድረግ ካቀረባቸው ምክንያቶች መገንዘብ ይቻላል፡፡
… ምንም እንኳ ኢህአዴግ ኢትዮጵያውያን ያነሷቸውን የነፃነት ጥያቄዎች ለማፈን የ“ሽብርተኝነት” አቧራ ለማስነሳት እጅግ ቢደክምም፣ ራሱ መንግሥት ለህጋዊ እና ሰላማዊ የህዝቦች የመብት ጥያቄ ምላሽ እየሰጠ ያለው የ“ሽብርተኝነት” ተግባር በመፈፀምነው፡፡ በዚህም መሠረት በመጀመርያ የሞከረው፣ “አንድ ግደል፤ አሥር ሺህዎችን አሸብር” የሚለውን የቻይኖች አባባል ተግባራዊ ማድረግ ነበር፡፡
ኢትዮጵያውያን ወያኔ ሊገባው በማይችል ጠንካራ የአንድነት ገመድ ተሳስረዋል ፡፡ በወንጀለኛ የፌደራል ፖሊሶች የሚተኮሱ ጥይቶችና ከብረት የተሰሩ የግፈኛ በትሮች ጭቁኑን ህዝብ ለበለጠ ሰላማዊ ትግልና መስዋዕትነት ያዘጋጁታል እንጂ ከቶውኑም ከትግሉ አያሸሹትም፡፡

ከጭቆና በላይ ሽብር የለም። ምክንያቱም ጭቆና ማስፈራራት፣ ግድያ ……… ምናምን (ሰው ፈርቶና ተሸብሮ ሳይቃወም እንዲገዛ ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶች የሽብር ተግባራት ናቸው)። “ሽብር” ማለት’ኮ ኣንድ ኣካል ራሱ የሚፈልገውን ተግባር በሌሎች ሃይል በመጠቀም ወይ በማስፈራራት ለመጫን ሲሞክር ነው። ሌሎችን እያስፈራራ ያለው ማነው?ማነው ንፁሃን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን በየመንገዱ የገደለ ? ኣሸባሪ ማነው? ማነው ሰለማዊ ዜጎችን በማፈን እያሸበረ ያለው?

ወያኔ፣ ዓመታትን ባሰቆጠረው ግፍና የመብት ረገጣው፣ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በስነልቦና ሽብር አፍኖ፣ አንዱን የህብረተሰብ ክፍል በሌላው ላይ እንዲነሳ በማድረግ፣ የከፋፍለህ ግዛ መንገዱን በማጠናከር፣ የአምባገነን የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም እየጣረ መሆኑ ግልጥ ነው። ዛሬ በሀገራችን ውሰጥ፣ በወያኔ መብቱ ያልተረገጠ፣ የጥቃቱ ስለባ ያልሆነ የህብረተሰብ ክፍልን ማግኘት አይቻልም። ይህን መጠን የለሽ ረገጣ ለማስቆምና ዴሞክራሲያዊና ስብዓዊ መብቶችን ለማስከበር የሚቻለው ደግሞ ሁሉም ዜጋ፣ በግልም ሆነ በጋራ፣ ለመብቱ መከበር “እምቢ አልገዛም” ብሎ ሲነሳ ብቻ ነው።
by Lemlem Kebede from Oslo Norway

[/imgwrap][/imgwrap]