ቀዳማዊ ሃይለስላሴ (ተፈሪ መኮንን) :-የ“የንጉሡ ገመና” … ንጉሡ ወሬ ይወዳሉ ስስታም ;ታማኞችን አይወዱም ;አይጾሙም ;ሴሰኛ ;ተደባዳቢ… ነበሩ::

–ታላቁን ገመና የደበቀው የ“የንጉሡ ገመና”
የመጽሐፉ ርዕስ – የንጉሡ ገመና
የገጽ ብዛት – የ172
የታተመበት ዘመን – 2006 ዓ.ም
የሽፋን ዋጋ – ብር 49.75
አሳታሚ – ግርማ ለማ
የመጽሐፉ ይዘት ከታሪክ ዘውግ የሚመደብ ሆኖ አሳታሚው ሁለት ምንጮችን ተጠቅመው ነው ያሳተሙት፤ እነሱም ለ14 ዓመታት በንጉሥ አሽከርነት ያገለገሉት የአቶ ሥዩም ጣሰው መንዜው የግል ማስታወሻና የልዩ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጽ/ቤት ቀይ ሽብርን አስመልክቶ ያሳተመው “ደም ያዘለ ዶሴ” የተሰኙ መፃሕፍት ናቸው፡፡
በተለይ አቶ ሥዩም ከልጅነታቸው ጀምረው በቤተመንግሥት ያደጉና ለድፍን 14 ዓመታት በንጉሡ አሽከርነትና አልባሽነት ያገለገሉ በመሆናቸው የንጉሠ ነገሥቱን ጓዳ ጐድጓዳ፤ የአሽከሮችን፣ የደንገጡሮችንና የወቅቱን ባለሥልጣናት ጠቅላላ ሁኔታ የማየት ብቻ ሳይሆን የማወቅ ዕድሉ ስለነበራቸው ማስታወሻቸው ተአማኒነት ይኖረዋል። አቶ ሥዩም ንጉሠ ነገሥቱ ሥልጣናቸውን ተቀምተው መጀመሪያ በቤተመንግሥታቸው ቀጥሎም በ4ኛ ክፍለ ጦር እስረኛ እስከሆኑበት ድረስ ንጉሡን በታማኝነት አገልግለዋል፤ በደርግ ዘመን እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ኖረው ኢህአዴግ ሲገባ በቁጥጥር ስር መዋላቸውና ከጠባቂዎች አምልጠው ራሳቸውን ማጥፋታቸው ይነገራል፡፡ ወደ መጽሐፉ እንመለስ፡፡
አሳታሚው ግርማ ለማ፤ በምስጋና ገጹ ላይ የጽሑፉን ዋና ቅጅ (ኦሪጅናል) የሰጠው “በያን ናስር” የተባለ ሰው መሆኑን ጠቅሷል፤ ግን በያን የሥዩምን ጽሑፍ እንዴት እንዳገኘው ወይም የሥዩም ወኪል ይሁን፤ የገለጠልን ነገር የለም፤ የተገኘበት መንገድ ቢጠቀስ በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ምክንያቱም ሥዩም የሞተው በድንገት ነው፤ የተያዘውም ሳያስበው ቤቱ በታጣቂዎች ተከቦ ነው፡፡ ስለዚህ ሃሳባችንን ወደአልተፈለገ ጥርጣሬ እንዳያመራን ግርማ ረቂቁን እንዴት እንዳገኘው ቢገልጥልን መልካም ነበር፡፡ የተጻፈልን ታሪክ ነዋ! ታሪክ ያለአስተማማኝ ማስረጃ ሊታሰብም ሊጻፍም እጅግ ይከብዳል፡፡
መጽሐፉ የምስጋናና የመግቢያ ገጾችን ሳይጨምር፣ በዘጠኝ ምዕራፎች የተዋቀረ ነው፡፡ ስምንቱ ከስዩም ጣሰው ማስታወሻ የተወሰዱ ሲሆን ዘጠነኛው ምዕራፍ “ደም ያዘለ ዶሴ” ከተባለው መጽሐፍ የተገለበጠ ነው፡፡
የመጽሐፉ ጠንካራ ጐኖች
መጽሐፉ በንጉሡ ጓዳና ቢሮ ውስጥ ስለነበረው እውነት የገለጠልን በመሆኑ፣ የንጉሠ ነገሥቱን አጠቃላይ ሰብዕና ለሚያጠና ሰው ትልቅ የታሪክ ጥቅም ይኖረዋል፡፡ ንጉሡ በካህናትና ባለሥልጣናት ዘንድ ተፈርተው ይከበሩ ስለነበር፣ ድምሩ ህዝብም አባቱን እየተወ “ኃይለሥላሴ ይሙት” በማለት በስማቸው ይምልና ይገዘት ነበር፡፡ ግን እንደ ሥዩም ጣሰው ጓዳቸውን ገብቶ የማየት ዕድል ቢገጥመው ኖሮ ምን ያህል ሲታለል እንደኖረ ይገባውና ከልቡ ይቆጭ ነበር ያሰኛል፡፡ ለማንኛውም የመጽሐፉን ጠንካራ ጐኖች በአምስት ከፍያቸዋለሁ፡፡
ገመና አንድ
ንጉሡ ተደባዳቢ ነበሩ
ንጉሡ አሽከሮቻቸውን ይደበድቡ ነበር፤ “…የፀጉር ቅባት ፓንተን ሳቀርብላቸው ቀና አሉ፤ አዩኝ፡፡ አሰቡ አሰቡና ‘ማታ ማነው ፍራፍሬውን የደገሰው’ ብለው ጠየቁኝ፡፡ እኔም ራሴ መሆኔን ነገርኋቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ብድግ አሉና ተያያዙኝ፡፡ እስከሚደክማቸው ድረስ ደበደቡኝና ቁጭ ብለው ፀጉራቸውን አበጠሩ፡፡ ክራባታቸውን አሰሩና ተነሱ። ልብሳቸውን ለብሰው ሲጨርሱ ጠሩኝ፡፡ እኔም አቀርቅሬ ተጠጋሁ፡፡ አስጐነበሱና እስከሚበቃቸው ወገሩኝና እየተሳደቡ ወደ ቁርሳቸው ሄዱ” (ገፅ 11-12)
ይህን አይነት እርግጫና ጥፊ ለሥዩም አዲስ አልነበረም፤ በየጊዜው ይገረፋል፤ የስድብ ውርጅብኝ ይዘንብበታል፡፡ ሁለት ቀን ብቻ ከተገረፈ በኋላ ብር እንዲሰጠው አድርገዋል፤ ይህ አንድም ምሥጢራቸው እንዳይወጣ ማባባያ ነው፡፡ አለዚያም ካሣ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሆኖም የሥዩም (አሽከርና የታሪኩ ፀሐፊ መሆኑን አንዘንጋ) ትልቁ ፈተና ከንጉሡ ዱላ ይልቅ የሴት አሽከሮች በእሱ ላይ ማደምና ከባለሥልጣናት ጥርስ ውስጥ ማስገባት ነበር ትልቁ ፈተና የሆነው። ለዚያ ሁሉ እርግጫ፣ ጥፊና ዱላ ሰበቡ ንጉሡ የገረዶችንና የአሽከሮችን ወሬ ስለሚሰሙ ነው፡፡ (ገፅ 14)
ንጉሡ ወሬ ይወዳሉ፤ የሆነ ያልሆነን ሁሉ የሚቀላምድላቸውን ሰው ያስጠሩትና ምንም ሳያጣሩ የተወራበትን ሰው ራሳቸው ይገርፋሉ፤ ካስፈለገም ግዞት ይልካሉ፡፡ (ገፅ 21 እና 24)
ገመና ሁለት
ንጉሡ ሴሰኛ ነበሩ
ንጉሡ ሴት በጣም አብዝተው ይወዱ ነበር፤ በዚህ የተነሳ ከጽዳት ሠራተኞች፤ ከአበሻ ወጥ ቤቶች፣ ከእንጀራ ጋጋሪዎች፣ ከቅንጬ ቤቶች፣ ከሴተኛ አዳሪዎች፣ ከሆስተስና ከባለ ትዳር ሴቶች ጋር ይቀብጡ ነበር፡፡ “ሴቶቹ አብዛኛውን ጊዜ የሚገቡት ቀን ከምሳ መልስ እረፍት በሚያደርጉበት ጊዜ ከ8-10፡30 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ጃንሆይ ገብተው ከተኙ በኋላ ትንሽ ቆይተው ደወል ይደውላሉ፡፡ በዚያ ጊዜ በዚህ ነገር የተለየ ባለሟል የሆኑ አሽከሮች በተራቸው ይገቡና “ዕገሊትን ጥራ” ሲባል ይጠራል፡፡ ምን አልባት እርሱ ከተጠራችው ሴት ጋር ሽርክና ከሌለው ወይም ከምትወስደው ገንዘብ በብዛት ካላካፈለችው “እርሷ አሁን የለችም” በማለት የርሱ ሽርክ በየጊዜው ብዙ ገንዘብ የምትሰጠውን ሴት “ዕገሊት አለች፤ እርሷ ከሥራዋ ላይ አትጠፋም” በማለት ይቀላምድና ይጠራል፡፡ ሲገቡና ሲወጡ የተለየ ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ ነገር ግን ሴቶቹ በሚያሳዩት መለዋወጥ የተቀረው ሰው እዚያ ቦታ እንደደረሰች ይገባዋል” (ገፅ 51)
“ቢሮ የሚደረገው ደሞ ሌላ ነው፤ ቢሮ በሚሠሩበት ጊዜ ረፈድ ሲልና አንዳንድ ባለሥልጣኖችን ካነጋገሩ በኋላ ገለል ብለው ቢሮ አጠገብ ካለው መኝታ ቤት ጐራ ይላሉ፡፡ ከዚያም በዚያ አካባቢ ከሚሠሩት ሴቶች ውስጥ የፈለጓትን አስጠርተው ትንሽ ከተጨዋወቱ በኋላ ወደ ቢሮአቸው ይገባሉ፡፡ …ሆስቴሶችንና ሌሎችን ደግሞ እምድር ቤት ካለው ቢሮ ነው የሚያገኙአቸው” (ገፅ 51)
ይህ ሁሉ ሲሆን እንደየሴቶቹ የንቃት መጠን ዛቅ ያለ ገንዘብ ይከፈላቸዋል፤ ከሥራ ቤት፣ እንጀራ ቤትና ወጥ ቤት ለሚመጡት ሴቶች የሚከፈላቸው አነስተኛ ገንዘብ ሲሆን ለጽዳት ሠራተኞችና ለሌሎች ሴቶች ግን ከ70-80 ሺህ ብር ይከፍሉ ነበር፡፡ ሴቶቹ ደግሞ ወደ ንጉሡ ላቀረባቸው ሰው (ደላላው) ከ5-10 ሺህ ብር ቀረጥ የመክፈል ግዴታ ነበረባቸው። በዚህ የተነሳ ከንጉሡ ጋር የተገናኙ ሴቶች ሁሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቆንጆ ቪላና ዘመናዊ መኪና ይገዙ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ እንዲያውም ፖለቲካዊ ሥልጣኑን ተቆጣጥረው የፈለጉትን ያስሾሙ ያስሸልሙ፤ የጠሉትን ደግሞ ያሰቃዩት ነበር (ገፅ 51)
አንዳንድ የንጉሡ ውሽሞች በጣም ቀበጦች ስለነበሩ በመንግሥት ወጭ፣ አስተርጓሚ ጭምር ተመድቦላቸው ለሽርሽር ፈረንጅ አገር ይሄዱ ነበር። በጣም የሚያሳዝነው ግን ንጉሡ የባለቤታቸውን የዕቴጌ መነን አስፋውን ጌጣጌጥ ሳይቀር ለውሽሞቻቸው መስጠታቸው ነው፡፡ ለአንዳንድ ውሽሞቻቸውም ቋሚ ደሞዝ ተቆርጦላቸው የቤተ መንግሥት አሽከሮች በየወሩ እቤታቸው ድረስ እየሄዱ ይከፍሉ ነበር፡፡ (ገፅ 56)
ይህ ድርጊት ያንገበገበው ሥዩም “ኢትዮጵያ በተለይ ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ ስትገዛ የኖረችው በንጉሠ ነገሥቱ ሳይሆን በእልፍኝ አስከልካዮች፣ በጥቂት የእልፍኝ አሽከሮችና በገረዶች ነበር፡፡ …ቤተመንግሥቱ ቤተመንግሥት መሆኑ ቀርቶ ፍጹም የሰይጣን ቤት ሆኖ ነበረ” ሲል ትዝብቱን አስፍሯል። (ገፅ 20)
ገመና ሶስት
ንጉሡ አይጾሙም ነበር
ንጉሡ አክሱም ጽዮንንና ሌሎች አብያተ ክርስቲያናትን ስለአሠሩ ካህናት ያወድሷቸዋል፤ ይሰግዱላቸዋል፡፡ “አቤቱ ፍርድን ለንጉሣችን ስጠው” እያሉም ዘወትር ይፀልያሉ፤ እንደ ጻድቃንና ሰማዕታት በመቁጠርም መልክአ ኃይለሥላሴ ደርሰውላቸው ነበር፡፡ ሆኖም ንጉሡ የክርስቲያንን ህግና ሥርዓት በመጣስ፣ አርብና ረቡዕን እንዲሁም ሌሎች አጽዋማትን አይጾሙም ነበር፡፡ (ገጽ 25 እና 34)
ገመና አራት
ንጉሡ ጠንካራ ሰራተኞችንና ታማኞችን አይወዱም ነበር
“ግርማዊነታቸው የሚወዱት ሰው ፈጣን፣ አጭበርባሪ፣ አሳባቂ፣ በዕውቀት ያልበሰለ፣ እርሳቸውን አምታቶ የሚያታልላቸውን ሰው በጣም ይወዱታል፡፡ የጥቅም ተካፋዮቻቸው በሙሉ በዕውቀት ያልበሰሉ፣ የሰውን መብት በፍጹም ያልተረዱ፣ ሰውን ሸጠው ለመክበር ብቻ ጽኑዕ ዓላማ ያላቸው፣ ለኔ እንጂ ለኛ የሚል መንፈስ ፈጽሞ የሌላቸው ጨካኞች፣ ሰው በችግር ሲሰቃይ ሲያዩ ከማዘን ይልቅ መደሰትን የሚመርጡ ከንቱዎች ናቸው፡፡
“ግርማዊነታቸው አጥብቀው የሚጠሉት ሰው እውነትን በጣም አድርጐ የሚወድ፣ ዘወትር የሚከራከራቸው፣ በእውነት ፍጹም በሆነ መንገድ የሚወዳቸው፣ ሲዋሹ የሚያስተባብላቸው፣ የሚታሙበትን ነገር እንዲተው የሚነግራቸው፣ የማይንቀዠቀዥ፣ አዋቂ ሰው በፍጹም አይወዱም” (ገፅ 31) ይለናል፤ ሥዩም በ14 ዓመት የአሽከርነት ዘመኑ የታዘበውን ሲያካፍለን፡፡
ገመና አምስት
ንጉሡ ስስታም ነበሩ
ንጉሠ ነገሥቱ ኢትዮጵያን የምታክል ታላቅ አገርና እጅግ ብዙ ህዝብ የመግዛታቸውን ያህል ስስታቸውም ያን ያህል አሳፋሪ እንደነበር በመጽሐፉ ላይ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል፡፡ በልጅነት ዘመናችን የምናውቃቸው ንጉሥ፤ በየቦታው ሲዘዋወሩ ብር እንደጥሬ እየበተኑ የሚሄዱ መሆናቸውን ነበር፡፡
ሥዩም የሚያውቀውን እውነት ሲነግረን ግን ስስታቸው በጣም የወረደና ለማመን የሚያስቸግር ሆኖ እናገኘዋለን “…በተለይ ከኬኩ ትንሽ በቄንጠኛ አኳኋን ቆርሰው ከበሉ በኋላ በምልክት አድርገው በጥንቃቄ እንዲቀመጥ ይናገራሉ፡፡ በማግስቱ ሲመጣ ትንሽ ለውጥ ከታየበት “ማነው የተጫወተበት” በማለት ማሰቃየት ነው፡፡ አንድ ኬክ ከሶስት እስከ አምስት ቀን ድረስ እየተመላለሰ ይቀርባል፡፡ ለምሳሌ ሐሙስ ቀን ተጀምሮ እንደሆነና ቅዳሜ ደብረዘይት ቢሄዱ አብሮ ይሄዳል፤ ማሩንም በጣም አድርገው ይቆጣጠራሉ፡፡ ከማስቀመጫው ብልቃጥ ውስጥ ትንሽ ጐድሎ ያገኙት እንደሆነ “እንደፈለጋችሁ ትጫወቱበታላችሁ” ብለው መለብለብ ነው” (ገፅ 33) ሲል ያየውን ትዝብት ያካፍለናል፡፡
ከዚህ ሌላ መኝታ ቤታቸው በስጦታ ዕቃዎች፣ በቸኮላት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ስለሚሞላ ዕቃ ቤት ይመስል ነበር፤ እንዲያውም አትክልትና ፍራፍሬው፤ እንዲሁም ቸኮላትና ኬኩ እየተበላሸ የመኝታ ቤታቸውን ሽታ ያበላሸው ነበር፡፡ (47፣ 116፣ 117)
ከመጽሐፉ ውስጥ በጣም የገረመኝ ቢኖር (ገፅ 149) ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ ከ1963 ዓ.ም ጀምሮ ለንጉሡ ልክ “ልዩ ካቢኔ” ይባል እንደነበረው የስለላ ተቋም፣ በየቀኑ ለንጉሡ ደብዳቤ ይልኩ የነበሩ መሆናቸው ነው፤ ለመሆኑ ቀኛዝማች ተሥፋን ከንጉሡ ጋር ያውም በየቀኑ የሚያገናኛቸው ምን ብርቱ ምሥጢር ነበር ይሆን እንድል አድርጐኛል፡፡
የመጽሐፉ ድክመት
መጽሐፉ ከላይ በመጠኑም ቢሆን የነካካኋቸውን ጉዳዮች የዓይን ዕማኙን ሥዩም ጣሰውን ዋቢ አድርጐ የመቅረቡን ያህል ሌላ ድክመት እንዳለበትም መዘንጋት አያሻም፡፡
አሳታሚው በመግቢያው ላይ “አሽከር ሥዩም (አፈሩን ገለባ ያድርግለትና) በሰነዱ ውስጥ ጽሑፉን ለንባብ ሳያበቃው እንዳይሞት አምላኩን የተማጸነበት ፀሎት አለ” ብሎናል፡፡ ግን ይህንን ከሰነዱ ውስጥ አናገኘውም፡፡ ይህ የሚያሳየን የሥዩም ሰነድ የተነካካ ወይም የተቆራረጠ ፍሬ ነገር አለው ማለት ነው፤ ይህ ከሆነ ደግሞ ፍጹም ስህተት ነው፡፡ አንድ አካል ሲቆረጥ ሌላውን ምሉዕ እንደማያደርገው ሁሉ የሥዩም ጽሑፍም የቋንቋ አርትኦት ብቻ ተደርጐለት መታተም ነበረበት፡፡
ሌላው ከወሲብ፣ ከንዋይና ከሃይማኖታዊ ገመናቸው ይልቅ የንጉሱ ፖለቲካዊ ገመና ቢታከል ኖሮ ጽሑፉን ተወዳጅ ያደርገው ነበር፤ ሰዎችን በምሥጢር መግደልና ማስገደል፣ በፍርድ አካባቢ የነበረው ሸር ሁሉ ሊገለጽ በተገባ ነበር፡፡ ይህን አይነቱን ታላቅ ገመና ሥዩም ሳይነካካው አልቀረም፤ ግን በመጽሐፉ ላይ አናገኘውም፡፡ ይህ ደግሞ ታላቁንና ለ44 ዓመታት የኖሩበትን ገመና ምስጢር አድርጐብናል፡፡ ከገጽ 141 ጀምሮ እስከ ገጽ 172 ያለውና “ደም ያዘለ ዶሴ” ከሚለው መጽሐፍ እንዳለ ተገልብጦ የቀረበልንም የመጽሐፉ ትልቅ ድክመት ነው፡፡ እንደ ትርፍ አንጀት የተለጠፈውን 32 ገጽ ከዋናው መጽሐፍ “ደም ያዘለ ዶሴ” ላይ አንብበነዋል፤ እዚህ ላይ መደረቱ ለምን አስፈለገ?
addis admass newspaper