በጎንደር የቅማንት ብሔረሰብ አመራርና አባላት እየታደኑ በመታሰር ላይ ናቸው።

ከ50 በላይ የሚሆኑ የቅማንት ብሔረሰብ አመራርና አባላት መታሰራቸው ተጠቆመ::
ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት እያቀረበ ባለው የማንነትና የራስ አስተዳዳርነት ጥያቄ ምክንያት፣ ከ50 በላይ የሚሆኑ አባላትና አመራሮቹ መታሰራቸውን የቅማንት ብሔረሰብ አመራር ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
የካቲት 9 ቀን 2006 ዓ.ም. ‹‹ቅማንት የሚባል ሕዝብ የለም ያለ አካል ባይኖርም የራስ አስተዳደር ግን ሊፈቀድ አይችልም›› በሚል የክልሉ መንግሥት ተወካዮች ምክር ቤት ነሐሴ 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ያስተላለፈውን ውሳኔ በመቃወም፣ በጎንደር ከተማ እስከ 300 ሺሕ የሚደርሱ ተወላጆች በተገኙበት ሰላማዊ ሠልፍ https://www.facebook.com/photo.php?fbid … =3&theater ማድረጉን ተከትሎ፣ በተለይ በአመራር ኮሚቴው ላይ ጫናና ወከባ ሲደርስበት መቆየቱን ገልጿል፡፡
በመሆኑም የክልሉ መንግሥት በተቀናጀ መንገድ በአባላቱና በአመራሩ ላይ በአድማ በታኝና ፖሊስ ሠራዊት በታገዘ ኃይል አማካይነት፣ ከየካቲት 28 ቀን 2006 ዓ.ም. እስከ መጋቢት 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ድረስ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ በድምሩ 50 አመራርና አባላት ከመኖሪያ ቤታቸው ተወስደው እንደታሰሩበት ኮሚቴው አስታውቋል፡፡ በመተማ ወረዳ ሰላማዊ ሠልፍ አድርገው በሰላም ካጠናቀቁ በኋላም የታሰሩ አባላት እንዳሉም አክሏል፡፡
የክልሉ መንግሥት በምን ምክንያት እንዳሰራቸው ግልጽ ባያደርግም፣ የታሰሩ አባላቱ በቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዳይጠየቁ፣ ከጎንደር በ80 እና 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኙ ዳባትና ደባርቅ ወረዳዎች ተወስደው መታተሰራቸው የሰብዓዊ መብት ረገጣ መሆኑን ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
የቅማንት ብሔረሰብ ተወካይ ኮሚቴ በአባላቱና አመራሩ ላይ የአማራ ክልል መንግት ፈጽሞብኛል ስለሚለው እስራትና መንገላታት ማብራሪያ እንዲሰጥ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን መምርያ ሲጠየቅ፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ኮማንደር ሰኢድ መሐመድ ምንም መረጃ እንደሌላቸው ገልጸው፣ የሰሜን ጎንደር ዞን ፖሊስ መምርያን ለማብራሪያ ጠቁመዋል፡፡ የሰሜን ጎንደር ፖሊስ መምርያ ፖሊስ ባልደረባ የሆኑትና ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ፖሊስ፣ ‹‹እኛ ቅማንት የሚባል ብሔረሰብ አናውቅም፤ የምናውቃቸው አማራ መሆናቸውን ነው፤›› ካሉ በኋላ፣ በበኩላቸው የሰሜን ጎደር ዞን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወደ ኮማንደር ዘመነ አመሸ ቢጠቁሙም፣ የቢሮም ሆነ የግል ስልካቸውን ሊያነሱ ባለመቻላቸው የኮማንደሩን ምላሽ ማካተት አልተቻለም፡፡ Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ) ምንጭ ረፖርተር ጋዘጣ