ያለ ለውጥ፣ ያለ ዋስትና መራመድ አይቻልም፡፡

እየደጋገምን የምናጠፋው ጥፋት እኛን ራሳችንን ይዞ እንዳይጠፋ መጠንቀቅ ያባት ነው!

ያለ ለውጥ፣ ያለ ዋስትና መራመድ አይቻልም፡፡
በማንኛውም ረገድ ራስን መቻል እንደሚኖርብን ልብ እንበል፡፡ በምግብ ራሳችንን ችለን ረሀብተኛ ዲሞክራሲ ይዘን እንጓዝ ብንል የማያዋጣንን ያህል፤ በባዶ ሆድም ዲሞክራሲን አንግቦ መጓዝ ወንዝ አያሻግረንም፡፡ ጥቂት የናጠጡ ሀብታሞችና አያሌ የኔ-ብጤዎች ያሏት ሀገርም ሆነ ሰላሟን አጥታ ብዙ ሀብታሞችን ያፈራች ሀገር እንድትኖረን አይደለም ደፋ-ቀና የምንለው፡፡

እንደጥንቱ መፈክር “ጉዟችን ረጅም ትግላችን መራራ” ነው ማለትም አያዛልቀንም፡፡ ሁሌም ረጅም፣ ሁሌም መራራ መሆን የለበትምና! ያለ ለውጥ፣ ያለ ዋስትና መራመድ አይቻልም፡፡ የለውጥ አንቀሳቃሹ በአብዛኛው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ በዕውቀት የተገነባ፣ ለውጥ የገባው፣ ዛሬ ላይ የተደረሰው ብዙ ለውጥና መስዋዕትነት ታይቶ መሆኑን የተረዳ ወጣት እንጂ “ፋስት” በሚል ታርጋ የታሸገ የቢዝነስ ተሯሯጭ ለብ-ለብ ትውልድ ብቻ እንዳይሆን አገርና ነገር የገባው ወጣት መገንባት ያስፈልጋል፡፡ባለራዕይ-ለማኝ ዐባይ ሲገደብ የምሰጥህ ሁለት ብር አበድረኝ ይላል::

ያልፈጠርነውን፣ ያላስተማርነውን፣ በአግባቡ ያላነፅነውን ልጅ የሌለ ቅፅል ሰጥተን ብናሞካሸው ረብነት የለውም፡፡ በአናቱ ቅቤ ጣል ያለበት ሹሮ ዓይነት ካፒታሊዝም ኑሮአችን ቅቤ በቅቤ ነው እንደማያሰኝ ሁሉ፤ በእንዲህ ያለ ሥርዓት ውስጥ የሚያድግም ልጅ በአርቲፊሻል የተኳኳለ ከመሆን በቀር ኦርጅናሌ እንደማይሆን እናስተውል፡፡

ከመጠላለፍ ይሰውረን፡፡አደቡን ይስጠን፡፡ በተጠራጠርነው ሁሉ ፍርድ ከመስጠት ያድነን፡፡ እየደጋገምን የምናጠፋው ጥፋት እኛን ራሳችንን ይዞ እንዳይጠፋ መጠንቀቅ ያባት ነው! የምንገባው ቃል መፈፀሙን የሚያረጋግጥልን አንድም ታሪካችን፣ ሁለትም ለራስ መታመናችን ነው! በተግባር የምንሠራው በቃል የምናወራውን ካልመሰለ ዕቅዳችን፣ ስትራቴጂያችን ሁሉ፤ ውሃ የበላው ቤት እንደሚሆን አንርሳ! በታሪክ ያየነው ስህተት እንዳይደገም መጣጣር አዲስ ታሪክ መሥራት ነው!