ውህደት ለምን ይኮነናል?

ውህደት ለምን ይኮነናል? በዳንኤል ተፈራ
#Ethiopia #UDJ #AEUP #Blueparty #EPRDF #Ginbot7

ሰሞኑን በውህደት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ዘመቻ ተከፍቷል፡፡ እየተለፋበት ባለው የውህደት እንቅስቃሴ ላይ ዘመቻ የከፈቱ ኃይሎችን በሦስት ከፍሎ ማየት የሚቻል ይመስለኛል፡፡

1ኛ. ኢህአዴግ ሲሆን ተቃዋሚዎችን በተበታተነ ሁኔታ በመግጠም አሸናፊ ሆኖ መውጣት ይቻላል ብሎ ስለሚያምን ነው፡፡ ወደ ኮሮጆ ግልበጣ ከሚሄድ ይልቅ ተቃዋሚዎችን ከፋፍሎ ወይም ተሰባስበው አንድ ትልቅ የፖለቲካ ሃይል እንዳይፈጥሩ በማድረግ ለማሸነፍ መሞከር የመጀመሪያ ምርጫው ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ውህደቶች እንዳይሳኩ ትግል ማድረጉን ይቀጥላል፡፡ በአጠቃላይ ዉህደት ለዚህ ስርዓት አይመቸውም፡፡

2ኛ. በሁለተኛነት ብቻችንን የኢትዮጵያን ፖለቲካ መሸከም እንችላለን የሚሉ ወገኖች እንዲሁ የውህደት እንቅስቃሴው ላይ ቀስት ለመስበቅ የተጣደፉ ይመስለኛል፡፡ ባለብዙ መልኩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ግን ለእንደዚህ አይነት ሀሳብ የሚመች አይደለም፡፡ ፖለቲካችን ወደድንም ጠላንም አታካችም ቢሆን የተለያዩ አስተሳሰቦችን ማቀራረብ የሚፈልግ፣ በውይይት መለዘብ የሚገባውና በብሄርና ህብረብሄር ጫፎች የተወጠረ ነው፡፡ ስለዚህ በሀገር ጉዳይ ላይ መወያየትና ውህደት መፍጠር ተገቢ ነው፡፡ አንድን ‹‹ግሩፕ›› ብቻ እወክላለሁ የሚል የፖለቲካ ሃይል ውህደትን በመኮነን፣ ያውም ውህደት ያስፈልጋል የሚሉ የፖለቲካ ሃይሎችን ሀሳብ ሳያከብርና በጣም ተራ የሆነ ምክንያት እየሰጠ ውህደቱ እንዳይሳካ ይታገላል፡፡ ቢያንስ ብቻየን የኢትዮጵያን ፖለቲካ እሸከማለሁ ማለት መብት እንደሆነ ሁሉ ውህደት ያስፈልጋል ማለትም መብት እንደሆነ የሚያምን አይመስለኝም፡፡ እናም ወንጋራ ሀሳብ የሚያቀርቡ አንዳንድ ግለሰቦች ቆም ብለው ቢያስቡ መልካም ይመስለኛል፡፡

3ኛ. በሦስተኛነት ውህደትን የሚኮንኑት በቅንነት የተቃውሞ ጎራው በመዋሃድ ትልቅ ሃይል መሆን ይገባዋል ብለው ሲወተውቱ የነበሩትና እስካሁን በውህደት ትልቅ ሃይል አለመፈጠሩ የሚያስቆጫቸው አንዳንድ ግለሰቦች ናቸው፡፡ ግን ደግሞ ፖለቲካ ያው ፖለቲካ ነውና እንደ ቅን ሰዎች ሃሳብ ነገሮች ላይሄዱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በሆደ ሰፊነት ውህደቶች እንዲሳኩ መጣር የእያንዳንዱ ሀገር ወዳድ ሁሉ ውትወታና ስራ መሆን አለበት፡፡ በመጨረሻ ግን እኔ በግሌ እንደማምነው የኢትዮጵያን ፖለቲካ የተወሰኑ ግለሰቦች ሊሸከሙት እንደማይችሉ ነው፡፡ ምናልባት ወደፊት ግን ይቻል ይሆናል፡፡ የግለሰቦች መብት የሚረጋገጥበት ስርዓት ከተዘረጋ በኋላ ማለት ነው፡፡ ጎበዝ አሁን እየተደረገ ያለው ትግል ግን ስርዓት የመፍጠር ነውና ሃሳብን እያቻቻሉ መዋሃድ ተገቢና ወቅታዊ ነው፡፡