ስልቶች ጠንቅቆ ማወቅ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ሠንጠረዥ እጅግ ጠቃሚ ነው!!! እጅ መስጠት የሚጀምረው ከአንጐል ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ አስቀድመህ የባላንጣህን አዕምሮ ክበብ::

ብልህ የጥንቶቹንም ለመከተል አይፈልግም፤ ዘልዓለማዊ ነው የሚባል ደረጃ ለመመደብም ሆነ ለማስቀመጥ አይሻም፡፡ ይልቁንም የራሱን ዘመን መርምሮ ለዚያ የሚያዋጣውን ዘዴ ይዘይዳል፡፡“የብልህ አመራር ማለት ገዢው የሱ ሰዎች ልክ እሱ ያዘዘውን ያሰቡ እንዲመስላቸው ማድረግ ነው፤” ትላለች የሩሲያዋ ታላቋ ካቴሪን፡፡ ቀጥላም “ይሄን ለማድረግም፤ አንድ እርምጃ ከህዝቡ ፍላጐት መቅደምና ከአልቀበል – ባይነቱ ጋር መላመድ ነው” ትለናለች፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል! ራመድ ብለን የንግሥቲቱን አካሄድ ስንመረምር ለውጥን ያለጉልበት በዘዴ እንዴት ለማምጣት እችላለሁ? የማለት፤ ጥበባዊ ፍላጐትን የመቀዳጀት ጥያቄን ይሰርጽብናል፡፡ የኛ ዕቅድ፣ መርህ፣ ስትራቴጂ ወዘተ. ከሰማይ በወረደ ኃይልም አይታጠፍም፣ አይቀየርም፣ የምንለውን፤ በልባምነት አውጠንጥነን እንድናይ የሚያግዘን አስተውሎት ነው፡፡

ተቃዋሚዎቻችንን ወይም በግልባጩ ገዢዎችን የምናይበትን ሁኔታ በሁለት ታዋቂ የሰንጠረዥ ጨዋታዎች ምሳሌነት ለማፀኸየት እንሞክር፡፡ አንደኛው፤ ቼዝ ነው፡፡ ሁለተኛው፤ ጐ የሚባለው ጨዋታ ነው ፡፡ ቼዝ ጨዋታ፤ በጠባብ ሜዳ የምንጫወተው ሠንጠረዥ ነው፡፡ 32 ጠጠሮች አሉት – አለቃና ምንዝር የሆኑ። ከሁለቱም ወገን የሚሠለፉ፡፡ የቼዝ ጨዋታ የጠላትን ወታደርና መኮንኖች ግንባር ለግንባር እየገጠሙ መደምሰስ ነው፡፡
በአንፃሩ በ “ጐ” ጨዋታ፣ ከቼዝ ስድስት ጊዜ በሰፋ ሰፊ ሜዳ በየጐራው 52 ጠጠሮችን በጥቁርና በነጭ አሰልፎ መፋለም ሲሆን፤ ዘዴው እያንዳንዱን ጠላት በመክበብ ከእናት ክፍሉ ለይቶ መጠጊያ ማሳጣት ነው፡፡ ከዚያም እንዲሟሽሽና ሽባ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡

በሰፊው ማሰብ፣ ትንሽ ቦታ ሰውቶ፣ ቀስ በቀስ ሰፊ ቦታ መያዝ፤ በመጨረሻም ማሸነፍ ነው፡፡ ሁለቱን ስልቶች ጠንቅቆ ማወቅ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ሠንጠረዥ እጅግ ጠቃሚ ነው! ቅልጥፍናን ከገዢ መሬት በላይ የማየት ክህሎት ይኑርህ ነው ነገሩ!
እጅ መስጠት የሚጀምረው ከአንጐል ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ አስቀድመህ የባላንጣህን አዕምሮ ክበብ ይላሉ፤ የፖለቲካ ፀሐፍት ቀስቅስ፣ ግንዛቤ ፍጠር፣ አንቃ ነው፡፡ የማዖን የጦር ዘዴ ለአዕምሮ ጦርነት ማሰብ ድንቅ ነው፡፡

“ጠላት ሲገፋ አፈግፍግ፡፡ ጠላት ካምፕ ውስጥ ሲያርፍ እረፍት – ንሳው፡፡ ጠላት ሲዳከም አጥቃው፡፡ ጠላት ሲያፈገፍግ አንተ ግፋ፡፡” ዘመኑ የአዕምሮ ትግል ወቅት ነውና አዕምሮህን አስላ፡፡ እቅድህን አጥራ፡፡ ስትራቴጂህን በጥንቃቄ ቀንብብ እንደማለት ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን ከብጤህ፣ ከእኩያህ፣ ከአምሳያህ፣ የፖለቲካ አዕምሮ – ፈርጁ ከአዐምሮ – ፈርጅህ የሚጣጣም የፖለቲካ ባልንጀራ አበጅተህ ወቅቱ በሚፈቅደው ዛፍ ጥላ ሥር ሆነህ፣ ንጋት፣ ቀትርና ጨለማ ለይተህ፣ መጓዝ እንዳለብህ ማወቅ ነው ታላቁ ቁምነገር፡፡ እንዲያው በጥቅም – ቀደም – አካሄድ ለእለት – እንጀራ የተጐዳኘኸውን ወይም ብረት – ድስትና ሸክላ – ድስት ሳትለይ የተወዳጀኸውን ሁሉ የፖለቲካ ወዳጄ ነው ብለህ ከተጓዝክ “ከማይመጥነው ሰው ጋር የሚካኤል ማህበር ጠጣ፤ ተራውን ሳያጠጣ ሞተ” ከመባል አታመልጥም!!#MinilikSalsawi