መንግስት በኢስላም ሀይማኖት ላይ ጠልቃ እንደገባ የህወሃት መስራች አቦይ ስብሃት ለመጀመሪያ ጊዜ አምነዋል ፡:

ከትላት በስቲያ እሁድ የካቲት 2\2006 ከጠዋቱ 3፡30 ጀምሮ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የስብሰባ ማእከል በተካሄደው በዚህ የሽልማት ስነስርዐት ላይ የህወሃት አባት የሚባሉት አቦይ ስብሃትን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ፣ የአዲስ አበባ
ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ ሃላፊ አቶ ፀጋዬ ሀይለማሪያም ፣ የህገ ወጡ መጅሊስ ፕሬዚደንት ዶክተር አህመድ አብዱረህማን ፣ የፌዴራሉ ህገ ወጥ መጅሊስ ምክትል ፕሬዚደንት ታጋይ (ሸይክ ከድር ) ፣ የአንዋር መስጂድ ኢማም ሀጂ ጡሃ ሃሩን ፣ የ10 ሩም ክፍለ ከተማ ሃላፊዎች ፣ የወረዳና የክፍለ ከተሞች መጅሊስ አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ፡፡

ከሽልማቱ በኋላ ንግግር ያደረጉት አቦይ ስብሃት መንግስት በሙስሊሙ ጉዳይ ጠልቃ እንደገባ የሚያረጋግጠውንንግግራቸውን አድርገዋል ፡፡ አቦይ ስብሃት በአዳራሹ ለተገኘው ሰው ባደረጉት ንግግር
“ … ማንኛውም ነገር ከፍተኛ ጥረት ከተደረገበት ስኬት ይኖረዋል ፡፡ የሙስሊሙ ትግል ሲጀመር በጣም ተደናግሮን ነበር ፡፡ በኋላ ብዙ አስበንበት ስናበቃ ለምን መንግስትን የሚደግፍ መጅሊስ አናቋቁምም አልንና ጥረት ጀመርን ፡፡እኔ እራሴ ሄጄ ግዴላችሁም ከየክፍለ ከተማው ሙስሊም ሆነው መንግስትን የሚደግፉ ሁለት ወይም ሶስት ሰዎችን ብቻ ፈልጉልኝ አልኩ …፡፡ የጀመርነው ከቦሌ ክፍለ ከተማ ነው ፡፡ ወደ አምስት ሰዎችን አገኘንና እነሱን አደራጀን ፡፡ በኋላ ሌሎችም ክፍለ ከተሞች የቦሌን ተሞክሮ እንዲተገብሩ አደረግን ፡፡

ሁሉም ክፍለ ከተሞች ጥቂት ሙስሊሞችን አደራጁ ፡፡ ከዚህ በኋላ ነገሩ ሁሉ የተቃና ሆነ ፡፡ እኛም በሁሉም ክፍለ ከተሞች በተወሰኑ ሰዎች
መደራጀቱን ስናውቅ ጉዳዩን የአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮና ክፍለ ከተሞች እንዲረከቡንና በበላይነት እንዲቆጣጠሩት አደረግን ፡፡ እንዲህ
እያለ የሄደው ጥረት አሁን አክራሪዎችን ለማቆም የሚያስችል ጉልበት እንድናገኝ ረድቶናል … ” ብለዋል ፡፡

ይህ የአቶ ስብሃት ነጋ ንግግር መንግስት በሙስሊሙ ጉዳይ ጠልቃ አልገባሁም እያለ ከሚያስተባብለው ጋር የሚጋጭ እንደሆነ ተገልፇል ፡፡ በበርካታ ጉዳዮች ንግግር ያደረጉት አቦይ ስብሃት ኢስላምን የሚያጥላላ ንግግርም አድርገዋል ፡፡ “ቅድም የፌዴራሉ መጅሊስ ምክትል ሰብሳቢው ሸህ ከድር እንዳለው የዱሮው እስልምና ሌላ ነው ፡፡ እኔ ከድርን በፊት ጀምሮ ትግራይ ውስጥ አውቀዋለሁ ፡፡ ምርጥ የህወሃት ታጋይ ነበር ፡፡ አብሮን ታግሏል ፡፡ አሁን ደግሞ ሙስሊሙን እያገለገለ ነው ፡፡ እስልምና እነዚህ የታሰሩት ሰዎች እንደሚሉት አይመስለኝም ፡፡
እስልምና እነዚህ ሰዎች እንደሚያሳዩት ዓይነት ዕምነት ከሆነ እንደ ዕምነት አያስፈልግም ፡፡ ፈፅሞ ሰዎቹ ለሀገር አይሆኑም ” ብለዋል ፡፡ በዚህ
ንግግራቸው በቦታው የነበሩ ሙስሊሞችም ጭብጨባ ለግሰዋቸዋል ፡፡