የህዝብን ችግር ቸል አንበል፡፡ የኋላ ኋላ ጣጣው ይመለከተናልና! ምንሊክ ሳልሳዊ

ምንሊክ ሳልሳዊ :- የህዝብን ኑሮና የሀገርን ውስብስብ ችግሮች በወቅቱ የመፍታት ቅን ልቦና ከሌለ ዕጣ- ፈንታ ወዳዘዘው ውድቀት ማምራት ግድ ይሆናል፡፡ የአስተዳደር ብስለታችን፣ የዲፕሎማሲያችን ጥራት፣ ስለፓርቲና ስለ ሀገር ያለን ግንዛቤ፤ የምንመራውን ህዝብ አመኔታና ተቀባይነት የሚያስገኘው ቁልፍ ነገር መሆኑን መቼም ቢሆን መቼም እንወቅ፡፡ የህዝብን የልብ ትርታ፣ የሀገር ወዳዶችንና ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ድምጽ እንደገዝጋዡ ሳይሆን እንደ አጋዡ በማየት ማግባባት፣ ማስማማት፣ ማደራደር ከመሪ የሚጠበቅ የብልህ እርምጃ ነው፡፡

የህዝብን የልብ ትርታ፣ የሀገር ወዳዶችንና ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ድምጽ እንደገዝጋዡ ሳይሆን እንደ አጋዡ በማየት ማግባባት፣ ማስማማት፣ ማደራደር ከመሪ የሚጠበቅ የብልህ እርምጃ ነው፡፡
ለትናንሽ የኢኮኖሚ ችግሮች መፍትሔ ሳንሰጥ ወደ ውስብስብና ግዙፍ ችግርነት እንዲያድጉ ከፈቀድንና ቸልታችን ከበዛ፤ ያለ ጥርጥር ወደ ፖለቲካዊ ችግርነት ማደጋቸው አይቀሬ ነው፡፡ የወሎ ረሃብ እንደተነናቀ ወደ አብታዊ ማዕበልነት ተለወጠ፡፡ የሚሊተሪ ዲክታተራዊ አገዛዝ መናጠጥ፣ የቢሮክራሲያዊ በደል ማጠጥ፣ የሥልጣን መባለግና ያላግባብ መበልፀግ የአማጽያንን መፈልፈልና የተቃዋሚን ቁርጠኝነት መውለዱን ወለደ፡፡

ዛሬም የህዝብን ኑሮና የሀገርን ውስብስብ ችግሮች በወቅቱ የመፍታት ቅን ልቦና ከሌለ ዕጣ- ፈንታ ወዳዘዘው ውድቀት ማምራት ግድ ይሆናል፡፡ በዚህ ጉዳይ የመንግሥት ዋንኛ ትኩረት የአንበሳውን ድርሻ ይውሰድ እንጂ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራትና ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጐች ወዘተ የነገዋ አገራችን ዕጣ-ፈንታ ይመለከተናል ማለት ኤጭ የማይባል ነገር መሆኑን ልብ ማለት ደግ ነው!

ዕጣ-ፈንታችንን አናመልጥም፡፡ የዕጣ-ፈንታችን አካል ነን፡፡ የምንለው፣ የምናቅደው፣ የምንራዕየው ሁሉ የእኛው አካል ነው፡፡ በተናገርነው እንነገርበታለን፡፡ በደነገግነው እንቀጣበታለን፡፡ በደሰኮርነው እናፍርበታለን ወይም እንኮራበታለን፡፡ በተለይ መንግስት ስንሆን ባወጣነው ህግ እከሌ ከእከሌ ሳንል፣ ወገናዊና ኢፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ መተዳደርና መቀጣት አለብን፡፡ የመንግሥትነታችን ትልቅ ቁም ነገር የህዝብን ደህንነትና የሀገርን ህልውና መታደግ ነው፡፡ ይህ ዋና ኃላፊነት ነው፡፡ ህዝብ እንዳይሸበር፣ እንዳይጠራጠር፣ ዕምነት እንዳያጣ ማድረግ፤ በአገሩ፣ በመንግሥቱና በኃላፊዎቹ ላይ የመተማመን ስሜት እንዲያድርበት ያደርገዋል፡፡ምንሊክ ሳልሳዊ