ተፃራሪ ኃይሎች በአንድ ቦታ ተገኝተው የሃሳብ ፍልሚያ ያደረጉበት መድረክ MUST READ

በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን የድህረምረቃ ተማሪዎች የኢትዮጵያን የፕሬስ ሁኔታ በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ውስጥ የሚኖረውን ሚና በተመለከተ የአንድ ቀን የውይይት መድረክ አዘጋጅተው ነበር።

መድረኩ ዘግየት ብሎ ቢጀመርም የተጠናቀቀውን ግን ከምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ ነው። የውይይቱ ሙቀትና ግለት በፈጠረው ስሜት የሻይና ቡና እረፍትን ያስፈለገው አልነበረም። በውይይቱ ላይ በርካታ ርዕዮተ ዓለማዊ መፋጨቶችና ጉንተላዎች የታዩበት ነው። ውይይቱ በዋናነት ኢህአዴግ እመራበታለሁ በሚለው “ልማታዊ ዴሞክራሲ” አስተሳሰብ ውስጥ የፕሬሱ ሚና ምን እንደሆነ ለማየት ቢፈለግም፤ ውይይቱ ግን ኢህአዴግና አንድነት ፓርቲ የሚሟገቱበት እንዲሁም ዶ/ር ዳኛቸውና አሰፋና የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል በኀሳብ የተጎሻሸሙበት፣ የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው የፓርቲያቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ የሞከሩበት፤ አቦይ ስብሃትና አቶ ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው የኢህአዴግን ጥቅም ላለማስነካት የተፋለሙበት፤ ሁሉም ተፃራሪ ኃይሎች በአንድ ቦታ ተገኝተው የሃሳብ ፍልሚያ ያደረጉበት መድረክ ነበር ለማለት ይቻላል። ውይይቱ የተቃራኒ አስተሳሰብ ባላቸው ወገኖች የሚደረግ ቢሆንም፤ ዶ/ር ዘነበ በየነ መድረኩን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መርተውታል።

በውይይት መድረኩ የተገኙ፣ ጥናት ያቀረቡ ወገኖች የአሰላለፍ መስመራቸው ከወደ ገዢው ፓርቲ የሚያደሉ ቢመስሉም፤ ከተሳታፊዎች ተነስተው የነበሩ ኀሳቦችም ሚዛናቸው ከፍተኛ ስለነበር ውይይቱ ውጥረት ይታይበት ነበር። በመጠኑም ቢሆን የምርጫ 97 የምርጫ ክርክር የሚያስታውስ ይመስል ነበር። በምርጫ 97 ወቅት የኢህአዴግ ተከራካሪዎች በኀሳብ እጥረት ቢበለጡም በእሁድ ዕለቱ ውይይት ላይ ግን ለኢትዮጵያ የሚበጀው መንግስታዊ ስርዓት “ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ” ነው ሲሉ ተሟግተዋል። በአንፃሩ “ልማታዊ ብሎ ዴሞክራሲ” የለም በሚል ከፍተኛ የሆነ የኀሳብ ትንቅንቅ የታየበት ነበር።
የዕለቱ ዋነኛው መከራከሪያ በልማታዊ ዴሞክራሲ ስርዓት ውስጥ የሚዲያው ሚና ምን መሆን እንዳለበትና በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ እንዲያተኩር ቢፈለግም ፖለቲካዊ ክርክሩ የጎላበት ነበር።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት ኃላፊ ዶ/ር አብዲሳ ዘርአይ ለመወያያ ባቀረቡት ጽሁፍ ላይ የልማታዊ መንግስት አስተሳሰብ ከሩቅ ምስራቅ ሀገራት ማለትም ከደቡብ ኮሪያ፣ ከታይዋንና ከጃፓን የሚቀዳ አስተሳሰብ መሆኑን በመጠቆም የአስተሳሰቡን ተግዳሮቶች ወገናዊ ባልሆነ (Neutral) መንገድ አቅርበውታል። “የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ” የሚለውንም የኢህአዴግ መስመር ብዥታ ያለበት አካሄድ መሆኑንም በስሱ ገልፀውታል። ከሁሉም በላይ ልማታዊም ተባለ ዴሞክራሲያዊ ቢያንስ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በጋራ ሊያግባባ የሚችል፣ ሀገራዊ መግባባት (National Consensus) አስፈላጊነትን ደጋግመው ገልፀዋል። ዶ/ር አብዲሳ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ከ400 በላይ ሰዎች ታስረዋል በሚባልበት ሀገር ይሄንን ገዢ ሀሳብ ወገናዊ ባልሆነ መንገድ ማንፀባረቃቸው በተወያዮች ዘንድ በበጎ እንዲታይላቸው አድርጓል። ይሁን እንጂ ዶ/ር አብዲሳ ለብሔራዊ መግባባት “የታሰሩ ይፈቱ፣ በውጪ የተሰደዱም ይመለሱ፣ መንግስትና ተቃዋሚዎች ያለቅድመ ሁኔታ ይደራደሩ” በሚል መጠን (Tone) ቢናገሩት የተሻለ እንደነበረም መገመት ይቻላል። ለዚህም ይመስላል የዶ/ር አብዲሳን የመወያያ ጽሁፍ አፍቃሬ የገዢው ፓርቲ ተወያዮችንና ተቀዋሚዎችን ያላጠገበው።

የፋና ብሮድካሰት ኮርፖሬት አክሲዮን ማኅበር ሥራአስኪያጅ በዕለቱ የመወያያ ጽሁፍ ካቀረቡ አንዱ ነበሩ። ስራ አስኪያጁ አቶ ወልዱ ይምሰል ሚዲያው በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ በሚፈጠረው ፖለቲካል ኢኮኖሚ ውስጥ ወሳኝ ተሳትፎ ከሌለው በቀር ሚናውን መወጣት እንደማይችል በመግለፅ አሁን ያለውን ሚዲያ ተችተዋል። በተለይ የግል ሚዲያውን አነሳስና አመጣጥ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ገልፀውታል። አቶ ወልዱ ሚዲያው በዴቨሎፕመንታል ዴሞክራሲ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ለመሆን የፋና ብሮድካስትን ሞዴል የሚመስል ነገር ተናግረዋል። በዕለቱ በስብሰባው ላይ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ወክለው የተገኙት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ በአሁኑ ወቅት ያለው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሳይሆን የፖለቲካ ስልጣን ወይም ኃይል (Political Power) ነው በማለት የአቶ ወልዱን ጥናት በአጭር ቃል መትተውታል።

ዶ/ሩ በዕለቱ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ከመሰረቱ (Public) የሕዝብ ቢሆንም የግል (Private) ሆኖ ከመቆየት መጥቶ አሁን ሕዝባዊ የበላይነት ይዞ በመጣበት ጊዜ ውይይቱ መካሄዱን አወድሰዋል። ነገር ግን በውይይቱ ላይ ሁሉም አካላት አለመጋበዛቸው ወይም ግብዣው ያላረካቸው መሆኑን ሳይናገሩ አላለፉም። በውይይቱ የተሳተፉ አካላት ሚዛናዊ አለመሆኑንም ለመጥቀስ የገብረክርስቶስ አባትን ተረት የአለቃ ደስታ ነገዎ የመጀመሪያው የአፄ ኃይለስላሴ ፓርላማ ሲቋቋም አፄ ኃይለስላሴ የፓርላማው ተሰብሳቢዎችን ከአንድ ወገን መሆናቸውን በማየት (እነዚህ ሰዎች የሚመክሩ ወይስ የሚመከርባቸው) በማለት የውይይቱ ተሳታፊዎች ሚዛናዊ አለመሆን ጠቅሰዋል። ከዚሁ የተሳታፊዎችና አቅራቢዎች ሚዛናዊ አለመሆን ጋር በተያያዘም “አንዳንድ ሚኒስትር ዲኤታዎችን በማይበት ጊዜ” በማለት የአቶ ሽመልስ ከማልን በውይይቱ ላይ መገኘት ጥያቄ እንዳጫረባቸው ጠቅሰዋል።
የዶ/ር አብዲሳን የማወያያ ጽሁፍን ዶ/ር ዳኛቸው ሲያሄሱም በልማታዊ መንግስትነትና በዴሞክራሲያዊ መንግስት መካከል ውጥረት (Tension) አለ ማለታቸውን እንደሚስማሙበት ገልፀዋል። በደርግ ጊዜም እኩልነት ከነፃነት (Equality Vs Liberty) የተፋጠጡበት በመሆኑ ደርግ የዜጎችን ነፃነት ጨፍልቆ እኩልነት ሊያመጣ ፈለገ ብለዋል። በእሳቸው አገላለፅ “አሁን የመጣብን ጉድ” ያሉት ልማትን በበላይነት ይወስድና ነፃነትን (Liberty) ይጨፈልቃል። ኢህአዴግ አሁን የሚመራበት “ልማታዊና ዴሞክራሲ የፈለጋችሁትን ያህል ብትባባሉት አይታረቅም ብለዋል።

በመቀጠል የተናገሩት አቦይ ስብሃት ነበሩ። የአቦይ ስብሃት ምላሽ ለዶ/ር ዳኛቸው መልስ የሚመስል ነበር። በአቦይ ስብሃት እምነት ልማት እንደ አይዲዎሎጂ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው። የመኖር ወይም ያለመኖር ነው። በአቦይ እምነት ልማት የዴሞክራሲ መሰረት ነው። የዴሞክራሲ ኃይሎች የሚባሉ ባለሃብቱና ላብ አደሩ ናቸው። ሌሎቹ የደጋፊነት ሚና ሊኖራቸው ይችላል። ልማት የእንጀራና የቤት ጉዳይ ሳይሆን የፀጥታ ጉዳይ ነው። ልማት ያለ ዴሞክራሲ አይሄድም። ቢያንስ ባለው ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ መብቶች መፈቀድ ስላለባቸው። ኢህአዴግ በሕገመንግስቱ እነዚህን መብቶች አስቀምጧል። እነዚህም የመነጋገር የመፃፍና የብሔር እኩልነት ናቸው ብለዋል።

“ልማትና ዴሞክራሲ አይነጣጠሉም” የሚለውን ደግሞ አቶ ስብሃት ሲያስረዱ “አንዱ ያለ ሌላው ሊኖር አይችልም” ብለዋል። በኢትዮጵያ ልማት ከሌለ ዴሞክራሲ የለም። ሁለቱም ተባብረው መሄድ አለባቸው ብለዋል። እንደ አቦይ ሰብሃት ገለፃ በሀገሪቱ የዴሞክራሲ መገለጫዎች አንዱ የነፃ ገበያ ስርዓት ነው። ነገር ግን የነፃ ገበያ አስተሳሰብና ኢህአዴግ የተዋወቁት በድንገት ነው። አቦይ ስብሃት የተገናኙበትንም አጋጣሚ ሲገልፁ፤ “መጀመሪያ የነበርነው ሶሻሊዝም ነበር። ነገር ግን ወደ ካፒታሊዝም እንዙር ተብሎ ነገሩ ሲጠና ሰዎች ወደ ውጪ ልከን፣ መፃህፍት ከውጪ አምጥተን ነበር። ይሄ ካፒታሊዝም የሚባል ነገር ምን እንደሆነ በሀገሪቱም ሆነ እኛም እንደ ድርጅት አናውቀውም። ነፃ የኢኮኖሚ ባዕዳዊ እንሰሳ በመሆኑ ይሄንን ባዕድ እንሰሳ ለማጥናት ብዙ ጊዜ ወስዶብናል። በደርግም ቢሆን የነፃ ገበያ አስተሳሰብ ብዙ ሰው አስገድሏል። ኢህአዴግም ነፃ ገበያን ለማጥናት በአራቱም አቅጣጫ ሰው ልኮ በታላቅ እሩጫ አስጠንቷል” ብለዋል። ከዚያም ወደ ዴቨሎፕመንታል መንግስት ማምራቱንና በእሳቸው ቃል በቃል አገላለፅ “የመንግስት እጅ ያለበት ነፃ የኢኮኖሚ ስርዓት” መመስረቱን አስረድተዋል። ስለሆነም መንግስት በጥንቃቄ በተመረጡ ጉዳዮች ገበያው ሊፈፅማቸው በማይችል መስኮች እጁን ያስገባል። ልማታዊ ዴሞክራሲ መንግስት ማለት ይሄው ነው ብለዋል። መንግስት እጁን ያላስገባበት ካፒታሊዝም እንደሌለ በመናገር የእንግሊዝም ሆነ የአሜሪካ መንግስታት ልማታዊ መንግስታት እንደነበሩም ተናግረዋል።
በመቀጠል መነጋገሪያው ወደ አንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወጣቱ ፖለቲከኛ ሀብታሙ አያሌው ነበር። አቶ ሃብታሙ አገዛዙ በልማታዊ መንግስት ባህሪይ ስም እንቅፋት ናቸው ያላቸውን በማጥፋት የተመሠረተ በመሆኑ ለዴሞክራሲያዊ ሂደት መፈናፈኛ የማይሰጥ ስርዓት ነው ብሎታል። እስካሁንም ድረስ አንዱን ከአንዱ ከማምታታት ባለፈ ኢህአዴግ ስለልማታዊ መንግስት ግልፅ አለመሆኑን ጠቅሷል። በተለይ ከ1993 ዓ.ም “ተሃድሶ” በኋላ የመጣው የኢህአዴግ ባህሪ ልማታዊ አስተሳሰብን እያቀነቀኑ በስልጣን ላይ በመቆየት ገዢ የመሆን ፍላጎት መኖሩን፣ ልማት የሕዝቡና የሀገር ሳይሆን የገዢው ፓርቲ ህልውና ተደርጎ መታየቱን ከግምት የሚያስገባ እንደሆነና በዙሪያው ደግሞ እንቅፋት ይሆናሉ ብሎ የሚያስባቸውን ገለል በማድረግ፣ አስቀድሞ ይዞት በመጣው የፖለቲካ ባህሪው የሚነሳውን ማንነቱን በጉልበት እያሰፈነ የሚሄድ ስርዓት ነው ብሎታል።

ይሄ ስርዓት ደግሞ የቱንም ያህል ተሻግሮ ተሻሽሎ ቢመጣ ልማታዊ ባህሪውን ይዞ ለስልጣኑ እንቅፋት የሚሆኑትን በጠላትነት ፈርጆ መንቀሳቀሱን የጠቀሰው አቶ ሀብታሙ በዚህ ረገድ የግል ሴክተሩን ከማቀጨጭ ባለፈ ምሁራንን በጥርጣሬ እንደሚያይና የግል ሴክተሩን በፖለቲካ ካድሬ ከመምራት ባለፈ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወደ ዳር ማግለሉን ጠቅሷል። ኢህአዴግ ሁሉንም አገልግሎ እያለ የተለየ ኀሳብ መስተናገድ ባልቻለበት ሁኔታ ዴሞክራሲ እንዴት ሊኖር ይችላል ሲልም ጠይቋል።

“ኢህአዴግ ከእኔ የተለየ አስተሳሰብ የያዘ በሙሉ መጥፋት አለበት ብሎ የሚያምን ስርዓት እንዴት አድርጎ ዴሞክራሲያዊ ግን ደግሞ ልማታዊ የሚሆነው” የሚለው አቶ ሀብታሙ አሁንም በልማትም ሆነ በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ያስፈልጋል ብሏል።
የግል ሚዲያውን በተመለከተ የሬዲዮ ፋና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ወልዱ እና አቦይ ስብሃት የሰጡትን አሉታዊ አስተያየት በተመለከተም አቶ ሃብታሙ ምላሽ ሲሰጥ የሚሚ ስብሃቱን ሬዲዮ ጨምሮ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ የሕዝብ የመገናኛ ብዙሃን ፍርድ ቤት ባልወሰነበት ሁኔታ በሕግ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱትን ተቃዋሚ ፓርቲዎች “አሸባሪ ናቸው” እንደሚሉ በመግለፅ ከግሉ ሚዲያ በላይ መወቀስ ያለባቸው መሆኑን ጠቅሷል። በጥቅሉ በሂደት ይመጣል የተባለው ዴሞክራሲ ሂደቱ እየተደናቀፈ በሂደት ይመጣል ማለት ዘበት ነው። በርካታ ጋዜጠኞችንና ፖለቲከኞችን እስር ቤት ወርውሮ ለብቻው እየፈረጠመ ያለ መንግስት ልማታዊ ባህሪ የለውም፣ የግሉ ሴክተር ከጠቅላላው የሀገሪቱ ሀብት ጂ.ዲ.ፒ 5.6 በመቶ በያዘበት አሳፋሪ ሁኔታ ፈጣን ልማት ሊረጋገጥ አይችልም። በኢትዮጵያ የግል ዘርፍ እድገት የልማት ብቻ ሳይሆን የዴሞክራሲ ጉዳይ ነው። የግል ዘርፉ በቀጨጨበትም ልማት አይመጣም። የግል ዘርፉን የሚያቀጭጭ፣ ምሁሩን የሚጠራጠርና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን “አሸባሪ” የሚል ስርዓት ልማታዊ ሊሆን አይችልም ብሏል። የፖለቲካ አለመረጋጋት ከመፈጠሩም በፊት ኢህአዴግ ከዚህ ባህሪው መውጣት እንዳለበትም ገልጿል። ለዴሞክራሲ ማበብ ወሳኝ የሆኑ ተቋማት ነፃነታቸው ማረጋገጥና ሚዲያውም መሀል ላይ ቆሞ ኅብረተሰብ የሚያገለግል መሆን አለበትም ሲል አስረድቷል።

አቶ ዛዲግ አብርሃ በዚሁ ጉዳይ ላይ ለውይይት የሚሆን ጽሁፍ ከማቅረባቸው ባሻገር ልማታዊነትና ዴሞክራሲያዊነት የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ለማስረዳት ብዙ ብለዋል። አቶ ዛዲግ እምብዛም በሕዝብ የማይታወቁ (public personality) ባይኖራቸው በየጥናታዊ መድረኩ የኢህአዴግን አቋም ከሌሎች በተሻለ የሚያቀርቡ ወጣት ፖለቲከኛ ናቸው። በአሁኑ ወቅት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው።

ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ የሚለውን የገዢው ፓርቲ አስተሳሰብ ለማስረዳት “የማይታረቅ ነው” የሚለውን የዶ/ር ዳኛቸውን፣ የዶ/ር ነጋሶን፣ የዶ/ር ያዕቆብን የአቶ ሀብታሙንና እንዲሁም የዶ/ር አብዲሳን የጥርጣሬ አቋም “የሚታረቅ ነው” በሚል የኮሪያና የታይዋንን ልምድ በማንሳት ለማስረዳት ጥረት አድርገዋል። ኮሪያና ታይዋን ልማታዊ መንግስታት ቢሆኑም ዴሞክራሲያዊ አለመሆናቸውን፣ ለዚህም ምክንያቱ የመጀመሪያው ደሞክራሲያዊ ላለመሆን ማስቻያ ምክንያት (enabling environment) መኖሩ ነው። ይኸውም በደቡብ ኮሪያም ሆነ በታይዋን ብዝሃነት አለመኖሩ፣ ሁለተኛው አርሦ አደሩ እርስ በርስም ሆነ ከገበያ ጋር የተገናኘ commercialized ስላልነበር መንግስትን የመቃወም ችሎታ አልነበረውም። እንዲሁም በወቅቱ ያሉት የደቡብ ኮሪያና የታይዋን መንግስታት ዴሞክራሲያዊ ያለ መሆን ፍላጎት (will) ነበረባቸው። ዴሞክራሲያዊ ያለመሆን ፍላጎታቸው የመጣው ደግሞ አክራሪ የቀኝ ኃይል (far right movement) በመሆናቸው፣ ሕዝባቸውን የሚጠራጠሩ መንግስታት ስለነበሩና ለአርሶ አደሩ መሬት አከፋፍለውትም ቢሆን አያምኑትም። እንዲሁም የሚፈሩት ሌላ ውጫዊ ጠላት የቻይና እና የሰሜን ኮርያ መንግስት ነበር። በእነዚህ ምክንያቶች ልማታዊ ቢሆኑም ዴሞክራሲያዊ አልነበሩም። ነገር ግን በሂደት ወደ ዴሞክሪሲ የተቀየሩት ተበትኖ የነበረው አርሶ አደር ምርት እየጨመረ ሲሄድ Commercialized ሲሆን፤ እርስ በርሱ በመገናኘቱ ለጭቆና የማያመች መሆኑ፤ በሌላ በኩል የመንግስታቱ ዴሞክራሲያዊ ያለመሆን ባህሪ የሶቪየት ኅብረት መፍረሱን ተከትሎ የሚፈሩት ጠላት ስላልነበረና የfar right movement ወደ መሀል መምጣቱን ተከትሎ ወደ ሶሻል ዴሞክራሲ መምጣት በመጀመራቸው ነው ይላሉ።

አቶ ዛዲግ ወደ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሲመጡ በመጀመሪያ ፖለቲካ ኢኮኖሚው በገበያ ያልተሳሰረ አርሦ አደር በመኖሩ ዴሞክራሲያዊ ላልሆነ አስተዳደር ሊመች ቢችልም በሀገሪቱ ከፍተኛ ብዝሐነት አለ ብለዋል። በሀገሪቱ የብሔር የሃይማኖተና የጾታም ብዝሃነት በመኖሩ። ይሄንን አቻችሎ ለመምራት ዴሞክራሲያዊ መሆን አስፈላጊ ነው ብለዋል። በእሳቸው አባባለ ብዝሀነትን ማስተናገድ ባለመቻላችን ከመፍረስ ጫፍ ደርሰን ተመልሰናል ብለዋል። ከዚህ አንፃር አሁን ያለው ስርዓት Undemocratic አይደለም ብለዋል።

በሌላ በኩል አሁን ያለው መንግስት ፀረ-ዴሞክራሲ የመሆን ፍላጎት (will) የለውም ብለዋል። ለዚህ ኀሳባቸው ደግሞ እንደ መከራከሪያ ያቀረቡት ታጋዮች ለልማት፣ ለመልካም አስተዳደርና ለዴሞክራሲ ስርዓት ትምርታቸውን አቋርጠው በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞት ገብረው ያመጡት ስርዓት ነው ብለዋል። “ኢህአዴግ አክራሪ የቀኝ ኃይል አይደለም። ኢህአዴግ ሕዝቡን የሚጠራጠርና አርሶ አደሩን የሚፈራ አይደለም። የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንዳሉት አርሶ አደሩ በሸካራ እጁ እቅፍ ድገፎ ያደርሰው አርሶ አደሩ ነው። እና ኢህአዴግ በአርሶ አደሩ ተፈጥሮ በአርሶ አደሩ እዚህ የደረሰ ሰርዓት ነው” ብለዋል። እንደታይዋንና ኮርያም የሚፈራው ሊውጠው የተዘጋጀ የጎረቤት መንግስት የጦርነት ስጋት ስለሌለበት በማንኛውም መመዘኛ ኢህአዴግ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ የሚሆንበት ዕድል የለውም።
በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ከላይ የተጠቀሱት ተናጋሪዎች ኀሳብ ተጨምቆ ሲታይ ሁለቱ አስተሳሰቦች የሚታረቁበት መስመር ቁልጭ ብሎ የወጣ አይመስልም። ኢህአዴግ ልማት ቢልም እየተካሄደ ያለው ልማት በዋናነት በቻይና መንግስት ብድርና እርዳታ የሚካሄድ መሆኑና ከኅብረተሰቡ የልማት ጥያቄ አንፃር አርኪም በቂም አለመሆኑ በሌላ ወገን ደግሞ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በተመለከተ በሕዝቡም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገሪቱ ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አስጊ መሆኑ የኢሕአዴግን “ልማታዊ ዴሞክራሲ” ብዥታዊነት ይበልጥ ያንፀባረቀ የሚመስል ነው። ኢህአዴግ በንድፈ ኀሳብ የደቦና የመብትን ጥያቄ ሳይነጣጠሉ አስኬዳለሁ ሲል ተቃዋሚዎቹ ደግሞ መብት ይረጋገጥና ከዛ ደቦው (ልማቱ) ይከተላል የሚል ኀሳብ እያንፀባረቁ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። በዚያኑ ዕለት አንድ ወጣት የዩኒቨርስቲ ተማሪ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር “የኢትዮጵያ ሕዝብ ዳቦ ወይስ ነፃነት ቢሉት ነፃነትን ይመርጣል” ማለታቸውን በማስታወስ ግራ መጋባቱንም ገልጿል።

በዕለቱ ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር ተቀራራቢነት ያለው የውይይት ኀሳብ ያቀረቡት አቶ ሞሼ ሰሙና የፎርቹን ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ታምራት ገ/ጊዮርጊስ ነበሩ። ሁለቱንም አቅራቢዎች በልማታዊ ደሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ የፕሬሱን ፈተና ዘርዝረዋል። በተለይ የአቶ ሞሼ ሰሙ ኀሳብ የፕሬሱ የአነሳስ ችግርና የመንግስትን ጫና በማያወላዳ ሁኔታ ጠቅሰውታል። ብዙዎቹ ተሳታፊዎች የአቶ ሙሼን ኀሳብ ዓይንን በማይስብ ማሸጊያ እንደታሸገ ግን ደግሞ ይዘቱ እንደሚጥም ብስኩት የመሰሉትም ነበሩ። የአቶ ሞሼን የጥናት ሃሳብ በሌላ ጊዜ የምንጠቃቅሰው ይሆናል።

ጋዜጠኛ ታምራትም ለጋዜጠኝነት ሙያ ሉአላዊነት ተሟግቷል። ሙያውን ፖለቲከኞች በራሳቸው አሰላለፍ ለማካተት የሚሄዱበተን ጥረት ትክክል እንዳልሆነ ገልጿል። የጥናት ኀሳቡ ከሕገ-መንግስቱ አንፃር በመሆኑ ሕገ-መንግስቱ የነፃነት ሰነድ (Liberal Document) እንደሆነ አስገንዝቧል። ምንም እንኳ በሕገ-መንግስቱ የመልማት መብትንና የብሔር ብሔረሰብ የቡድን መብትን በመጥቀስ ወደ ልማታዊ ሕገ-መንግስት የሳቡት ቢኖሩም ታምራት ግን ሕገ-መንግስቱ መሠረታዊ የመናገር፣ የመፃፍና ሌሎች የግለሰብ መብቶችን በበቂ ሁኔታ ያካተተ በመሆኑ የነፃነት ሰነድ በማለት ኢህአዴግና ደጋፊዎቹ ከልብ ወደማይወዱት ሊብራሊዝም ስቧቸዋል።

ጋዜጠኛ ታምራት በስራ ላይ ያለውን ሕገ-መንግሰት በውስጡ የተካተቱትን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በማስላት፣ የመገንጠልና የቡድን መብት ጥያቄዎችን እንደሌሉ በመቁጠር `Liberal Document` ነው በማለቱ ተቃውሞ የቀረበበት ከኢህአዴግ ወገን ብቻም አልነበረም። ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ “አንተ ለሀብታም ስለምትፅፍ ነው” በሚል ኃይለቃል ፖለቲካ ቢፅፍ ኖሮ የችግሩን ገፈት ይቀምስ እንደነበር በገደምዳሜም ቢሆን አስተያየት ሰጥተውታል። ዶ/ር ዳኛቸው ታምራት ሕገ-መንግስቱ “የነፃነት ሰነድ ነው” ያለበት አገላለፅ የፖለቲካ ጉዳዮችን ፅፎ ቢሆን ኖሮ ይሄንን ቃል በሙሉ ልብ አይጠቀምም ከሚል መነሻ ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ በጋዜጠኛ ታምራት እምነት ሕገ-መንግስቱ የነፃነት ሰነድ ቢሆንም በአስፈፃሚው የሚወጡ ሕጎች ግን ሕገ-መንግስቱን የዘነጉ መሆኑንም ሳይጠቅስ አላለፈም።

በመጨረሻ የተናገሩት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ለዶ/ር ዳኛቸው መልስ የሰጡበት ነበር። አቶ ሽመልስ ዶ/ር ዳኛቸው ነፃ ፕሬስ የለም ማለታቸውን “ደፋር” በሚል አገላለፅ ከመቱት በኋላ “ኀሳባችንን የምንገልፅበት መድረክ አጣን” የሚለውን የዶ/ሩን ቅሬታ ከእኛ በላይ የመጽሔትና የጋዜጣ ፊት በየዕለቱ እየወጡ እንደልባቸው የሚያጨናንቁ ሰዎች ኀሳባችንን መግለፅ አልቻልንም ማለታቸው ቅጥፈት መሆኑን በመግለፅ ሚኒስትር ዴኤታው በሀገሪቱ ነፃ ፕሬስና ኀሳበን የመግለጫ መሳሪያ ችግር እንደሌለ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ የውይይት መድረኩ የተሟሟቀ ነበር ማለት ይቻላል። በርካታ ሃሳቦችም ተፋጭተዋል። በጥቅሉ ፕሮፌሰር አብይፎርድ በመጨረሻ እንዳሉት የዴሞክራሲ ተራራ እየወጣን ነው ብለዋል። ተራራው ትክክል መሆኑን ማመን አለብን። አልፎ አልፎ ግን በውይይት ወቅት ሻካራ ስሜት ሊፈጠር፣ ሊኮሰኩስም ይችላል። ስለዚህ ዴሞክራሲያዊም ሆነ ልማታዊ ስንል ብዙ ጣጣ አለው። እነዚህን ችግሮች ክፍት በሆነ ውይይት ማስኬድ ነው። በመጨረሻም ዴሞክራሲያዊ በሆነ መርህ የሚደረግ ውይይት በፈላጭ ቆራጭ ቋንቋ መሆን የለበትም ብለዋል
በዘሪሁን ሙሉጌታ