The End of Party politics and Dr. Negaso Gidada / የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የፓርቲ ፖለቲካ ፍፃሜ/ Full Interview

ሪፖርተር፡- ዶ/ር ነጋሶ ፖለቲካ በቃኝ በማለት አንድነትን የለቀቁት የአቶ ሌንጮ ልዩ አማካሪ ሆነው ለመሥራት ተስማምተው ነው ይባላል፡፡
ዶ/ር ነጋሶ፡- ሌንጮን ያገኘሁት ከሦስት ዓመት በፊት አንድነት ፓርቲ ስዊድን ጋብዞኝ ሄጄ ነበር፡፡ ከዚያ ስመለስ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ማኅበር ጋብዞኝ ኖርዌይ ሄድኩኝ፡፡ ሌንጮ የሚኖረው እዚያ ነበር፡፡ የሥጋ ዘመዴ በመሆኑ ደውዬ አግኝቼዋለሁ፡፡ ግን ከዘመድ አዝማድ ጥያቄ ውጪ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ውይይት አላደረግንም፡፡ ከዚያ በፊት ግን እኔ ፓርላማ እያለሁ በኢሜይል እንገናኝ ነበር፡፡ መለስ ከልክሎት ነው መሰለኝ አቋርጦ ጠፋ፡፡ ምንም ዓይነት ግንኙነት የለንም፡፡ እንዲያውም ሰሞኑን አንድ ሚዲያና ዶ/ር መረራ ደውለው ‹‹ሌንጮ መጥቷል ይባላል እውነት ነው?›› ብለው ጠየቁኝ፡፡ እንዳልሰማሁና ከነሱ መስማቴን ከመግለጽ ውጪ ምንም ዓይነት ግንኙነት የለኝም፡፡

Image

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ደንቢዶሎ ከተማ ውስጥ ጳጉሜ 3 ቀን 1935 ዓ.ም. ከቄስ ጊዳዳ እና ከወ/ሮ ኢንሲ ሾሊ የተወለዱት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ በ73 ዓመታቸው ለ45 ዓመታት ከቆዩበት የፓርቲ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ራሳቸውን ማግለላቸውን ሰሞኑን ይፋ አድርገዋል፡፡

ለወላጆቻቸው አራተኛ ልጅ የሆኑት ዶ/ር ነጋሶ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በተወለዱበት አካባቢ ከተከታተሉ በኋላ፣ ወደ አዳማ በመምታት ከዘጠነኛ እስከ 11ኛ ክፍል በባይብል አካዳሚ ተምረዋል፡፡ በወቅቱ በመላ አገሪቱ የነበሩ የ11ኛ ከፍል ተማሪዎች በውጤታቸው ሲመረጡ እሳቸውም በመመረጣቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በነበረው በዕደ ማርያም ትምህርት ቤት ገብተው 11ኛ እና 12ኛ ክፍል ተምረዋል፡፡ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ሳይፈተኑ በቀጥታ ወደ ኤዱኬሽን ፋኩልቲ በመግባት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በታሪክ የትምህርት ዘርፍ አግኝተዋል፡፡ ወደ ጀርመን በመጓዝም ሁለተኛ ዲግሪያቸውንና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ወስደዋል፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ላለፉት 45 ዓመታት በነበራቸው የፖለቲካ ተሳትፎና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ታምሩ ጽጌ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ የጀመሩት መቼና እንዴት ነበር?

ዶ/ር ነጋሶ፡- አሥረኛ ክፍል እያለሁ በክረምት ወደ ደንቢዶሎ ስሄድ አንድ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ በአካባቢው ከተለያዩ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ለዕረፍት ይመጣሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ተሰባሰብንና ይኼንን የክረምት ወራት ለምን ተቀምጠን እናሳልፋለን? ለምን አናስተምርም? በማለት ድራማ አዘጋጀን፡፡ ድራማው የአርሶ አደሩን ችግር የሚገልጽ ነበር፡፡ ነገር ግን ድራማውን እንዳናሳይ የአውራጃው ሹም ከለከለን፡፡ በወቅቱ የፓርላማ አባላት ምርጫ የሚደረግበት ጊዜ ተቃርቦ ስለነበር ድራማው የተከለከለው ችግር ይፈጥራል በሚል ተሰግቶ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ምርጫው ደረሰና ግለሰቦች ለፓርላማ አባልነት መወዳደር ጀመሩ፡፡ ፊታውራሪ ገነነ በዳኔ፣ ከአንፊሎ ደግሞ አቶ ከበደና ሲሜንሶ ዴንጋ የሚባሉ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ለውድድሩ ቀረቡ፡፡ በወቅቱ የምርጫ ድምፅ ይሰጥ የነበረው በአንድ ሳጥን ውስጥ ሳይሆን በተወዳዳሪዎቹ ልክ ይዘጋጅና ምሥላቸው ይለጠፍበታል፡፡ እንዳሁኑ ድምፅ የሚሰጠው በአንድ ቀን አልነበረም፡፡ ሳምንቱን ሙሉ ነበር፡፡ አርሶ አደሩ ተመችቶት መጥቶ እስከሚመርጥ የምርጫ ጊዜው ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ቢሆንም፣ ከተወዳዳሪዎቹ አንዱ የሆኑት ሲሜሶ ዴንጋ ውድድሩን በአንድ ቀን ድምፅ አሰጣጥ አሸነፉ፡፡ የማሸነፋቸው ሚስጥር ደግሞ የቅስቀሳ ዘዴያቸው ነበር፡፡ አቶ ሲሜሶ ሦስት ፍሬ ባቄላ ማለት በጣም ያረረ፣ መካከለኛና ጥሬ ይዘው ወደ አርሶ አደሩ በመሄድ ቅስቀሳ ይጀምራሉ፡፡ አርሶ አደሮቹን በመሰብሰብ ‹‹ይኼንን ባቄላ ተመልከቱ፣ የእናንተ ኑሮ የትኛውን ይመስላል?›› በማለት ሲጠይቋቸው ‹‹የኛ ኑሮማ ያረረውን ባቄላ ነው የሚመስለው፤›› ሲሏቸው፣ ‹‹እኔን ከመረጣችሁኝ የፓርላማ አባል ስለምሆን፣ ለንጉሡ በማስረዳት ይኼንን ኑሯችሁን እቀየርላችኋለሁ፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ለአንድ ሳምንት እንዲመርጡ ይደረጉ የነበሩት አርሶ አደሮች በአንድ ቀን የአቶ ሲሜሶን የድምፅ መስጫ ኮሮጆ ሞሉት፡፡ በዚህም ምክንያት ‹‹ይኼ ሰውዬ መንግሥትንና ሕዝብን እያጣላ ነው›› በማለት አቶ ሲሜሶን የአውራጃው ሹም ያስሯቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ እዚያ የነበርን ተማሪዎች፣ መምህራንና የአገር ሽማግሌዎች ሰላማዊ ሠልፍ አደረግን፡፡ ወደ አውራጃ ገዥው ቢሮም ሄደን ትክክል አለመሆናቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ሰጠናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ አስተዳዳሪው ‹‹እናንተ ብዙ ናችሁ፡፡ ልጆችም ናችሁ፡፡ እኔ ከልጆች ጋርም አልነጋገርም፡፡ የበሰሉና ያገር ሽማግሌዎች ነገ ይምጡ፤›› ሲሉን ተመለስን፡፡ በሚቀጥለው ቀንም የተላኩት ሽማግሌዎች ታሰሩ፡፡ ከሁለት ወራት ቆይታ በኋላ ፓርላማ ሲከፈት ጥቅምት 23 ቀን ተለቀቁ፡፡ ይኼ ወደ ፖለቲካው የመግቢያዬ አንዱ መንገድ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚያስ?

ዶ/ር ነጋሶ፡- በወቅቱ የተማሪዎች እንቅስቃሴና ሠልፍ ነበር፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር ጉባዔ ምርጫ ነበር፡፡ በዚህ ውስጥ እኔም እሳተፍ ነበር፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር ከማናቸውም አድሎአዊ አሠራር የፀዳ ነበር፡፡ አንድ ዓይነት ዓላማና አቋም ነበረን፡፡ ‹‹የሕዝቦች መብት ይከበር፣ የሠራተኞች መብት ይከበር፣ የአርሶ አደሩ መብት ይከበር፣ ንጉሣዊ አገዛዝ አንፈልግም፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይመሥረት፣ የሴቶችና የሃይማኖቶች እኩልነት ይከበር፤›› የሚሉትን ዓላማዎች ይዘን ነበር የምንቀሳቀሰው፡፡ ሆኖም ግን እኔ በዕደ ማርያም ትምህርት ቤት ስገባ ሌላ ሁኔታ እየተፈጠረ ነበር፡፡ የሜጫና ቱለማ (የኦሮሞ ማኅበር) ተመሥርቶ ነበር፡፡ የብሔራዊ ፊደል ሠራዊት ሊቀመንበር የነበሩት ጄኔራል ታደሰ ብሩ ሊቀመንበሩ ነበሩ፡፡ የማኅበሩ ዓላማ በልማት ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ ማኅበሩ ባጭር ጊዜ ዝና አገኘ፡፡ ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባዎች ተመርጠው የፓርላማ አባል የነበሩ ሁሉ የማኅበሩ አባል ሆኑ፡፡ እኔም የማኅበሩ አባል ሆንኩኝ፡፡ በወቅቱ 12ኛ ክፍል ነበርኩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተ ወልድ የማኅበሩን ሊቀመንበር ጄኔራል ታደሰ ብሩን ጠርተው የማኅበሩን እንቅስቃሴ እንዲያቆሙ ነገሯቸው፡፡ ‹‹ይኼ ሕዝብ ባህር ነው፡፡ ከተማረ ስለሚያጥለቀልቀን የፊደል ሠራዊት ሌላ ሌላ የምትለውን አቁም፤›› አሏቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጄኔራል ታደሰ ኦሮሞ መሆናቸውን አላወቁም፡፡ በዚህ ጊዜ ጄኔራሉ፣ ‹‹እኛ ለልማት እየተንቀሳቀስን እንዴት አቁሙ እንባላለን›› በማለት ነገሩን ወደ ፖለቲካ በመለወጥ መቀስቀስ ጀመሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ፖለቲካው መስመር መያዝ ጀመረ፡፡ የመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ ‹‹ኩዴታ ታቀደ›› የሚባል ነገር ተሰማ፡፡ የመፈንቅለ መንግሥቱ ዋና ዓላማ አፄ ኃይለ ሥላሴን ለመግደል ነበር፡፡ በ‹‹ኩዴታው›› ውስጥ የተሳተፉት ጄኔራል ታደሰ ብሩና ጓደኛቸው መሆናቸው ሲነገር ጄነራሉ ሸፈቱ፡፡ በዚህ ጊዜ ጳጳሱ አቡነ ቴዎፍሎስ አማልደው ከንጉሡ ጋር አስታረቁዋቸው፡፡ ንጉሡ ከታረቁ በኋላ ጄኔራሉ የትም እንዳይንቀሳቀሱ የቁም እስር ፈረዱባቸው፡፡ ሜጫና ቱለማ ማኅበርም ተከለከለ፡፡ በዚህ ጊዜ ተማሪዎች ተሰባሰብንና ሌላ ማኅበር አቋቋምን፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ሆነን ‹‹ዴዴሳ የዕድገት ማኅበር›› የሚል አቋቋምን፡፡ ዓላማው ከየጠቅላይ ግዛቱ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለሚገቡ አዳሪ ተማሪዎች ሆስቴል ማሠራት ነበር፡፡ ትንሽ እንደተንቀሳቀስን እሱም ተከለከለ፡፡ ከዚያ በኋላ በዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ የተማሪዎች ማኅበር ውስጥ እየተሳተፍን፣ ጥቂት ተማሪዎች ተሰባሰብንና ‹‹ሜጫና ቱለማ ታገደ፣ ዴዴሳ የዕድገት ማኅበርም ታገደ፣ ለምን በማለት ተመካከርን፡፡ በወቅቱ ባሌ ጎባ አካባቢ የኦሮሞ ነፃ አውጪ የሚባል ተቋቁሟል የሚባል ነገር ስለነበር እሱም ተፅዕኖ አሳድሮብን ነበር፡፡ እኛ ለምን ለኦሮሞ ሕዝብ ነፃነት አንታገልም? የሚል ውይይት አደረግን፡፡ ሴቶችም፣ ሃይማኖቶችም፣ አርሶ አደሮችም ለእኩልነታቸው መታገል አለባቸው የሚል አቋም ያዝን፡፡ እነ ጥላሁን ግዛውና ዋለልኝ መኮንን የብሔር ጥያቄ ያነሱበት ወቅትም ነበር፡፡ ያ ያ ተፅዕኖ አሳድሮብን ስለነበር የኦሮሞ ሕዝብ መታገል አለበት በማለት መንቀሳቀስ ጀመርን፡፡ ዲማ ነገዎ (ዮሐንስ ነገዎ) የኦነግ የመጀመሪያው ሊቀመንበር ነበር፡፡ አዲሱ ቶሎሳ፣ ፀጋዬ ነመራ፣ ቦሩ አልዴቻ፣ በቀለ ወልዴ ሆነን መንቀሳቀስ ጀመርን፡፡ ‹‹ቮይስ ኦፍ ኦሮሞ አጌንስት ታይራኒ›› (ፀረ አምባገነንነት የኦሮሞዎች ድምፅ) በሚል በታሪክ ጉዳይ፣ በመሬት ይዞታ ጉዳይ፣ በግብር ጉዳይ፣ በመንግሥት ውስጥ የኦሮሞ ተሳትፎ መድልአ፣ የቋንቋና ሌሎችን ያካተተ ጽሑፍ ተዘጋጅቶ ተበተነ፡፡ እኔ የታሪኩን ጉዳይ ጽፌያለሁ፡፡ በዚህ ጊዜ እነ ባሮ ቱምሳ (የቄስ ጉዲና ወንድምና የኦነግ መሥራች ከነበሩት አንዱ) ናቸው የበተኑት ተብለው ታሰሩ፡፡ ወረቀቱ በብዛት በከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ተበትኖ ስለነበር፣ በእነ መረራ ጉዲና ላይም ተፅዕኖ አሳድሮ በአምቦ አካባቢና በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ ትምህርት ቤቶች እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡ በክረምት 1966 ዓ.ም. ኦነግ ሊመሠረት የቻለውም በዚያ እንቅስቃሴ አማካይነት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ የኦነግ አባል የሆኑት በዚያ ጊዜ ነው?

ዶ/ር ነጋሶ፡- እኔ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበርኩ ጊዜ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መማክርት ጉባዔ አባል ነበርኩ፡፡ በሁሉም እንቅስቃሴ እሳተፍ ነበር፡፡ በመካነ ኢየሱስ በኩል ጀርመን አገር የትምህርት ዕድል ተገኝቶልኝ ስለነበር ወደ ጀርመን ሄድኩኝ፡፡ ይኼ የሆነው የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን ጨርሼ በመምህርነትና በዳይሬክተርነት ወደ ወለጋ ተመልሼ አይራ ትምህርት ቤት ከሠራሁ በኋላ ማለት ነው፡፡ በ1966 ዓ.ም. አብዮቱ በተጀመረበት ወቅት ጀርመን ነበርኩኝ፡፡ አንድ ነገር ለማስታወስ የምፈልገው የትምህርት ዕድሉን አግኝቼ ወደ ጀርመን ለመሄድ ፓስፖርት ለማውጣት አዲስ አበባ ስመጣ (በክረምት 1966)፣ እነ ሌንጮ ለታ፣ ዲማ ነገዎ፣ አዲሱ ቶሎሳ ቀን ቀን አብረውኝ ይውሉና ማታ ማታ ይጠፉብኛል፡፡ ‹‹የት ነው የምትጠፉት?›› ብዬ ጠየቅኳቸው፡፡ ኦነግን በማቋቋም ላይ መሆናቸውንና እነ ታደሰ ብሩም የቁም እስረኛ ከሆኑበት ሐረር መፈታታቸውን ነገሩኝ፡፡ ይኼንን ከመስማቴ ውጪ አባል አልሆንኩም፡፡

ሪፖርተር፡- ጀርመን ከሄዱ በኋላ ግን የፖለቲካ ተሳትፎ ነበረዎት፡፡

ዶ/ር ነጋሶ፡- የሄድኩት ሁለተኛ ዲግሪዬን ጨርሼ ለመመለስ ነበር፡፡ በወቅቱ ግን ቀይ ሽብር በመጀመሩ መመለስ አልቻልኩም፡፡ ጀርመን ውስጥ ከሐረር፣ ከባሌና ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ለትምህርት የሄዱ ተማሪዎች (የጄኔራል ዋቆ ጉቱ የባሌ እንቅስቃሴ ቶኩቹማ መሪ የነበሩ) ነበሩ፡፡ በ1966 ዓ.ም. ብዙ እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡ እዚህ እነ ኦነግ ይቋቋማሉ፡፡ መኢሶንና ኢሕአፓ አገር ቤት ለመግባት ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ጀርመን አገር ደግሞ የኦነግ፣ የመኢሶንና የኢሕአፓ ደጋፊዎች አሉ፡፡ ማኅበርም መሥርተዋል፡፡ የኢሕአፓ ተማሪዎች ማኅበር ጄኔራል ዋቆ ጉቱን ጋብዞ (በክረምት 1966 ማለት ነው) ነበር፡፡ በወቅቱ ጄኔራል ዋቆን አጅበው የሄዱና እዚያው ጀርመን የቀሩ እኔ እንደሄድኩኝ አገኙኝ፡፡ ስለአገር ቤት ሁኔታ ጠየቁኝና ነገርኳቸው፡፡ እኔ የሄድኩት በ1967 ዓ.ም. መስከረም ወር ነው፡፡ ከሄድኩኝ ከሦስት ወራት በኋላ ተሰባስበን አንድ መጽሔት በቁቤ ማዘጋጀት እንዳለብን ወሰንን፡፡ መጽሔቱን አዘጋጀንና በብዙ የአውሮፓ አገሮች ጭምር መዳረስ ጀመረ፡፡ በዚህ መጽሔት አማካይነት ሰው መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ቀጥሎ ‹‹ለምን ማኅበር አናቋቁምም?›› ተብሎ በጀርመን ‹‹የኦሮሞ ተማሪዎች ማኅበር›› የሚል አቋቋምን፡፡ እኔ አመራር ነበርኩ፡፡ በክረምት 1967 ዓ.ም. ደግሞ ‹‹የኦሮሞ ተማሪዎች ማኅበር በአውሮፓ›› የሚል ሌላ ማኅበር አቋቋምን፡፡ በዚያም ውስጥ እ.ኤ.አ. እስከ 1980 ድረስ ነበርኩኝ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1977 ዲማ ከሴኔጋል ወደ ጀርመን መጥቶ ነበር፡፡ የኦነግ መሥራች ስለነበር ጀርመን የመጣበት ዓላማ የኦሮሞ ተማሪዎች ማኅበርንና የኦሮሞ ተማሪዎች ማኅበር በአውሮፓ አባላትን አሳምኖ የኦነግ አባል ለማድረግ ነበር፡፡ ስለኦነግም ገለጻ አደረገ፡፡ እኔም በማኅበሩ በኩል አባል ሳልሆን ለኦሮሞ ነፃነት ስል እረዳ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ1980 ወደ አገር ቤት ለመመለስ ስለማልችል የኦነግ አባል ለመሆንና እነሱ ወዳሉበት አካባቢ ሶማሊያ፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ ወይም ሱዳን ሄጀ ለመታገል ጥያቄ አቀረብኩኝ፡፡ እነሱ ግን፣ ‹‹አባል ነህ እዚያው ቆይተህ ትረዳለህ›› በማለት የኦነግ ወኪል አደረጉኝ፡፡ አንድ ዓመት ሳልቆይም በተማሪዎች ማኅበር ውስጥ ጭቅጭቅ ተፈጠረ፡፡ የእኔ ሐሳብ ሁሉም ተማሪዎች ኦነግን እንዲደግፉ ለማድረግ ነበር፡፡ መኢሶን ያቋቋመው የኦሮሞዎች ማኅበር ነበር፡፡ እኔ የኦሮሞ ተማሪዎች ማኅበር በአውሮፓ ከእነሱ ጋር መዋሀድ አለበት የሚል አቋም ያዝኩኝ፡፡ የኦነግ ደጋፊ ማኅበር አባላት ‹‹እንዴት ከእነሱ ጋር እንዋሀድ ትላለህ? ጎበና ከሀዲ ሆንክ እነሱ ጎበናዎች ናቸው አሉ፡፡ የመኢሶን ልጆች ከደርግ ጋር ይሠሩ ስለነበር ጎበናዎች (ከሀዲዎች) ናቸው ይባሉ ነበር፡፡ ‹‹እንዴት ከእነሱ ጋር ትሠራለህ?›› በማለታቸው ማኅበሩን ትቼ ወጣሁ እ.ኤ.አ. በ1981 ከኦነግ አባልነቴ ራሴን አሰናበትኩ፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚያ ወዴት ሄዱ?

ዶ/ር ነጋሶ፡- እ.ኤ.አ. እስከ 1984 ድረስ ምንም ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ሳልገባ ቆየሁ፡፡ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች ወደ ጀርመን አገር ከሄዱ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን የዕርዳታ ድርጅት አቋቋምን፡፡ እ.ኤ.አ. በ1985 የኦነግ ደጋፊ የነበረው አንደኛው የኦሮሞ ተማሪዎች ማኅበር ለሁለት ተከፈለና አንደኛው ጎበና ነው ሲለው ከነበረው መኢሶን ካቋቋመው የኦሮሞ ተማሪዎች ማኅበር ጋር ተቀላቀለ፡፡ በዚህ ጊዜ እኔ እንድመለስ ጠየቁኝ፡፡ ተመልሼ አባል ሆንኩኝ፡፡ ማኅበሩ የኦሮሞዎች ማኅበር በአውሮፓ ተባለ፡፡ ይኼኛው ማኅበር የኦነግ አባል አልነበረም፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ የኦነግ አባል ሆነው ከደጋፊ ማኅበሩ ጋር በመሆን ሲደግፉ ነበር፡፡ ከአባልነቱ ከወጡ በኋላ አዲስ በተቋቋመው የሁለቱ ማኅበሮች ቅልቅል ውስጥ ተመልሰው አባል ሆኑ፡፡ ማኅበሩ ሥራው ምን ነበር? የምትረዱት ወይም የምትወክሉት የትኛውን የፖለቲካ ድርጅት ነበር?

ዶ/ር ነጋሶ፡- የማኅበሩ ዋና ዓላማ ኦሮሞዎችን ለማስተማር፣ የኦሮሞ ትግል ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ እንዲያገኝ ማድረግ፣ በየአካባቢው በሱዳን፣ በኬንያና በሶማሊያ ያሉትን ስደተኞችን መርዳት ነበር፡፡ ግን ማኅበሩ ገና በመመሥረት ላይ እያለ በ1982 ዓ.ም. በአውሮፓ ውስጥ አንድ ቡድን ተፈጠረ፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ነፃነት ድርጅት (OPLO) ተፈጠረ፡፡ የኦነግና የኦፒኤልኦ ልዩነት ነበራቸው፡፡ ኦነግ በኢትዮጵያ ስም ከተደራጁ ማኅበራት ጋር አይሠራም፡፡ ኦፒኤልኦ ግን ዴሞክራሲያዊ ከሆኑ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር እሠራለሁ ይላል፡፡ ይኼ ድርጅት ኦፒኤልኦ እንደተመሠረተ (በጀርመን) ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ መጣ፡፡ ደርግ ተሸነፈ፡፡ በ1982 ዓ.ም. የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ተቋቋመ፡፡ የሕወሓት ወኪል (በጀርመን) ነጋሽ ተክሉ (የዋልታ መሥራች) በኩል መረጃ እናገኝ ነበር፡፡ እነካሱ ኢላላ፣ ተፈራ ዋልዋና ወረደ ጀርመን መጥተው ስለኢሕአዴግና ኦሕዴድ መቋቋም ይነግሩን ነበር፡፡ በ1983 ዓ.ም. ዘመቻዎች ተጀመሩ፡፡ የዋለልኝ ዘመቻ፣ የቴዎድሮስ ዘመቻ፣ ዱላ ወልቂጡማ ቢሉሱማ ዘመቻዎች ነበሩ፡፡ ኢሕአዴግ ከጎጃም ወደ ወለጋ መሸጋገር ሲጀምር ኦፒኤልኦና የኦሮሞዎች ማኅበር በአውሮፓ አንድ ዘመቻ ጀመሩ፡፡ ዘመቻው መቆም አለበት የሚል፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ኢሕአዴግ ወደ ኦሮሚያ መግባት የለበትም፡፡ ይኼ ዳግም ወረራ ነው፡፡ መቆም አለበት አሉ፡፡ በዚያ ወቅት ትግራይና አማራ ክልል ከደርግ ነፃ ወጥተው ነበር፡፡ የእነሱም ጥያቄ ኦሮሚያም ነፃ መሆን አለበት የሚል ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ እኔ ኢሕአዴግ ወደ ኦሮሚያ አይግባ ስትሉ በሌላ አባባል ደርግ በኦሮሚያ ይቆይ እያላችሁ ነው አልኩኝ፡፡ መርዳት አለብን፡፡ ኦሕዴድንና ኢሕአዴግን ረድተን ደርግን ማስወገድ አለብን አልኩኝ፡፡ ባለመስማማታችን ማኅበሩን ለቅቄ ወጣሁ፡፡ ግንቦት 19 ቀን 1983 ዓ.ም. ወደ ሱዳን መጣሁ፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴትና ለምን ወደ ሱዳን ሊመጡ ቻሉ?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣትና ኦሕዴድን ለመቀላቀል፡፡

ሪፖርተር፡- ጀርመን እያሉ የኦሕዴድ አባል ሆነው ነበር እንዴ?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ቀደም ብዬ እንደገለጽኩልህ በጀርመን የኢሕአዴግ ተወካይ ከነበረው ከነጋሽ ተክሉና ከሌሎቹም ጋር ተነጋግረንና ተወያየን ተስማምተን ነበር፡፡ ቪዛ ያዘጋጀልኝና ወደ ሱዳን እንድገባ ያመቻቸልኝም ነጋሽ ተክሉ ነው፡፡ ምክንያቱም እኔ የጀርመን ዜግነት አልፈልግም ብዬ የነበረኝ የስደተኞች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፓስፖርት ነበረኝ፡፡ ቪዛዬን ያመቻቸልኝ ኢሕአዴግ ነው፡፡ የአዲስ አበባ መያዝን የሰማሁት ሱዳን ውስጥ እያለሁ ነው፡፡ ከሱዳን ግንቦት 21 ቀን 1983 ዓ.ም. ተነስተን በጎንደር፣ በቡሬ ዳሞት አድርገን ግንቦት 23 ቀን 1983 ዓ.ም. ነቀምቴ ገባሁ፡፡ ከኦሕዴድ ጋር አንድ ወር ቆይቼ ወደ ጀርመን በመመለስ ጠቅልዬ ወደ ኢትዮጵያ ተመለስኩኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ኢትዮጵያ ጠቅልለው ከተመለሱ በኋላ በዋናነት ሊሠሩት ወይም ሊሳተፉበት ያቀዱት ነገር ምን ነበር?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ዋና ዕቅዴ ወደ አይራ ተመልሼ ለማስተማር ነበር፡፡ ሌላ ሐሳብ አልነበረኝም፡፡ በወቅቱ ከመተማ እስከ ነቀምቴ ድረስ የነበረው አብዛኛው ሠራዊት የሕወሓት ነበር፡፡ ነቀምቴ እንደደረስኩ የኦሕዴድ ተሳትፎ በኢሕአዴግ ውስጥ ምን ያህል ነው? ከዳር እስከ ዳር የሕወሓት ሠራዊት ብቻ መታየቱ ደግሞ በአውሮፓ ‹‹ዳግም ወረራ ነው›› እየተባለ የሚወራውን የሚያረጋግጥ በመምሰሉ ለምን በሚል ጥያቄም አነሳሁ፡፡ በዚህ ወቅት ኩማ ደመቅሳ፣ አባዱላ ገመዳና ሐሰን ዓሊን ነበር ያገኘኋቸው፡፡ ስጠይቃቸው ‹‹እኛ የተመሠረትነው በቅርቡ ነው፡፡ ዓመትም አልሞላንም፡፡ እነሱ ግን ከአሥር ዓመታት በላይ ሆኗቸዋል፤›› አሉኝ፡፡ አሁን በምልመላ ራሳችንን ማጠናከር እንዳለብን ገለጹልኝና የኢሕአዴግ ሠራዊት የመጣው ክልሉን ይዞ ለመቆየት ሳይሆን የደርግ ሠራዊትን ተባብሮ ለማባረር መሆኑን ሲያስረዱኝ ተስማማሁ፡፡ እኔም መርዳት እንዳለብኝ ወስንኩኝና የኦሕዴድ አባል ሆንኩኝ፡፡ የሰላም ኮንፈረንስ በተደረገበት ወቅት ጠቅልዬ ለመምጣት ጀርመን ሄጀ ስለነበር አልተሳተፍኩኝም፡፡ ተመልሼ ስመጣ የሽግግር ፓርላማ ሲቋቋም ኦሕዴድ ከ12ቱ ወኪሎቹ አንዱ እንድሆን መረጠኝ፡፡ የሽግግር መንግሥት ተቋቋመ፡፡ በወቅቱ ታምራት ላይኔ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንድሆን ጠየቀኝ፡፡ በ1984 ዓ.ም. የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኜ ተሾምኩ፡፡ በዚያ ወቅት ዲማ ነገዎ የማስታወቂያ ሚኒስትር ነበር፡፡ እሱ ሲለቅ በ1985 ዓ.ም. ወደ ማስታወቂያ ሚኒስትር ተዛወርኩኝ፡፡ የክልሎች ማቋቋሚያ ምርጫ ሲደረግ የምርጫ ኮሚሽን አባል ሆንኩኝ፡፡ እኔና ዳዊት ዮሐንስ ለሕገ መንግሥት ጉባዔ ከኢሕአዴግ ተወከልን፡፡ በ1987 ዓ.ም. ፕሬዚዳንት ሆኜ ተመረጥኩ፡፡ እስከ 1994 ዓ.ም. ድረስ ለሰባት ዓመታት ፕሬዚዳንት ሆኜ ሠራሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከፕሬዚዳንትነት ከለቀቁ በኋላ የፖለቲካ ተሳትፎ አቁመው ነበር፡፡ ለምን ነበር?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ከ1994 ዓ.ም. እስከ 1996 ዓ.ም. ድረስ ምንም ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ አልነበርኩም፡፡ ማለትም ከፖለቲካ ወጥቻለሁ ወይም ምንም ዓይነት ፍላጎት አልነበረኝም ሳይሆን፣ በማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ አልነበርኩም ማለቴ ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም. ደንቢዶሎ በመሄድ በግል ተወዳድሬ ፓርላማ ገባሁ፡፡ እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ በፓርላማ ስሳተፍ ቆይቻለሁ፡፡ ፓርላማ ውስጥ እያለሁ ከእነአቶ ቡልቻ ደመቅሳ፣ ተመስገን ዘውዴ፣ መረራ ጉዲና፣ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ጋር በመወያየት ‹‹ለምን ፓርቲዎቹ አብረው አይሠሩም?›› የሚል ምክክር ጀመርን፡፡ በመቀጠልም መድረክን አቋቋምን፡፡ ወደ ጥምረት ሲሸጋገርና በምርጫ ቦርድ ሲመዘገብ እኔ የግዴታ የአንድ ፓርቲ አባል መሆን ነበረብኝ፡፡ በወቅቱ ከነበሩት ፓርቲዎች የትኛው እንደሚሻለኝ ለመምረጥ ፕሮግራማቸውን ወስጄ አጠናሁ፡፡ የተሻለ ፕሮግራም ያለውና ለእኔ ምርጫ የተስማማኝ አንድነት በመሆኑ የአንድነት አባል ሆንኩኝ፡፡

ሪፖርተር፡- አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲን (አንድነት) ሲቀላቀሉ ‹‹አሁን ገና ለሕዝብ የሚሠራና ከሕዝብ ጋር የሚያገናኝ ፓርቲ አባል ሆንኩኝ፡፡ በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ፤›› ብለው ነበር፡፡ አሁንም እንደነገሩኝ ጥሩ ፕሮግራም ያለውና በወቅቱ ለእኔ ምርጫ የተስማማ ፓርቲ ያገኘሁት አንድነትን ነበር ሲሉኝ፣ ሲቀላቀሉ ባደረጉት ንግግር ላይ ያሉትን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ከአምስት ዓመታት ቆይታ በኋላ በመካከላችሁ ምን ገብቶ ለመለያየት በቃችሁ?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ያንን ማለቴን አሁን አላስታውስም፡፡ ‹‹ከሁሉም የመድረክ አባል ድርጅቶች ልቤን የነካኝ የአንድነት ፕሮግራም ነው፤›› ብዬ ተናግሬ ይሆናል፡፡ ያንን ያልኩት ፕሮግራሙ ደስ ስላለኝ ነው፡፡ ፕሮግራሙ ልክ እንደ መድረክ ለአንድነትና ለሉዓላዊነት ይታገላል፡፡ መገንጠልን አይፈልግም፡፡ እኔ የማምንበት አንድ ነገር አለ፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 ላይ የተቀመጠው፡፡ ‹‹የሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል›› የሚለውን እደግፋለሁ፡፡ አምንበታለሁም ይኼ መብት ነው፡፡ ብዙዎች ይኼንን አንቀጽ የሚያዩት ‹‹መገንጠልን እደግፋለሁ›› ማለት እንደሆነ አድርገው ነው፡፡ ግን ይኼ መብትን ነው የሚያረጋግጠው፡፡ ለእኔ ይኼ አንድ ሕዝብ መብቱን እስከ መገንጠል ማለትም ከመንግሥት ተገንጥለህ ሌላ መንግሥት እስከ ማቋቋም ድረስ ሊሄድ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- አንድነት የሚቃወመው ይኼንን ነው፡፡ መገንጠልን አይደግፍም፡፡ እርስዎም ፕሮግራሙን ሲያጠኑ ያረጋገጡት ነው፡፡ አምነውበትና ወደውም ሐሳቡን በመደገፍ አባል ሆነዋል፡፡ አሁን ደግሞ መብት ነውና እደግፈዋለሁ የሚለው ሐሳብዎ እርስ በርሱ አይጋጭም?

ዶ/ር ነጋሶ፡- አይጋጭም፤ መብትን ማክበርና መደገፍ ነው፡፡ ለምሳሌ ባልና ሚስት ትዳር መሥርተው ሲኖሩ ቢጣሉና አንደኛቸው አልፈልግም ካሉ የፍች መብት መከበር አለበት፡፡ የመብት ጥያቄ ነው፡፡ የአገር ዜጎችም ጉዳይ ተመሳሳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሁሉም መብት ይከበር በሚል ሁሉም ለሚያነሳው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ እየተመራችበት ያለውን ሥርዓት ማስቀጠል ይቻላል?

ዶ/ር ነጋሶ፡- እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ በሚቀርብበት ጊዜ ተጠያቂው መፍትሔ በማፈላለግ ባለው ሁኔታ እንዲቀጥል ማድረግ ይገባዋል፡፡ መገንጠልን ለሚያስነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ማስተካከል ይቻላል ወይም ቁጭ ብሎ በመወያየት መፍትሔ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ሕገ መንግሥታዊ መብት በመሆኑ መከበር እንዳለበት በሕገ መንግሥቱ ከተረጋገጠ በኋላ፣ የሚቀርበውን ጥያቄ መፈጸም እንጂ እንደገና ለውይይት መቅረብ አለበት ይላሉ?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ አንድነትን ሲቀላቀሉ ይኼ ልዩነት እንዳለዎት አሳውቀው ነው የገቡት?

ዶ/ር ነጋሶ፡- አንድነት በፕሮግራሙ አንቀጽ 1፣ 3 እና 5 ላይ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ የሚለውም ዓቢይ የፖለቲካ ጥያቄዎች የሚፈቱት በሰላማዊ፣ በዲሞክራሲያዊና በድርድር ነው ይላል፡፡

ሪፖርተር፡- ዓብይ የፖለቲካ ጥያቄዎች የሚባሉት ምንድናቸው?

ዶ/ር ነጋሶ፡- አንዱ ዓብይ ጥያቄ የብሔር ጥያቄ ነው፡፡ ማለትም ‹‹ቋንቋዬና ባህሌ ይከበርልኝ፣ ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ክፍፍል ይኑር፣ አልተመቸኝምና ልገንጠል፤›› የሚሉት ናቸው፡፡ ሌላው የመሬት ጥያቄ ነው፡፡ የፌዴራሊዝም አወቃቀርም ሌላው ዓብይ ጥያቄ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ጥሩ ነው አይደለም? ሊሻሻል ይገባዋል ወይስ አይገባውም? የኢኮኖሚ ጥያቄና የመሳሉት ዓብይ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ አንድነትም እነዚህ ጥያቄዎች በውይይት፣ በድርድር፣ በሰላምና በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፈታት እንዳለባቸው በፕሮግራሙ አስቀምጧል፡፡ ይኼ ካልተቻለ ጥያቄው ወደ ሕዝብ ይሄድና ሕዝብ ይወስናል ይላል፡፡ ባንድም በሌላም የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 እዚያ ውስጥ ተካቷል፡፡

ሪፖርተር፡- አንድነት ፓርቲ ውስጥ ከአባልነት እስከ ሊቀመንበርነት ድረስ በተለያዩ ኃላፊነቶች ሠርተዋል፡፡ በመድረክና በአንድነት መካከል የተፈጠረው ችግርና አለመግባባቶች መነሻቸው ምንድነው?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ አንደኛ የፕሮግራም ጉዳይ ነው፡፡ በፕሮግራም ጉዳይ ላይ አንድነት ባደረገው ግምገማ ያስቀመጠው ‹‹የመድረክ ፕሮግራምና የአንድነት ፕሮግራም አይስማሙም፡፡ በፍፁም አብረው ሊሠሩ የሚችሉ ድርጅቶች አይደሉም፤›› የሚል ነው፡፡ ነገር ግን መድረክ ሲቋቋምና ጥምረት ሲፈጠር ከብርቱካን ሚደቅሳ ጋር ተወያይተን ነበር፡፡ ጥምረቱ በተፈጠረበት ወቅት አንድነት ገና በመደራጀት ላይ ስለነበር በታዛቢነት እንጂ በተሳታፊነት ወይም በአባልነት መሳተፍ እንደማይችሉ ከብርቱካን ጋር ባደረግነው ውይይት ተስማምተን በታዛቢነት ተገኝተዋል፡፡ ብዙም ሳይቆዩ አባል ሆኑ፡፡ ለአንድ ዓመት በፕሮግራም ጉዳይ መድረክ ውይይት አደረገ፡፡ በአብዛኛው ላይ ተስማምተናል፡፡ ያልተስማማንባቸው የቡድን መብት ይቅደም ወይስ የግለሰብ በሚለው ላይ ነበር፡፡ ልዩነቱን በማንሳት አስታርቀነው የሁለቱንም ለማክበር ተስማማን፡፡ በአንቀጽ 39 እና በፌዴራሊዝም ጥያቄዎች ላይ ግን መስማማት አልቻልንም፡፡ በጋራ ስንወስን ‹‹በሌሎቹ ላይ ከተስማማን በተስማማነው ላይ በምርጫ ጊዜና ከምርጫ በኋላ በእሱ ላይ እንሠራለን›› በሚል ነው የተስማማነው፡፡ በምርጫ ካሸነፍንና ፓርላማ ከገባን ፓርላማ ከገቡ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የጋራ መንግሥት እንደምናቋቁም ተስማምተን ነበር፡፡ የጋራ መንግሥት፣ ሕገ መንግሥቱን የማሻሻል ሁኔታ መፍጠር፣ ሕዝብ ውሳኔዎች የሚካሄዱበትን ሁኔታ መፍጠር በሚል ነበር የተስማማነው፡፡ ጥምረት ለመፍጠር ስምምነት ላይ ከደረስን በኋላ፣ እያንዳንዱ የፖለቲካ ድርጅት መጀመሪያ በሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ከተወያየንና ወደ ጠቅላላ ጉባዔ ወስደው ካስወሰኑ በኋላ፣ ሁሉም በመድረክ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ አቅርበው ውሳኔ ላይ ተደረሰ፡፡ ጥምረቱም ተፈጠረ፡፡ በመቀጠልም በተመሳሳይ ሁኔታ ጥናትና ውይይት ከተደረገ በኋላ ስምምነት ላይ ሲደረስ ግንባሩ ተፈጠረ፡፡ ጥቂት የሕገ ደንብ ችግሮች ካልሆኑ በስተቀር ጥምረቱ እንደሚያሠራን ተስማምተን ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- አንድነት ፓርቲ ከተስማማ በኋላ ጥምረቱን በሚመለከት ለብቻው ግምገማ ላይ የተቀመጠበት ምክንያት ምንድነው?

ዶ/ር ነጋሶ፡- በአንድ በኩል እነ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ‹‹አቶ ግርማ ሰይፉ እኛን አይወክለንም›› የሚል ቅስቀሳ በመገናኛ ብዙኃን ማካሄድ ጀመሩ፡፡ አቶ ግርማም መልስ መስጠት ጀመረ፡፡ አቶ ግርማ ሰይፉ የተመረጠውና ፓርላማ የገባው በአንድነት ስም ሳይሆን በመድረክ ስም ነው፡፡ በግልም አይደለም፡፡ በፓርላማም የመድረክ ወኪል ነው፡፡ ፕሮፌሰር በየነ ደግሞ ስለአቶ ግርማ ሲጠየቁ፣ ‹‹ይኼንን የሚያውቀው ኢሕአዴግ ነው፤›› የሚል መልስ መስጠት ጀመሩ፡፡ ይኼ ደግሞ በመድረክና በአንድነት ውስጥ ቅሬታ ሲፈጥር ቆይቷል፡፡ አቶ ቡልቻ ደግሞ፣ ‹‹አንድነት የአማሮች ድርጅት ነው፤›› የሚል ቅስቀሳ ጀመሩ፡፡ መድረክ የገንዘብ እጥረት ስላለበት እንደፈለገ ተንቀሳቅሶ መስተካከል ያለባቸውን ነገሮች ማስተካከል አልቻለም፡፡ አንድነት ደግሞ በገንዘብ አቅም የተሻለ በመሆኑ ሁለቱ ድርጅቶች ተጣጥመው ሊሄዱ አልቻሉም፡፡ ሌላው የአንድነት ፖሊሲ የነበረው መድረክ ወደ ግንባር መሸጋገር ብቻ ሳይሆን ወደ ውህደት መሄድ አለበት የሚልም ቢሆንም፣ እንደተፈለገው ባለመሄዱ በአንድነት ውስጥ ቅሬታ መፈጠር ጀመረ፡፡ በመሆኑም በአንድነትና በመድረክ ውስጥ ያለውን አለመጣጣምና የተለያዩ የሚነሱ ጉዳዮችን በማጥናት የሚገመግም አንድ ኮሚቴ ተቋቋመ፡፡ ኮሚቴው ግን ሥራውን ሊሠራ አልቻለም፡፡ ሌላ ኮሚቴ እንዲቋቋም የአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት አዘዘ፡፡ በአንድ ወር ውስጥ አጥንቶ እንዲያቀርብ በታዘዘው መሠረት ኮሚቴው ባደረገው ጥናት፣ ‹‹አንድነትና መድረክ አብረው ሊሄዱ የሚችሉ ድርጅቶች አለመሆናቸውንና ከመድረክ ወደ ጥምረት ከዚያም ወደ ግንባር የተደረገው አካሄድ ትክክል አይደለም፡፡ ይኼንንም ያደረጉት መሪዎች ናቸው፤›› የሚል ሐሳብ በኮሚቴው የግምገማ ውጤት ላይ ተቀምጧል፡፡ ምክር ቤቱ ሲቀበለው ጥቂቶች እኔን ጨምሮ ተቃውሞ አቅርበን ነበር፡፡ ምክንያታችንም ሁሉም ነገር የተፈጸመው ተስማምተን ነበር፡፡ አካሄዱም የመሪዎች ውሳኔ ሳይሆን በየደረጃው ውይይት ተደርጎበት ውሳኔ ያገኘ መሆኑን ተናገርን፡፡ አብዛኛዎቹ በመደገፋቸው የእኛ ተቃውሞ ውጤት አልነበረውም፡፡ ያም ቢሆን ግን የብሔራዊ ምክር ቤቱ ውሳኔ ወደ መድረክ ተልኮ በልዩነቶቹ ላይ ውይይት መደረግ ሲገባው፣ ውይይቱና ውሳኔው እንዲሁም ግምገማው በመገናኛ ብዙኃን ተገለጸ፡፡ ይኼንንም ያደረጉት አቶ ሀብታሙ አያሌውና የብሔራዊ ምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ዘካርያስ የማነ ብርሃን ናቸው፡፡ የሚገርመው ነገር ብሔራዊ ምክር ቤቱ አሻሻልኩ ያለው ሰነድ ለሥራ አስፈጻሚው (ለእኔ) ቀድሞ መድረስ ሲገባው በመገናኛ ብዙኃን ከተገለጸ በኋላ በሳምንቱ ነው የደረሰኝ፡፡ በዚህ ጊዜ አካሄዱ ትክክል አለመሆኑን በመግለጽ ደብዳቤ ጻፍኩኝ፡፡ ምላሽ ሊሰጡኝ ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ተስማምተን አብረን ያፀደቅነውን ፕሮግራም ከመካዳቸውም በተጨማሪ፣ ወደ መድረክ ሄዶ ውይይት ተደርጎበት ውሳኔ ላይ ካልተደረሰ ወድ ጉባዔው ተመልሶ ለውይይት መቅረብ ሲገባው ወደ መገናኛ ብዙኃን እንዴት ይላካል? በሚለውና በሌሎችም ተጨማሪ ምክንያቶች ልለቅ ችያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- አንድነት ምክንያቶችን ፈጥሮ ከመድረክ ጋር የነበረውን ስምምነት ለመቀልበስ ያስገደደው ምክንያት ምንድነው ይላሉ?

ዶ/ር ነጋሶ፡- በአንድነት ውስጥ ሁለት አቅጣጫዎች ነበሩ፡፡ አንደኛው አቅጣጫ መድረክ ካልተዋሀደ በግንባርነት አጠናክረነው እንሥራ የሚል ሲሆን፣ ሌላኛው አሁን መጨረሻ ላይ እንደታየው ከመጀመሪያው ሳያምኑበት የገቡበት ሁኔታ ያለ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- አንድነት ፓርቲ ውስጥ የኢሕአዴግ አባል የሆኑ ግለሰቦች በአባልነት ተካተው የድርጅቱን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴና የውስጥ አሠራር በማጥናት፣ አፍራሽ የሆነ ሐሳብ በማቅረብ፣ አቅጣጫ በማስቀየርና ፓርቲው እንዳሰበው እንዳይራመድ የሚያደርጉ አሉ ተብሎ ይናፈሳል፡፡ ምላሽዎ ምንድነው?

ዶ/ር ነጋሶ፡- በእርግጥ ተነጋግረንበት አናውቅም፡፡ በአንድነት የአምስት ዓመት ስትራቴጂ መጽሐፍ ውስጥ አንድ ነገር አለ፡፡ አንድነት የተበታተኑ ፓርቲዎችን አሰባስቦ አንድ ፓርቲ የማድረጊያ ማዕከል መሆን እንዳለበት በመጽሐፉ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ ምናልባት አሁን እያደረገ ያለው ነገር ከዚያ ጋር ተያይዞ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ኢሕአዴግ ግን ይህንን ያደርጋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ አንድ የገረመኝና ያስደነገጠኝን ነገር ልንገርህ፡፡ ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ለተወሰነ ጊዜ ጠፍቶ ነበር፡፡ አንድነት ግምገማውን ባደረገበት ቀን ግን ተገኝቶ ነበር፡፡ ‹‹አንድነትን ወደ መድረክ ያስገባሁት እኔ ነኝ፡፡ አሁን ደግሞ የመጣሁት ከመድረክ ላስወጣው ነው፡፡ ከመድረክ ጋር ውህደት መፍጠር የማይቻል ከሆነ ጊዜ ማጥፋት አያስፈልግም፤›› ብሎ ተናገረ፡፡ ኢሕአዴግ ፓርቲዎች ቢበታተኑ፣ ቢሰባበሩና ቢሰነጣጠቁ ደስ ይለዋል፡፡ አንተ በጥያቄህ ያነሳኸውን አያደርግም ለማለት አይቻልም፡፡ ግን ማስረጃ የለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ሕዝብ ማወቅ አለበት የሚሉት የአንድነት ችግር ምንድነው?

ዶ/ር ነጋሶ፡- የአንድነት ፓርቲ ዋናው ችግር ካልተዋሀድን በስተቀር አብረን መሥራት አንችልም የሚለው አካሄዱ ትክክል አይደለም፡፡ ሕዝቡ ብዙ ጊዜ የሚያነሳው ጥያቄ አለ፡፡ ‹‹ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ›› የሚል ጥያቄ ነው፡፡ ‹‹አንድ ሁኑ›› ይባላል፡፡ እንዴት ተደርጎ ነው በአንድ ጊዜ መዋሀድ የሚቻለው? ፍቅር እንኳን ቀስ ብሎ በመላመድ ነው ወደ ትዳር የሚያመራው፡፡ ሁሉም ነገር በሒደት ነው፡፡ የአንድነት ፓርቲ ‹‹ውህደት እንጂ ግንባር አያስኬድም›› የሚለው ዋናው ችግር ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የኦነግ አመራር የነበሩት አቶ ሌንጮ ለታ አዲስ ፓርቲ ይዘው በመጪው ምርጫ ላይ ለውድድር እንደሚቀርቡ እየተነገረ ነው፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?

ዶ/ር ነጋሶ፡- የኦነግ ፕሮግራም የወጣው መስከረም 1966 ዓ.ም. ነው፡፡ በ1968 ዓ.ም. ደግሞ ተሻሽሎ የኦሮሚያ ሪፐብሊክን እናቋቁማለን አለ፡፡ ርዕዮተ አለሙ ከቻይናና ከሻዕቢያ ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ በ1983 ዓ.ም. የሽግግር መንግሥት በሚመሠረትበት ጊዜ ሁለት ቦታ ተከፍሎ ነበር፡፡ አንደኛው ወገን የእነ ሌንጮ ሲሆን ‹‹ቻርተሩን ተቀብለን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንመሥርት›› የሚለው ነው፡፡ ሌንጮ በኋላም የቀጠለበት ይመስለኛል፡፡ ከመለስ ጋርም ብዙ ግንኙነት እንደነበራቸው ይወራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ኢንዲፔንደንት ኦሮሚያ ሪፐብሊክን እናቋቁማለን›› (ነፃ ኦሮሚያ ሪፐብሊክን እናቋቁማለን) የሚል ቡድን ነበር፡፡ ወደ ሽግግር መንግሥቱ ሲገቡ ሰፊው የኦነግ አባል አንዳንድ አመራሮችን ጨምሮ ቻርተሩን ተቀብለን ቀስ በቀስ ‹‹ኢንዲፔንደንት ኦሮሚያ ሪፐብሊክ እንመሠርታለን›› የሚል አቅጣጫ ይዘው ስለነበር ሊመጡ ችለዋል፡፡ እነ ሌንጮ ግን ‹‹ኢንዲፔንደንት ኦሮሚያ ሪፐብሊክ›› የሚለው እንደማያዋጣ በመገንዘባቸው ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንገንባ የሚለውን የቀጠሉ ይመስለኛል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄም መልስ የሚያገኘው በዚህ ነው በማለቱ ይመስለኛል ሌንጮ ከኦነግ አመራር የተባረረው፡፡ በውጭ አገር በተለያዩ ከተሞች ሲወያዩ ቆይተው የኦሮሚያ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) የሚለውን ድርጅት መመሥረታቸውን አውቃለሁ፡፡ የእኔ ጥያቄ ድሮም ቢሆን ዴሞክራሲ ይሻላል፣ ሰብዓዊ መብት ይከበር የሚል ነበር፡፡ በመሆኑም እነ ሌንጮ ለታ ዴሞክራሲን የተከተለ መንገድ አስበው ከመጡ ጥሩ ነው፡፡ በኦነግ ስም ብዙ ሰው ተጎድቷል፡፡ ሕዝቡ ጦርነት ሰልችቶታል፡፡ በሰላም መኖር ነው የሚፈልገው፡፡ በዴሞክራሲ አቋም መምጣታቸው ጥሩ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ዶ/ር ነጋሶ ፖለቲካ በቃኝ በማለት አንድነትን የለቀቁት የአቶ ሌንጮ ልዩ አማካሪ ሆነው ለመሥራት ተስማምተው ነው ይባላል፡፡

ዶ/ር ነጋሶ፡- ሌንጮን ያገኘሁት ከሦስት ዓመት በፊት አንድነት ፓርቲ ስዊድን ጋብዞኝ ሄጄ ነበር፡፡ ከዚያ ስመለስ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ማኅበር ጋብዞኝ ኖርዌይ ሄድኩኝ፡፡ ሌንጮ የሚኖረው እዚያ ነበር፡፡ የሥጋ ዘመዴ በመሆኑ ደውዬ አግኝቼዋለሁ፡፡ ግን ከዘመድ አዝማድ ጥያቄ ውጪ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ውይይት አላደረግንም፡፡ ከዚያ በፊት ግን እኔ ፓርላማ እያለሁ በኢሜይል እንገናኝ ነበር፡፡ መለስ ከልክሎት ነው መሰለኝ አቋርጦ ጠፋ፡፡ ምንም ዓይነት ግንኙነት የለንም፡፡ እንዲያውም ሰሞኑን አንድ ሚዲያና ዶ/ር መረራ ደውለው ‹‹ሌንጮ መጥቷል ይባላል እውነት ነው?›› ብለው ጠየቁኝ፡፡ እንዳልሰማሁና ከነሱ መስማቴን ከመግለጽ ውጪ ምንም ዓይነት ግንኙነት የለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ሙሉ ለሙሉ ከፖለቲካ ራስዎን አገለሉ ማለት ነው?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ከድርጅታዊ የፖለቲካ ተሳትፎ ሙሉ በሙሉ ራሴን አግልያለሁ፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው በምንም ሁኔታ ራሱን ከፖለቲካ ነፃ ማድረግ ስለማይችል፣ እኔም በተለያዩ ጉዳዮች የግል አስተያየቴን (ትችትም ይሁን ድጋፍ) መሰንዘሬ አይቀርም፡፡