የጀመርነው ህዝባዊ ንቅናቄ ለትግሉ ፅናታችንን፣ ለወኪሎቻችን ታማኝነታችንን ማረጋገጫ ነው!

የጀመርነው ህዝባዊ ንቅናቄ ለትግሉ ፅናታችንን፣ ለወኪሎቻችን ታማኝነታችንን ማረጋገጫ ነው!
እሁድ ጥር 18/2006

በ ‹‹730 ቀናት ለሃይማኖት ነፃነት›› ህዝባዊ ንቅናቄ ጅማሮ በሃገራችን አራቱም አቅጣጫ የሰላማዊ ትግላችን ማዕከላት የሆኑት መስጂዶች እንደትግሉ ጅማሮ ወኔ በታጠቁ አማኞች ዙሪያቸው ተጥለቅልቆ ነበር፡፡ የትናንት ወዲያው ጁሙዓ በ2004 በረመዳን ዋዜማ እንደነበሩት ግዙፍ ድምፅ አልባ ተቃውሞዎች ታለቅ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

በአሁኑ ጁሙዓ እና በረመዳን ዋዜማ የነበሩቱን አንድ የሚያደርጓቸው ወሳኝ ነጥቦች አሉ፡፡ የረመዳኑ ዋዜማ አስደማሚ ድምፅ አልባ ተቃውሞዎች መንግስት ሰላማዊ ትግላችንን ለወራት ባወደሰበት ሚዲያው እና ባለስልጣናቱ ‹‹የሽብር እንቅስቃሴ›› ሲል የሀሰት ስም የለጠፈበት፣ ኮሚቴዎቻችንን የማሰር ፖለቲካዊ ውሳኔ ተላልፎ ከፍተኛ ውጥረት የነገሰበትና የኮሚቴዎቻችን መታሰርም እውን እንደሚሆን ሁሉም የተረዳበት፣ ህጋዊ ወኪሎቻችን በማንኛውም ቅፅበት እጃቸውን ለካቴና፣ ወገባቸውን ለበዳዮች ዱላ እያመቻቹ እኛን ግን በፅናት እና በሰላማዊነት ላይ ‹‹አደራ! አደራ!›› ያሉብን ታሪካዊ ወቅት ነበር፡፡ ትግላችንም እኛም በፅኑ የምንፈተንበት ጊዜ ነበር፡፡ የህዝበ ሙስሊሙ የወቅቱ ጀግንነት እና ወኔ ይህንን ፈተና በሚገባ ተሻግሮ ትግሉን ለማስቀጠል ትልቅ ዋስትና የሰጠ ነበር፡፡ በእርግጥም የሁለት አመት ትግላችንን በምናስብበት በዚህ ወቅት በዚያ የረመዳን ዋዜማ ላይ በአስደናቂ ህዝባዊ ወኔ የተሳተፉ ሁሉ ተገቢውን ክብር ሊቸራቸው ይገባል፡፡

አሁን የምናደርገው ህዝባዊ ንቅናቄ ደግሞ መንግስት ‹‹በእምነቴ ጣልቃ አትግባ!›› ስላለ ብቻ መላው ሙስሊም ላይ እንዳሻው በሚዘውረው ፍርድ ቤቱ ‹‹ሽብርተኛ›› ሲል የጥፋተኝነት ውሳኔ ባስተላለፈበት ማግስት የሚካሄድ ነው፡፡ ውድ ኮሚቴዎቻችንም ለወራት የደረሰባቸውን ግፍ እና መከራ ቃል በቃል በመግለጫቸው አስተላልፈውልናል፡፡ ከዚህ በኋላ የሚተላለፍባቸው የፖለቲካ ውሳኔ ምን እንደሆነ ሳያስጨንቃቸው በዚህ ስቃይ ውስጥ አልፈው፣ ፅናት ተላብሰው በፅናት እና ሰላማዊነት ላይ የጠበቀ አደራ በመግለጫቸው አስተላልፈውልናል፡፡ የጁሙዓው ሃገር አቀፍ ንቅናቄ እና አለም አቀፍ መርሃ ግብሮች ለሰላማዊ ትግላችን ያለን ፅናት እና ለወኪሎቻችንን ያለን ታማኝነት ዳግም የተረጋገጠበት ሌላ ታሪካዊ ወቅት ነው፡፡ አሁንም በዚህ ወሳኝ ወቅት ለትግሉ ባለቤት መላው ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ክብር ሊቸረው ይገባል፡፡

በእርግጥ ህዝበ ሙስሊሙ ለሰላማዊ ትግሉ ያለው ቁርጠኝነት ፈፅሞ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ነገር ግን በትናንቱ ጁሙዓ ድምፅ አልባነቱን ጥሶ የተስተጋባው ትልቁ መልእክት መጪው ጊዜ ካለፉት የተሻለ አንድነት የሚጠይቅ እና ከመቼውም የበለጠ ለድል የቀረበ እንደሆነ ነው፡፡ በሰላማዊ ትግል ውስጥ ህዝቡ ሊያልፍባቸው የሚገቡ እርከኖችን በሙሉ እየተሻገረ በመጣ ቁጥር የመጨረሻው የድል በር ላይ ለመድረሱ ማረጋገጫ መሆኑ ነው፡፡ በሰላማውያን እና ሰላማዊነት በማይዋጥላቸው አካላት መካከል ያለው ትልቁ ልዩነት ይህ ነው፡፡ ሰላማውያን ከእነርሱ የሚጠበቀውን ሁሉ እያሟሉ በማለፋቸው እና ረጅም ርቀት በመጓዛቸው ለድላቸው ፍሬ ይበልጥ መብሰል ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በተቃራኒው ያሉ አካላት ሰላማዊ የመብት ታጋዮች የሚያልፏቸውን የትግል እርከኖች ያመከኑ ሲመስላቸው ታጋዮችን ሌላ መፈናፈኛ እያሳጡ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ የሰላማዊ ትግል ሂደት መራዘምም ‹‹ታጋዮችን ከመንገድ ያስቀራል›› ብለው ያስባሉ፡፡ የትናንቱ ጁሙዓ ህዝባዊ ወኔ ይህንን ደካማ አስተሳሰብ ሰብሮ ማለፍ የሚያስችል አቅም አሳይቷል፡፡

በሰላማዊ ትግላችን ማለፍ የሚጠበቅብንን እርከን እየቆጠርን እያለፍን ነው፡፡ ያለፉት ሂደቶች አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት፣ እየተባሉ የሚታለፉ የትግል ሂደቶች ነበሩ፡፡ መጪዎቹ ሂደቶች ግን ተቆጥረው የሚያልፉ ሳይሆን በዚያው ላይ ፅኑ በመሆን ድልን ሳይጨብጡ የማይታለፍባቸው ጊዚያት ሊሆኑ እንደሚገባ አመላካች ነገሮች አሉ፡፡ የትናንቱ ጁሙዓ ደግሞ ለዚህ ትልቁን መሰረት የጣለ ነው፡፡ በትናንቱ ጁሙዓ ጠንካራ መልእክት የተላለፈላቸው ውስጣዊም ውጫዊም ሃይሎች ነበሩ፡፡ በዋናነትም በእፎይታ ጊዜ ውስጥ መሆናችንን ተገን በማድረግ መንግስት እና የመንግስትን ፀረ አንድነት ፖሊሲ የሚያራምዱ አካላት ሜዳውን እንዳሻቸው ሲጠቀሙበት ቆይተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ግን ህዝበ ሙስሊሙን ያስተሳሰረውን የአንድነት እና የፅናት ገመድ ሊፈታው አልቻለም፡፡ የትናንቱ ጁሙዓ የዚህ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ ሰላማዊ ትግላችን በማይዋዥቅ ፅናት እና በማይበጠስ አንድነት ላይ እንደተገነባ እስከድል በር ይደርሳል፤ ኢንሻአላህ!!!

ለትግሉ ፅናታችንን፣ ለወኪሎቻችንን ታማኝነታችንን ሁሌም እናረጋግጣለን!

ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!

Like ☑ Comment ☑ Share ☑

ይሄን ሊንክ ጠቅ አድርገው ይከተሉና አዲሱን የፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ!
https://www.facebook.com/DimtsachinYisema2

ይህኛውን ሊንክ ጠቅ በማድረግ ደግሞ መደበኛውን ድረ ገጻችንን መጎብኘት ይችላሉ!
http://www.dimtsachinyisema.info/