የዩክሬን አውሮፕላን አዲስ አበባ አቅራቢያ ተከሰከሰ
ከኡጋንዳ ኢንቴቤ ተነስቶ ወደ ሰንዓ የመን በመብረር ላይ የነበረ ንብረትነቱ የዩክሬን የሆነ አንቶኖቭ 28 የመንገደኞች አውሮፕላን ባለፈው ሰኞ አዲስ አበባ አቅራቢያ ለገዳዲ አካባቢ ተከሰከሰ፡፡
ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ የአውሮፕላኑ አብራሪዎች ሰኞ ማለዳ ከባለሥልጣኑ ጋር ባደረጉት የሬዲዮ ግንኙነት ከኢንቴቤ ተነስተው በኢትዮጵያ በኩል ወደ የመን ለመብረር ፈቃድ ጠይቀው ነበር፡፡ ባለሥልጣኑም የበረራ ፈቃድ ሰጥቷቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ኤር ናቪጌሽን ክፍል ለአብራሪዎቹ የሚበሩበትን ከፍታ ሰጥቷቸዋል፡፡ አውሮፕላኑ የኢትዮጵያን አየር ክልል አቋርጦ በማለፍ ላይ ሳለ አዲስ አበባ አካባቢ ሲደርስ የሞተር ብልሽት ያጋጥመዋል፡፡ ይህንኑ ለአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የበረራ መቆጣጠሪያ ማማ አሳውቆ ‹‹ኢመርጀንሲ ላንዲንግ›› እንደሚያደርግ (በድንገተኝነት እንደሚያርፍ) ሪፖርት አድርጐ፣ ከጠዋቱ 3፡35 ሰዓት ላይ ለማረፍ ወደ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በማምራት ላይ ሳለ ለገዳዲ አካባቢ ተከስክሷል፡፡
አደጋው እንደደረሰ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ፈልጐ ማዳን ቡድን ወደ ሥፍራው ተንቀሳቅሶ የአውሮፕላኑ አብራሪዎችን ወደ ሆስፒታል በመውሰድ ሕክምና እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ በአውሮፕላኑ ውስጥ ተሳፋሪዎች እንዳልነበሩ ታውቋል፡፡ በአደጋው አብራሪዎቹ የተጐዱ ቢሆንም፣ ሕይወቱ ያለፈ ሰው እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአውሮፕላን አደጋ መከላከልና ምርመራ ክፍል ባለሙያዎች የአደጋውን መንስዔ ለማወቅ ምርመራ ጀምረዋል፡፡ ባለሙያዎቹ አውሮፕላኑ ወደ ወደቀበት ሥፍራ በማምራት መረጃ በማሰባሰብ ላይ ይገኛሉ፡፡
ሩሲያ ሰራሽ የሆኑ አንቶኖቭ አውሮፕላኖች ከተመረቱ ረዥም ጊዜ ያስቆጠሩ በመሆኑ በየጊዜው እክል እየገጠማቸው በተለያዩ አገሮች በመከስከስ ይታወቃሉ፡፡ እነዚህ ዕድሜ ጠገብ አውሮፕላኖች ዋጋቸው ርካሽ በመሆኑ በአፍሪካ አገሮች በብዛት ይገኛሉ፡፡ ያረጁ በመሆኑና ተገቢ የሆነ ጥገና ስለማይደረግላቸው በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በተደጋጋሚ አደጋ እንደሚያደርሱ የአቪዬሽን ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ Reporter