በፍራቻ የተዋጡ የመንግስት ሰራተኞች
በፍራቻ የተዋጡ የመንግስት ሰራተኞች = የፍትህ ያለህ ….
ጥቅማ ጥቅምን ሽፋን አድርጎ የመንግስት እና የፓርቲ ስራ ደባልቆ መስራት ከባድ አደጋ አለው::
መርዛማዊ ሃይል ያዘለ የፖለቲካ መስፋፋት የመንግስት ሰራተኛውን የመስራት እንዲሁም የመኖር ህልውና አደጋ ውስጥ ከቶታል::
ምንሊክ ሳልሳዊ :- በኢያንዳንዱ የመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ ሁሉንም ፖለቲካኛ የማድረግ እና ለፖለቲካ ፍጆታው ለመጠቀም የሚፈልገው ሕወሓት መራሹ መንግስት ህገመንግስታዊ የዜጎችን የመስራት/ሰርቶ የመኖር መብት እየደፈጠጠ ነው:: በኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው የከተማው ነዋሪ በመንግስት ስራ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል:; ይህ ዜጋ በተለያዩ አስተሳሰቦች እና እምነቶች የራሱ በሆነ ሂደት ውስጥ የሚጓዝ መሆኑ የማይካድ ሃቅ ነው::በተለያዩ ጊዜያት የተፈራረቁ መንግስታት ኢላማ የሆነው የመንግስት ሰራተኛው ዛሬም የፍትህ ያለህ የነጻነት ያለህ በማለት ላይ ነው::
በየትኛውም የአለም ክፍል ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ የሚያገለግለው ለቀጠረው ህዝባዊ አካል ሲሆን በመንግስት ሰራተኛው መሃል የተላያዩ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ድጋፎች እና ተቃውሞዎች የመኖራቸውን ያህል ለፖለቲካ ግድ እስከሌለው ጀምሮ ፖለቲካ መስማት እስከማይፈልጉ እና ስራቸው ላይ ብቻ ማተኮር የሚፈልጉም ዜጎች አሉ :: ይህ ደሞ ህገመንግስታዊ መብታቸው እስከሆነ ድረስ ሊከበርላቸው ይገባል::
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው መርዛማዊ ሃይል ያዘለ የፖለቲካ መስፋፋት የመንግስት ሰራተኛውን የመስራት እንዲሁም የመኖር ህልውና አደጋ ውስጥ ከቶታል::ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ አለም አቀፍ የሰብኣዊ መብት ድርጅቶችም ይህንን በመንግስት ሰራተኞች ላይ የሚፈጸመውን በመስራት/በመኖር ላይ ያነጣጠረ ደባ አሳሳቢነት በይፋ ገልጸዋል::ከመንግስታዊ ጥቅማ ጥቅምም እንዲታገዱ እየተደረገ እንደሆነም ጩኸታችንን አሰምተናል::መንግስት ስንል ህዝብ ማለታችን መሆኑን ይገንዘቡልን..መንግስት የሚለው ቃል ወያኔን አይወክልም::
ወያኔ በህዝቦች ላይ የሚያራምደው አደገኛ የአገዛዝ ስልት የሚመለከቱ አብዛኛዎች የፓርቲው አባላት እና ካድሬዎች የትግል ቁርጠኝነታቸው ከመላሸቁም ሌላ ከፓርቲ ስራዎች ይልቅ በጥቅማዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮራቸው ያሳሰበው ወያኔ አንድ ለአምስት በሚባል አደረጃጀት የፓርቲውን ስራ ከመንግስት ስራ ጋር ጎን ለጎን ለመተግበር ደፋ ቀና በማለት የዜጎችን ህልውና አደጋ ውስጥ ጥሎታል::የወያኔን ድርጅታዊ ስራ ከመንግስት ስራዎች ጋር ቀይጦ ለመተግበር መሞከር አደጋው ወደማይወጡበት አዘቅት ሊከት እንደሚችል መታወቅ አለበት ::
ወያኔ የስልጣን ጊዜውን ለማስረዘም ብቻ በሚያደርገው መፍጨርጨር በህዝብ እና በሃገር ላይ ሊመጡ የሚችሉትን አደገኛ እንቅፋቶች ከግንዛቤ አለማስገባቱ በላይ ማንጫውን ዜጋ ህዝብን በሚያገለግልበት የመንግስት ስራዎች ላይ መፈጸም የሚገባውን እንዳይፈጽም እና በድርጅታዊ ስራ ስፋን ለቢሮክራሲ ለሙስና ለህዝቦች እንባ በር መክፈት መሆኑን ልብ አለማለቱ የወያኔ ዝቅጠት ገሃድ አድርጎታል::
በልማት ስም እየተፈጸሙ ያሉት ደባዎች እና ሴራዎች አልበቃ ብሎት በኢኮኖሚ ድቀት እየተንገፈገፍ ያለን ህዝብ በድርጅታዊ ስራ ለመወጠር ማሰብ የፈነዳ እለት የሚያስከትለውን ችግር ማንም ሊወጣው እንደማይችል ለማረጋገጥ እንወዳለን ስለዚህ በመንግስት ሰራተኞች ዙሪያ እየተካሄደ ያለው እሽክርክሪት ሊታሰብበት ይገባል::