‹‹ተጠያቂው መለስ ዜናዊ ነው!››
ምንሊክ ሳልሳዊ…ትናንትና ማታም ኢቲቪ ስለ አቶ መለስ ዜናዊ የተመሰከረውን ቆረጠው፡፡ ያ በ1984 ቤተሰቦቻቸውን ያጡትና አሳዛኝ ሰውዬ ትናንትናም በኢቲቪው ዶክመንተሪ እያለቀሱ ታዩ፡፡ እነ ዶክተር መረራ ጊዲና፣ ፕሮፌሰር መስፍን፣ ኢንጅነር ይልቃል፣ ግርማ ሰይፉ በሽብርተኝነት ስም መንግስት እያሸበረን ነው በማለታቸው ተብጠልጥለዋል፡፡
በሌላ በኩል ያ መከረኛ ሰውዬ የሰጡት ምስክርነት አሁንም ተቆርጧል፡፡ ባይቆረጥ ኖሮ ሰውየው ‹‹ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው መለስ ዜናዊ ነው!›› ነበር የሚሉት፡፡ ማን ይናገር የነበረ ቢሆንም የአሁኖቹ ወጣት የኢቲቪ ካድሬዎች ግን ቆርጠውታል፡፡ አዎ! ኢቲቪ አሁንም ዳግመኛ ቆረጠው፡፡ በእነ ዶክተር መረራና በእነ ፕሮፌሰር መስፍን ላይ ደግሞ የሌለውን መረጃ ቆርጦ ቀጥሏል፡፡ እነ አንዱ ዓለም አራጌ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ እስክንድር ነጋ፣ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው ይህን ነው የሚባል ምስክር ሳይቀርብባቸው እስር ቤት ውስጥ ታጉረዋል፡፡ ቤተሰባቸው ላይ ማን ጥቃት እንዳደረሰ፣ ማን ተጠያቂ እንደሆነ የተመሰከባቸው አቶ መለስ ግን ምስክርነቱ ተቆረጠላቸው፡፡ እነ አንዱ ዓለም አራጌ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ እስክንድር ነጋ፣ መፍትሄ አፈላላጊ እንዲህ እያለቀሰ ‹‹ቤተሰቦቼን ፈጁብኝ! ለዚህ ሁሉ ተጠያቂዎቹ እነሱ ናቸው›› የሚል ቢገኝ መስካሪው ካለው ባሻገር ሆድ አደር ‹‹ተንታኞችና ተመራማሪዎች፣ ጋዜጠኞች›› ለጥጠው፣ ጨምረውበት ስንት ሰቅጣጭ ፊልም ይሰራበት ነበር፡፡
አንዳንዴ ሳስበው ካድሬዎቹና ኢቲቪ (ያው ካድሬ ነው) አቶ መለስን ከአምላክ በላይ ይፈሯቸዋል/ያከብሯቸዋል፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ መጽሃፉ፣ የእምነት አባቶች እግዚያብሄር ሰውን በውሃም ሆነ በሌላ ነገር ማጥፋቱን አይደብቁም፡፡ እስኪ ስለ ይሁዳም ሆነ ሌላ ከየትኛውም መላክ በተቃራኒ ስለሚገኙት አካላት የምታወቁ ንገሩኝ? ተከታዮቹ ጥፋታቸውን ይደብቁላቸዋል እንዴ?
ምስክር ምስክር ነው፡፡ ደግሞም ከኢቲቪ፣ ከኢህአዴግ፣ ከአቶ መለስ ይልቅ ዶክተር መረራ፣ ፕሮፌሰር መስፍን፣ ኢንጅነር ይልቃል፣ ግርማ ሰይፉ ያሉትን አምነዋለሁ፡፡ ምክንያቱም እነ አንዱ ዓለም፣ አቡበክር፣ እስክንድር፣ ርዕዮት ሳይሆኑ የሚያስሸብሩን ካድሬዎቹ፣ ባለስልጣናቱ፣ ኢህአዴግ፣ ኢቲቪም ናቸው፡፡
ያን መከረኛ ሰውዬ ደግሞ ከምንም በላይ አምናቸዋለሁ፡፡ እንዴት አልመናቸው? እሳቸው ስለ ሽብር ሲያወሩ በቅርብ ስለሚያውቋቸው ቤተሰቦቻቸው ጭፍጨፋ እንጅ ስለ ስልጣን አይደለም፡፡ እናም ኢቲቪ የቆረጠውን እኔም አልቆርትባቸውም፡፡ ልክ ነዎት! ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው መለስ ዜናዊ ነው፡፡ ኦነግ ፈጸመው ለተባለው ብቻ ሳይሆን አሁንም ድረስ ቤተሰቦቻቸው እንዳያዩዋቸው ተደርገው ጨለማ ቤት ውስጥ ለሚታጎሩት ሰላማዊ ታጋዮች፤ ኑሮ፣ ካድሬ፣ የመለስ ራዕይ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ የአቅርቦት እጥረት……ለሚያሸብረው የኢትዮጵያ ህዝብ ተጠያቂው፤ ሽብርተኝነትን በመንግስት ደረጃ አዋቅረው ያለፉት አቶ መለስ ናቸው፡፡ የፈለጋችሁ ሙት ወቀሽ በሉኝ፡፡ ይህን የአቶ መለስ ‹‹ሌጋሲ›› አልረሳውም፡፡ ቢያንስ ኢህአዴግ ራሱ አምኖ ‹‹ተሳስተን ነበር፡፡ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው መለስ ዜናዊ ነው፡፡ እኛም ሆድ አደር ሆነን አብረን አጥፍተናልና ተጠያቂዎች ነን›› እስኪል ድረስ!