ጭፈራ የመብራት፣ የስራ፣ የትምህርት፣ የቤት…ችግርን ቢፈታ… ጭፈራ ጭፈራ ነው፡፡ የሞቅታ፣ የስካር፣ የማወናበጃ፣……

እነሆ ባለ ስልጣናት፣ ‹‹ልማታዊ›› አርቲስቶችና የፓርቲው የኪነት አባላት ሲጨፍሩ ሰነበቱ፡፡ ራሳቸውን ‹‹ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች›› ብለው ጠርተው፣ ኢትዮጵያንም ወክለው፡፡ በእርግጥ እነዚህ ሰዎች አብረው መጨፈር መቻላቸው ራሱ አንድ ነገር ነው፡፡ ባለፉት 23 አመታት የተነዛው ጥላቻ በገንዘብና በሆድ አደርነት የሚሸፈንም አልነበረም፡፡ እንደ ቅስቀሳው ብዛት ካድሬዎች፣ የኪነት ቡድኑ አባላትና ‹‹ልማታዊ›› አርቲስቶች እርስ በእርሳቸው አለመተራረዳቸውም አንድ ነገር ነው፡፡ ችግሩ ከጭፈራ ያለፈ አለመሆኑ ነው፡፡ ጭፈራ ችግር ቢፈታ ኖሮ በአንድ ስታዲየም ውስጥ የተገኙት ፖለቲከኞች፣ የኪነት ቡድንና ‹‹የጥበብ›› ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን 90 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን አሸሸ ገዳሜ ከማለት ወደኋላ አይሉም ነበር፡፡ ጭፈራ ችግራችን ቢቀርፍልን ኖሮ!

ይህ የአንድ ቀን ‹‹የብሄር ብሄረሰቦች›› ጭፈራ ዳቦ መሆን ቢችል ኖሮ የባለስልጣን መኪናዎች በክረምት ጭቃ፣ በበጋ አባራ አልብሰዋቸው የሚያልፉት የጎዳና ተዳዳሪዎች በባዶ ሆዳቸው፣ በጎስቋላው አካላቸውም ቢሆን ለአንድ ቀን ይቅርና አመቱን ዳሌያቸውን መወዝወዝ ባልከበዳቸው፡፡

እውን ጭፈራ ለኢትዮጵያውያን ችግር መፍትሄ መስጠት ቢችል ሳውዲ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ዚምባብዌ፣ ኢትዮጵያም፣ ማዕከላዊ፣ ቂሊንጦ፣ ጉራፈርዳ፣ ኦጋዴን…… ውስጥ ከመሰቃየት ልክ እንደ ስፖርት ጧት ጧት፣ ልክ እንደ ምግብ ወይንም ክኒን በቀን ሁለት ወይንም ሶስት ጊዜ ቅስቀሳ፣ ዝግጅት፣ ወጭ……ሳያስፈልገን ሚሊዮን ሆነን ከመጨፈር ባልሰነፍን!

ጭፈራ ውሃ ቢሆን ህጻናትና አዛውንቶች አሁን ጀሪካን የሚያጎብጠውን ወገባቸውን ‹‹ለብሄር ብሄረሰቦች ቀን›› ባልለገሙ፡፡ ጭፈራ የመብራት፣ የስራ፣ የትምህርት፣ የቤት…ችግርን ቢፈታ… የህዝቡስ የህዝብ ነው፡፡ ብሄርን፣ ብሄረሰብንና ህዝብን ወክለናል የሚሉትን ተለጣፊ ፓርቲዎች ጭፈራ ከህወሓት ተመጣጣኝ ስልጣን የሚሰጣቸው ቢሆን ኖሮ ባለፈው 23 አመታት የጨፈሩት የትራንስፖርትና የሴቶች ጉዳይን እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲቆጥሩ ባልቆዩ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ከደብረጽዮን ስድብ፣ ከስብሃት ነጋ ቅብጠት፣ ከአባይ ጸሃዬ ግልምጫ፣ ከመለስ የሙት መንፈስ.. ቢገላግላቸው ምንም ፈቀቅ ሳይል ከነጎደው የእድገቱና… ይልቅ በጭፈራ ትራንስፎርሜሽን ወገባቸውን መቆራረጣቸው ባልከፋ፡፡

እውን ጭፈራ ለህዝብ ስልጣን መፍትሄ ቢሆን ኖሮ እነ ታማኝ በየነም በባዕዳ አገር ከመንከራተት ይልቅ ጅጅጋ ይቀርባቸው ነበር፡፡ ታማኝ እንኳ ወጣት ነው፡፡ አርጅተውም ስለ ህዝብ ስልጣን፣ ስለ ፖለቲከኞች ችግር መናገር ያላቆሙት እነ ዶክተር ሀይሉ፣ እነ ፕሮፌሰር መስፍን፣ አስግደ፣……. ሰሚ ካጣ ጩኸት የአንድና ሁለት ቀን ሆታ፣ ጭፈራና ፌሽታ ሊከብዳቸው አይችልም፡፡ ግን ምን ያደርጋል? ጭፈራ ጭፈራ ነው፡፡ የሞቅታ፣ የስካር፣ የማወናበጃ፣……