የእፎይታ ጊዜው የኮሚቴዎቻችንን የፍርድ ቤት ውጤት ተምርኩዞ እንደሚያበቃ ድምፃችን ይሰማ አስታወቀ::

የእፎይታ ጊዜው የኮሚቴዎቻችንን የፍርድ ቤት ውጤት ተምርኩዞ እንደሚያበቃ ድምፃችን ይሰማ አስታወቀ::

መንግስት በኮሚቴዎቻችን ላይ የጥፋተኝነት ብይን የሚሰጥ ከሆነ የእፎይታ ጊዜው እንደሚያበቃ እና በአዲስ ጉልበት ሰላማዊ ተቃውሞው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ድምፃችን ይሰማ አስታወቀ፡፡

ሙሉውን መግለጫ ከዚህ በታችን እንደሚከተለው ይቀርባል፡

ከዒደል ፊጥር አስቀድሞ የታወጀው የእፎይታ ግዜ ማብቂያ ከኮሚቴዎቻችን የፍርድ ሂደት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ይኖረዋል፡፡ በርካታ መስዋእትነት በከፈልንበት ሰላማዊ ትግላችን ውስጥ ኮሚቴዎቻችንን ነፃ ማውጣት አንዱ ጥያቄያችን መሆኑም ይታወቃል፡፡

ህዝበ ሙስሊሙ ደጋግሞ እንደገለፀው ለዚህ ጥያቄው መሪዎቻችንን በነፃ ከማሰናበት ውጪ ምንም አይነት መልስ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ መሪዎቻችንን በቀጠሮ ዳግም ማጉላላት ወይም በሃሰት ተመስርቶ መፍረድ በእፎይታ ጊዜው ርዝመት እና ከዚያ በኋላ በሚኖረው ትግላችን ጥልቀት ላይ ግልፅ ተፅእኖ ይኖረዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ከእፎይታ ጊዜው በኋላ ለሚኖረን ረጅም ጉዞ የመንግስትን እግር እየተከታተልን መሪዎቻችንን በመያዣነት እንዲጠቀምባቸው እንፈቅዳለን ማለት አይደለም፡፡

በእፎይታ ጊዜው ሰላማዊ ትግላችን በሚገባ ተገምግሟል፡፡ ብዙሃኑ የተሳተፈበት የቀጣይ አቅጣጫ ቀረፃ እና የአካሄድ ስልትም ተነድፏል፡፡ በዚህ ረገድ የእፎይታ ጊዜው ለተገቢው ስልታዊ ጥቅም ውሏል፡፡ በዚህ ወቅት የተከናወኑ አበይት ተግባራት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚገለፁ ይሆናሉ፡፡ ቀጣይ አቅጣጫችን እና የትግል ስልታችን የእፎይታ ጊዜው ማብቂያ እስከሚታወጅ ድረስ ይፋ ባይሆንም በነዚህ ጊዜያት መንግስት እየመረጠ ያለው አካሄድ የህዝቡም አቅጣጫ ምን ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ የሚሰጥ ነው፡፡

በቀሪው ጊዜ የመሪዎቻችን የፍርድ ሂደት እንደመጨረሻ ግብአት ተወስዶ የእፎይታ ጊዜው ማብቂያ እና የቀጣዩ ጉዞ ጅማሬ ይሆናል፡፡ የመሪዎቻችን የፍርድ ሂደት ላነሳናቸው ጥያቄዎች መፍትሄ የማፈላለጉ ሂደት ቀጣይ ጉዞ ወይም በጥያቄዎቻችን መልስ ማጣት ማግስት የሚጠነሰሰው ሌላው ትግል መጀመሪያ ይሆናል፡፡