የጋራ ላይ ፉጨት!! //ደመቀ ከበደ – ጣና ዳር//
የጋራ ላይ ፉጨት!!
//ደመቀ ከበደ – ጣና ዳር//
‹‹ሀበሽ አባ ደፋር – አባ ሰው አይፈሬ
ጫማ የለም ከእግሩ – ተሰርቶ ጎፈሬ፤
ሀበሽ አባ ሞጋች – አባ ጎበዝ ጤፉ
ጋራ ላይ ያቅራራል – በጎቹ ሲጠፉ››
የሚሉት ቀረርቶ – የሚሉት ሽለላ
ስንት ወንድ ገደለ – ስንት ጎበዝ በላ፤
‹‹ደፋር ነው እያሉ – ጀግና ነው እያሉ
የሞት ሞቱን ሲሞት – ዳር ቆመው ያያሉ፤
ተውት ይሄን ሶታ – ይሄንን ጠንበለል
ጀግና ነህ አትበሉት – እንዲያው ይንጎማለል፤››
የሚሉት የእናት ወግ – የአባት ማስፈራሪያ
ስንት ወንድ አከሸፈ – እንደ ዘመን ድሪያ፤
እኔ ግን እላለሁ፤
ተውት ይኸን ጀግና – ይውጣ ወደ ጋራ
ይሸልል ይፎክር – እንዳሻው ያቅራራ
እንዳሻው ‹‹ቡ!›› ይበል – ያሻውን ይጣራ
ሰው እንዴት ይኖራል – እያየ መከራ!!
