ከኤርትራውያን ጎን መቆም አለብን!!!

ልሂቃን ለስልጣናቸው ሲሉ ሊሰብሩት የሚጥሩትን ድልድይና ገመድ አጠናክረነው በሰላም አብረን መኖር የምንችለው፡፡
በእርግጥ እኛም ከኤርትራውያን የምንሻልበት ደረጃ ላይ አይደለንም፡፡እነሱም እንደኛው ናቸው፡፡ መከራ ውስጥ ሆነውም ቢሆን ግን በሳውዲ አረቢያ ሰቆቃ የደረሰባቸውን ዜጎች ድምጽ ከጎናችን ሆነው አሰምተዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ከጎናችን ሆነው የአገራችን ቡድን አበረታትተዋል፡፡
ድሮም ቢሆን ህዝብ በራሱ ተሳስቶ አያውቅም፡፡ ህዝብን የሚያወናብዱት ልሂቃን ናቸው፡፡ ኤርትራ በጣሊያን እጅ በነበረችበት ወቅት በርካቶቹ ወደ እናት አገራቸው ጠፍተው ገብተው በከፍተኛ ስልጣን አገራቸውን አስተዳድረዋል፡፡ እነ አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስግዶም ስለ እናት አገራቸው መስዋትነት ከፍለዋል፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌደራል ስርዓት ስትቀላቀል ጨፍረዋል፣ ደስታቸውን በእምባ ሳይቀር ገልጸዋል፡፡ ይነሱም ይብዙም ኤርትራውያን በኢትዮጵያ መከራ ጊዜ ከጎናችን እርቀው አያውቁም፡፡
አጼ ኃይለስላሴ ፌደሬሽኑን ሲያፈርስ በኢትዮጵያውያን ድጋፍ ወይንም ግፊት አልነበረም፡፡ መንግስቱ ኃይለማሪያም በኤርትራውያን ላይ እርምጃ ሲወስድም ቢሆን እንዲሁ፡፡ ጀብሃና ሻዕቢያ በአረብ አገራት ድጋፍ ኤርትራን ለመገንጠል የጣሩት በህዝቡ ትዕዛዝና ግፊት አሊያም ድጋፍ አልነበረም፡፡ እንዲያውም ይህንን ተገንጣይነት ኤርትራውያን ‹‹እናት አገር ወይንም ሞት›› ብለው ተዋግተውታል፡፡ በኢትዮጵያ የነበሩት አስተዳደሮችም ሆነ ‹‹ወንበዴዎቹ›› ስህተት ግን ሁለቱን ህዝቦች መካከል ያለውን ድልድይ ለመስበር ሳይታክቱ ሰርተዋል፡፡
ህወሓትና ሻዕቢያ ስልጣን ከያዙ በኋላም ቢሆን የሁለቱ ህዝቦች ትስስር እንደፈለጉት ሊበጠስላቸው አልቻለም፡፡ የሻዕቢያና የህወሓት ካድሬዎች ሁለቱን ህዝቦች እየደበደቡ፣ እየዘረፉ፣ እያሰቃዩ ከአስመራና አዲስ አበባ ሲያስወጡ ህዝብ የተለያየው በእንባ ነበር፡፡
በእርግጥ የመንግስታት ፕሮፖጋንዳ፣ ካድሬዎች የሚፈጥሩት መከራና ኢኮኖሚያዊ ወይንም ሌላ ግንኙነት በመቋረጡ ምክንያት ህዝቦች ሊቆራረጡ ይችላሉ፡፡ ሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ለመስበር የተደረገው ሙከራ ግን አልተሳካም፡፡ አዎ! ኤርትራውያን የአገሪቱ ‹‹መንግስት›› ሰላማዊ ሰልፈኞቹን ባሰረበትና በደበደበበት ወቅት ከጎናችን ሆነው ገመዱ ኃይለስላሴ፣ መንግስቱ ኃይለማሪያም፣ ኢሳያስ፣ መለስ፣ ህወሓት፣ ሻዕቢያ ሊበጥሱት የማይችሉ የደም ገመድ መሆኑ በድጋሜ አሳይተውናል፡፡
እናም እንደነሱው ከጎናቸው መቆም ይገባናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢሳያስ ጠፋ፣ ታመመ እየተባለ ነው፡፡ አምባገነን መሪ ሲሞት፣ ሲታመም፣ ወይንም አምባገነኑ ስርዓት ምክንያት ስርዓት ሲናጋ የሚጎዳው ሀብትና ጥበቃ የሌለው ምስኪን ህዝብ ነው፡፡ ሀብት ያላቸው የኤርትራ ባለስልጣናት በፈለጉት አገር ሄደው ይኖራሉ፡፡ ጥበቃ ያላቸው አገር ውስጥም ቢሆን አንጻራዊ ሰላም ይኖራቸዋል፡፡ ድሃውና ሲጨቆን የነበረው ህዝብ ግን አምባገነኑ እያለም ሆነ ሞቱ ስጋት ውስጥ ነው፡፡ የአገር አደጋ አደጋ የሚሆነው ለድሃው ነው፡፡
ኢትዮጰያውያን መለስ ዜናዊ ጠፋ፣ ታመመ፣ ሞተ በተባለበት ወቅት አምባገነንነቱን ረስተን ‹‹አገር ትፈራርሳለች›› ብለን ተጨንቀናል፡፡ ኤርትራውያንም አሁን ተመሳሳይ ስጋት ውስጥ ናቸው፡፡ ሁለቱ ህዝብ በተለያየ ጊዜ ይከሰቱ እንጅ ተመሳሳይ መከራ፣ ስጋት ውስጥ ናቸው፡፡ ችግራቸው መሰረት ተመሳሳይ ነው፡፡ እናም እነዚህን ችግሮች መፍታት የሚችሉት አንዱ ከአንዱ ጎን በመቆም ብቻ ነው፡፡
ለችግሮቻቸው መፍትሄ ማምጣት እንኳን ባንችል ልክ እንደወትሮው፣ ልክ እንደባህላችን፣ ልክ እነሱ እንዳደረጉት ከጎባቸው መሆናችንን ማሳየት አለብን፡፡ ሲሆን ታሪክ፣ ደም፣ አምሮ መኖር በደመነፍስ እያነጋኘን እንደሆነ በቅርቡ አይተነዋል፡፡ የሁለቱ አምባገነን ስርዓቶች ፕሮፖንዳና መሰሪነት በርካቶቹን እሴቶቻችን ሸርሽሮት አብሮ መስራት እንደማይቻል የሚያስብ የዋህ (ካድሬ ቢኖር እንኳ) ጎረቤቶች ነን፡፡ የኤርትራ ችግር መቼም ቢሆን የኢትዮጵያውያን ችግር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ችግር የኤርትራውያን ችግር ነው፡፡ ከሁለቱ አገራት መካከል አንዱ እንደ ሰው ተሰዶ ወይንም ሸሽቶ፣ አሊያም አጥሮ መኖር አይችልም፡፡ የሶማሊያና የሱዳን ችግር እንኳን ችግራችን ሆኗል፡፡
እናም በችግራቸው ጊዜ አብረናቸው መቆማችን ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለእኛም ጥቅም ነው፡፡ ስለሆነም ከኤርትራውያን ወንድምና እህቶቻችን ጎን አብረን መቆም ይኖርብናል፡፡ እንዲህ ሲሆንም ነው ልሂቃን ለስልጣናቸው ሲሉ ሊሰብሩት የሚጥሩትን ድልድይና ገመድ አጠናክረነው በሰላም አብረን መኖር የምንችለው፡፡ — with Getachew Shiferaw and 2 others.