የአዲሱ መዋቅር ብርታት ድካሞች(የቀለም ቀንድ ጋዜጣ ላይ የተስተናገደ)

የሃገራችን ፓርላማ መስከረም 24/2008 በአምስተኛ ዘመን የመጀመሪያ ጉባኤው የሃገሪቱን ጠ/ሚኒስትር ሾሞ፤ ጠ/ሚኒስትሩ ደግሞ 30 የካቢኔ አባላትን ሹመት በማግስቱ አቅርበው አስፀድቀዋል፡፡ ተሿሚ የካቢኔ አባላቱ 30 የደረሱት በአስፈፃሚው ውስጥ አዳዲስ የሚኒስትር መስሪያ ቤቶች በመዋቀራቸው ነው፡፡ ከሚኒስትር መስሪያ ቤቶች በተጨማሪ በኤጀንሲ፣በባለስልጣን እና ኮርፖሬሽን ደረጃ የሚዋቀሩ አስፈፃሚ መስሪያቤቶች እንደሚኖሩም ተገልጧል፡፡ የአዲሱ መዋቅር ትቂት መልካም አካሄድን ከብዙ ድንግርግሮችጋር ይዞ የመጣ ነው፡፡
በጎ ጎኖች
በግሌ መልካም መስለው ከሚታዩኝ አንዱ የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኤጀንሲ እንደገና ህልውና ማግኘት ነው፡፡ኤጀንሲው የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ከመከሰታቸው በፊት ቅድመ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ እና አደጋዎቹ ከተከሰቱ በኋላም በፍጥነት ለተጎጅዎች ደርሶ ጉዳቱን ባለበት የሚያስቀር ይሆናል የተባለለት ነው፡፡ ኤጀንሲው የተባለለትን ያህል በተግባሩ ላይ የሚገኝ ከሆነ የመስሪያቤቱ መፈጠር ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ እንደ እኛ ሃገር በተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ አደጋ ጥላስር ለሚኖር ህዝብ የዚህ አይነት መስሪያቤት ጥቅም የትየለሌ ነው- ያው የማስፈፀም ብቃቱ ጥርጣሬ እንዳለ ሆኖ፡፡ ከሚኒስትር መስሪያቤቶች ቁጥር ማሻቀብ ጋር የሴት ሚኒስትሮች ቁጥር(አራት) በአንጻራዊነት ከፍ እንዲል መደረጉም የአዲሱ መዋቅር በጎ ገፅታ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ሴቶች የህብረተሰቡን ከግማሽ በላይ ቁጥር መያዛቸውን ባገናዘበ ሁኔታ ተወክለዋል ማለት አይደለም፡፡
የአዲሱ መዋቅር ሌላ በጎ ጎን በገጠር እና በከተማ የስራ ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤንሲዎች መፈጠራቸው ነው፡፡ ስራ ፈጠራ ኮብል ስቶን መጥረብ፣ ከብት ማርባት እና ጣውላ መሰንጠቅ ብቻ እስከሚመስል ድረስ ወጣቱ በስራ ፈጠራ ድርቅ በሚንገላታበት ሃገር ስሙን የሚመጥን ስራ የመስራት አቅም የሚኖረው ከሆነ የመስሪያቤቱ መፈጠር ደግ ነው፡፡ለሃገራችን ኢኮኖሚ ካለው የአምድነት ድርሻ አንፃር የቡናና ሻይ ልማት እና ግብይት ኤጀንሲ መዋቀሩም መልካም ነው፡፡ በቀድሞው መዋቅር በመከላከያ ሚኒስተር ስር የነበረው የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን በአዲሱ መዋቅር ተጠሪነቱ ለጠቅላይሚኒስትሩ መሆኑ አዲሱ መዋቅር ያመጣው ሌላ መልካም እርምጃ ነው፡፡ የቀደመው መዋቅር ይህን ኮርፓሬሽን በመከላከያ ሚኒስትር ስር ማድረጉ የሃገር መከላከያ ሚኒስትርን ያለ ተፈጥሮው ንግድ ወደማጧጧፉ መርቶት ከርሟል፡፡ ይህ ደግሞ የወታደሩን ኢኮኖሚያዊ ጡንቻ ያለ ቅጥ አፈርጥሞ እንደ ግብፁ መከላከያ የሃገሪቱን በጀት ሳይቀር የምወስነው እኔ እንጅ ፓርላማው አይደለም ወደማለቱ፤ ብሎም እንደ ግብፅ አቻው የሃገሪቱን ባጀት የአንበሳ ድርሻ ወደ መውሰዱ አምባገነንነት ሊመራው የማይችልበት ምክንያት የለም፡፡ እነዚህ በኔ እይታ በጎ የመሰሉኝ የአዲሱ መዋቅር ገፅታዎች ሲሆኑ በመዋቅሩ ላይ ያየኋቸው ድንግርግሮችንም እነሆ፤
የቢሮ ግሽበት
አዲሱ የአስፈፃሚው የመንግስት ክንፍ መዋቅር አይነተኛ እንከን ተመሳሳይ ስራ የሚሰሩ፣ በአንድ ሚኒስትር መስሪያቤት ስር ተካተው ሊዋቀሩ የሚችሉ መስሪያቤቶችን በተለያዩ ሚኒስትሮች፣ ኤጀንሲዎች አለያም ኮርፖሬሽኖች ስር ተበጣጥሰው በተለያዩ አለቆች የሚዘወሩ ማድረጉ ነው፡፡
ግሽበት አንድ
በቀድሞው መዋቅር የግብርና ሚኒስተር አሁን ለሶስት ተከፍሎ የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስተር፣ የእንስሳትና አሳ ሃብት ሚኒስተር እና የአካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር(የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር የሚለው አጠራር ራሱ ግራ አጋቢ ነው) የሚባሉ ሚኒስትር መስሪያቤቶች ተፈጥረዋል፡፡ በሌላ በኩል የውሃ፣መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስተር የሚባል ሌላ ሚኒስተር ተፈጥሯል፡፡ እንደሚታወቀው እርሻ የሚለው ማዕቀፍ መስኖንም የማቀፍ ግዝፈት ያለው ነው፡፡ ስለዚህ ከኤሌክትሪክ ሚኒስተር ጋር የተዳበለው የመስኖ ጉዳይ በእርሻ እና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስተር ስር ሊታቀፍ የሚችል ነበር፡፡ ስለ መስኖ ሲሰሩ የእርሻን ጉዳይ መነጠል ይቻላል ተብሎ ነው እንግዲህ እነዚህ መስሪያቤቶች ለየብቻ ያውም በሚኒስትር መስሪያቤት ደረጃ እንዲዋቀሩ የተደረገው፡፡
በተመሳሳይ እርሻ እና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትር የሚለው መዋቅር እያለ የማዕድን፣ነዳጅ እና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር የሚባል ሌላ አዲስ የሚኒስትር መስሪያ ቤት ተዋቅሯል፡፡ነዳጅ፣የተፈጥሮ ጋዝና ማዕድን ተፈጥሮ ሃብት እንደሆኑ የታወቀ ነው፡፡ እናም የእርሻ እና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትር በነዚህ ሃብቶች ላይ የሚሰሩትን ስራዎች ማከናወን ሲችል ለማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ሃብት ሌላ ሚኒስትር ማዋቀሩ ግሩም ነገር ነው፡፡ ነዳጅ እና ተፈጥሮ ጋዝ የሚለው ለአዲሱ ሚኒስትር መስሪያቤት የተሰጠው የስም ድግግሞሽ ራሱ ሌላ ግራ አጋቢ ጉዳይ ነው፡፡
ከላይ እንደተጠቀሰው የቀድሞው ግብርና ሚኒስትር ሶስተኛ ክፋይ የሆነ የእንስሳት እና አሣ ሃብት ሚኒስተር የሚባል አዲስ መስሪያቤት ተቋቁሟል፡፡ በሌላ በኩል በቀድሞው ካቢኔ ውስጥም የነበረው የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር በአዲሱ መዋቅር የፌደራል ጉዳዮች እና የአርብቶ አደር ልማት ሚኒስትር ተብሎ በአዲስ መልክ ተዋቅሯል፡፡ የአርብቶ አደር ጉዳዮች የሚለው የዚህ ሚኒስትር መስሪያቤት የስራ ድርሻ በአመዛኙ አርብቶ አደሩ ከሚያረባው እንስሳት ምርታማነት ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ይህ የእንስሳቱን ምርታማነት ጉዳይ የሚመለከተው የስራ ክፍል የእንስሳት እና አሣ ሃብት ሚኒስትር በሚባለው ሚኒስትር መስሪያቤት መከናወን የሚችል ነው፡፡ የእንስሳት እና አሣ ሃብት ጉዳይ በሚኒስትር ደረጃ አወቃቀር ከተሰጠው አይቀር አርብቶ አደሩ የሚያረባቸው እንስሳትን ጉዳይም አብሮ ሊሰራ ይገባ ነበር፡፡ ካልሆነ ይህ መስሪያቤት ሰብል ከማምረት ጎን ለጎን እንስሳት የሚያረባውን አርሶአደር እና በከተማ በጥቃቅን እና አነስተኛ ተደራጅተው እንስሳትን የሚያረቡ ማህበራትን ጉዳይ ብቻ ይዞ ሊሰራ ነው፡፡ ይህ ከሚኒስትር መስሪያቤትነቱ ጋር ሲነፃፀር ስራ ሳያንሰው አይቀርም፡፡ የጥቃቅን እና አነስተኛ ከብት እርቢዎች እንቅስቃሴ ደግሞ ባለቤትነቱ የከተማ እና የቤቶች ልማት ሚኒስትር ነውና ሌላ ድንግርግር ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ ደግሞ ድንግርግሩን የሚያብስ የመንግስት ልማት ድርጅቶች በሚባለው አዲስ ሚኒስትር መስሪያቤት ስር የሚተዳደር የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የሚባል ድርጅት ይኖራል፡፡
በአዲሱ አወቃቀር ከፌደራል ጉዳዮች ጋር የተዳበለው የአርብቶ አደር ጉዳዮች ነገር ከአርብቶ አደሩ እንስሳት ምርታማነት በተጨማሪ የአርብቶ አደሩን ጤና፣ትምህርት፣ከተፈጥሮሃት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የሚነሱ ግጭቶችን ወዘተ በተለመከተ የሚሰራበት መዋቅር እንዲሆን ታስቦ ከሆነ እነዚህ የአርብቶ አደሩ ጉዳዮች በትምህርት፣ በጤና እና በፌደራል ጉዳዮች ወዘተ ሚኒስትሮች ውስጥ “ሜንስትሪም” ቢደረግ ይሻል ነበር፡፡በተቀረ የአርብቶ አደሩን ጉዳይ በአንድ ሚኒስትር መስሪያቤት ላይ መለጠፍ ወደ ተግባር ሲገባ የአሰራር ችግር ማስከተሉ አይቀርም፡፡
ግሽበት ሁለት
የቀድሞው የከተማ ልማት፣ቤቶች እና ኮንስትራክሽን(ይህን ቃል የሚተካ የአማርኛ ቃል ጠፍቶ ይሆን?) ሚኒስትር ለሁለት ተከፍሎ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር እና ኮንስትራችክሽን ሚኒስትር የሚባሉ አዳዲስ ሚኒስትሮች ተፈጥረዋል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የከተማ ቤቶች ልማት ስራ የኮንስትራክሽንን ጉዳይ ትቶ የሚሄድ ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለዚህ የከተማ ቤቶች ልማትን ለብቻው በአንድ ሚኒስትር፤ የኮንስትራክሽን ብሎ ደግሞ ሌላ ሚኒስትር አቋቁሞ ለሁለት መሸንሸኑ ትክክለኛ አካሄድ አይመስለኝም፡፡ ይህ አላግባብ የሆነ ሽንሸናም ሁለት ሆኑ በተባሉት መስሪያቤቶች መሃከል የሚና ድንግርግሮሽ (Role confusion) ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ለምሳሌ አሁን አሁን እየተስፋፋ ካለው የሪል እስቴት ግንባታ ኢንዳስትሪ አንፃር የከተማ ቤቶች ጉዳይ በምን መስፈርት ከኮንስትራክሽን ሚኒስትር ይልቅ ለከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ይቀርባል ተብሎ እንደተሰጠ አደናጋሪ ነው፡፡ ከኮንስትራክሽን ጉዳይ ውጭ ያለው የከተማ ቤቶች ጉዳይስ ምን ያህል ግዙፍ ሆኖ ነው ለብቻው ሚኒስትር መስሪያቤት የተቋቋመለት፡፡
በተመሳሳይ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ከኮንስትራክሽን ሚኒስትር ይልቅ በከተማ ልማት እና ቤቶች ሚኒስትር ስር እንዲሆን ሆኗል፡፡ የከተማ ቤቶችን እና የከተማ ፕላንን ጉዳይ ሳይይዝ የተዋቀረው የኮንስትራክሽን ሚኒስትር ምን ሊሰራ እንደሆነ የሚታይ ነው፡፡ ምናልባት እየተሰሩ ያሉትን ትልልቅ የኤሌክሪክ ግድቦችን እና መንገዶችን ይገነባል እንዳይባል ለግድቦቹ የኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን የሚባል መዋቅር እንደሚኖር ተነግሯል፡፡ መንገዶችን ለመገንባቱም ቢሆን ከመገናኛ እና ትራንስፖርት ሚኒስትር የሚተርፍ፤ ሌላ ሚኒስትር መስሪያቤት እስከማዋቀር የሚያደርስ ስራ ካለ ወደፊት ይታያል፡፡ ይብስ የሚገርመው ደግሞ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር በሚባለው አዲስ የተቋቋመ ሚኒስትር መስሪያቤት ስር የኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን የሚባል የልማት ድርጅት እንደሚመሰረት መነገሩ ነው፡፡
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር የከተሞች ስራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ተብሎ የሚጠራ ተቋምንም በስሩ እንዲያስተዳድር ተደርጓል፡፡ በሌላ በኩል በእርሻ እና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትር ስር የተቋቋመው የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ተቋም የሚባል መስሪያ ቤት እንደሚፈጠር ተገልጧል፡፡ የስራ እድል ፈጠራን እና የምግብ ዋስትናን የተመለከተ ተመሳሳይ ጉዳይን የሚሰሩ መስሪያቤቶችን በገጠር እና በከተማ ብሎ ሸንሽኖ ሁለት የተለያዩ ኤጀንዎች አቋቁሞ፤ በሁለት የተለያለዩ ሚኒስትሮች (በእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትር እና የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር) ስር ማድረግ ለሃገር ሃብት ያለማሰብ ነው፡፡
ግሽበት ሶስት
የመንግስት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር አዲስ ከተዋቀሩ ሚኒስትር መስሪያቤቶች አንዱ ነው፡፡ይህ ሚኒስትር መስሪያቤት ቀድሞ የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ሚኒስተርን ይመሩ በነበሩት ወ/ሮ ደሚቱ አንቢሳ የሚመራ ነው፡፡ ይህ ሚኒስትር መስሪያቤት የብዙ ሚኒስትር መስሪያቤቶችን ሃላፊነት(የሰላሳውንም ላለማለት ነው) በመሻማት እና አደናጋሪ ማንነት በመላበስ ወደር የሌለው ነው፡፡ ትቂቶችን ለማሳየት ያህል የመገናኛ እና ትራንስፖርት ሚኒስትርን መበወከል ይሁን በመገፍተር በማይታወቅ ሁኔታ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንን በስሩ ይዟል፡፡ በተጨማሪም ተጠሪነቱ የእርሱ ያልሆነውን ኢትዮጵያ አየር መንገድን የፋይናንስ አጠቃቀም እና አስተዳደርን ይቆጣጠራል፡፡ ከኢንዱስትሪ ሚኒስትር ላይ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽንን እና የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽንን ወስዷል፡፡ የኮንስትራክሽን ሚኒስትር ድርሻ መሆን የሚገባውን የኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽንን አቅፏል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽንን ከንግድ ሚኒስትር ላይ አፈፍ አድርጓል፡፡ ከእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትር ላይ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽንን ነጥሎ ወስዷል፡፡ የዲዛይንና ቁጥጥር ስራዎችም ከከተማ ልማትና ቤቶች ወይም ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ተገንጥሎ በዚሁ ሚኒስትር ስር ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅና ጋዝ ምርት አቅርቦት ኮርፖሬሽን በሚል ስም ይዋቀራል የተባለው ተቋምም ከማዕድን፣ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር ይልቅ ለዚህ ሚኒስትር ይቀርባል ተብሎ በስሩ እንዲሆን ጀባ ተብሏል፡፡የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽንም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ስር ነው ቢባልም ቁጥጥሩ የዚሁ አስገራሚ ሚኒስትር ይሆን ዘንድ ሆኗል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት የመስሪያ ቤቶች ብዛት፣የተጠሪነትና የሃላፊነት ግጭት፣የስሞች ድግግሞሾች ጉዳታቸው ብዙ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በነዚህ ሁሉ ሚኒስትር መስሪያቤቶች፣ በስራቸው ባሉ ኤጀንሲዎች እና ሌሎች ተቋማት ስውጥ ለሚሰገሰጉ ባለስልጣናት ደሞዝ እና ቅንጡ ህይዎት የሚፈሰው ንዋይ የደሃዋን ሃገራችንን የኢኮኖሚ አቅም ይብስ የሚያደቅ ነው፡፡