በመላው ዓለም በጉበት በሽታ (ሄፒታይተስ) በየዕለቱ አራት ሺሕ ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት ይዳረጋሉ፡፡
በመላው ዓለም በጉበት በሽታ (ሄፒታይተስ) በየዕለቱ አራት ሺሕ ሰዎች፣ በዓመት ደግሞ 1.5 ሚሊዮን ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት ይዳረጋሉ፡፡በኢትዮጵያ ደግሞ ወደ አሥር ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የቫይረሱ ተጠቂ ናቸው:: በዓለም ላይ ይህን ያህል የሚገድል ሌላ ተላላፊ በሽታ የለም፡፡ በአንዳንድ ጥናቶች ላይ እንደተመለከተው ከሆነ ኤችአይቪ፣ ቲቢ እና ወባ አንድ ላይ ተደምረው ሄፒታይተስ የሚገድለውን ያህል አይገድሉም፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የቫይረሱ ተጠቂዎች ብዛት ሊታወቅ የቻለው በጥናት ላይ በተመረኮዘ ዳሰሳ ሳይሆን የኤክስፐርቶች ግምት መሆኑ ሲታወቅ ግምቱም የተሠራው የሌሎች አገሮችን ተመሳሳይ አኗኗር ዘዴ፣ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና ውስን የሆኑ ጥናቶች በመመርኮዝ ነው::በዚሁ በሽታ ዙሪያ ላይ ትኩረት ያደረገ አገር አቀፍ የዳሰሳ ጥናት ለማካሄድ መታቀዱ ከዚህ ቀደም ተሰምቷል::
ጋስትሮንትሮሎጂ ማለት የምግብ ማንሸራሸሪያና ማዋሃጃ አካላት መሆኑንና ይህም የምግብ መውረጃ ቱቦን፣ ጨጓራን፣ ቆሽት፣ ሀሞት ከረጢት፣ ጉበት፣ ትንሹንና ትልቁን አንጀቶች ያካተተ ሲሆን ሄፒታይተስ ‹‹ሲ››ን ማዳን፣ ሄፒታይተስ ‹‹ቢ››› ደግሞ ተከትቦ መከላከል ይቻላል፡፡ ስለዚህ ልንቆጣጠረውና ከተያዝንም ልንድን የምንችለው ነው፡፡ ለዚህም በቂ ግንዛቤ፣ እንዲሁም የሚያስፈልጉ ምርመራዎችንና ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ በዋነኛነት ለኤችአይቪ የሚደረጉ ጥንቃቄዎች በሞላ ለሄፒታይተስ ቫይረሶችም ጠቃሚ ነው፡፡
ለኤችአይቪ የሚከናወኑ ስራዎች ሄፒታይተስንም ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ ኤችአይቪ፣ ሄፒታይተስ ቢ እና ሲ የሚተላለፉባቸው መንገዶች ጥንቃቄ በጎደለው የወሲብ ግንኙነት፣ በደም ንክኪ፣ በመርፌና ስለታም ከሆኑ ነገሮች ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ዓይነት የመተላለፊያ መንገዶች ስላላቸው የመከላከያ መንገዶቹም አንድ ዓይነት ናቸው፡፡ሄፒታይተስ ቢ ክትባት የሕፃናት ክትባት ፓኬጅ ውስጥ እንዲገባ ካደረጉት 47 የአፍሪካ አገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ የክትባቱ መድኃኒቶች 99 በመቶ ያህሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ይመረታሉ፡፡ ይህም ሆኖ ግን ለበሽታው ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ለተለዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አይደርሱም::
