የንጹሃን ዜጎች መታሰር የሀገር መታሰር ነው፤ ዜጎችም ያለሀጥያታቸው መታሰራቸው ሲቆም፣ ሀገር ትፈታለች!

ዛሬ የዞን 9 አራት ልጆች (ናቲ፣ አቤል፣ አጥናፍና ሶሊያና) ከክሳቸው ነጻ መባላቸውን አውቀናል፡፡ በፍቄም ተከላከል ተብሏል፡፡ ቀድሞም ነጻ የነበሩት አዳጊ ልጆች፣ ዛሬ ነጻ መባላቸው ደስ ይላል፤ በፖለቲካ ውሳኔ ያለአግባብ ከዓመት በላይ መታሰራቸው እጅግ ቢያሳዝንም! በፍቄም የጊዜ ጉዳይ እንጂ ከእስር እንደሚወጣ እናምናለን – ነጻ ነውና!
ዋናው ነገር ግን፣ እስከመቼ በሀሰት እየታሰርን፣ እየተሰቃየን፣ እየተፈታን፣ እንደገና እየታሰርን፣ እየተፈታን …እንቀጥለላለን የሚለው ነው፡፡
እስር ቤቶቻችን የሀሰት ክስ በቀረበባቸው ዜጎች መጨናነቅ ከጀመሩ ቆዩ! በኦነግ፣ በግንቦት ሰባት፣ በአርበኞች ግንባር፣ በደሚት፣ በኦብነግ፣ በጋምቤላ ነጻ አውጪ ግንባር፣ …ጋር ግንኙነት ነበራቸው በሚል .. እንዲሁም በሰላማዊ ትግል የፖለቲካ መስመር ተሰማርተው ሲንቀሰቀሱ ‹‹ለአመጽና ለሽብር ተግባር ሲንቀሳቀሱ …›› በሚል፣ ሀሳባቸውን በነጻነት በመግለጻቸው፣ በፖለቲካ የተለየ አመለካከት በመያዛቸው፣ ለሃይማኖት ነጻነት መብት …ወዘተ በመታገላቸው ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ንጹሃን ዜጎቻችን ያለሃጥያታቸው ‹‹አሸባሪ›› የሚል ታርጋ እየተሰጣቸው ለሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በፍርድ ሂደት ለመንገላላትና በእስር መሰቃየት ተገድደዋል፡፡ ይህ ዜጎችን ያለሃጥያታቸው የማሰቃየት የተለመደ የአገዛዙ የማጥቂያ አካሄድም ገደብ ተበጅቶለት ሊቆም ይገባዋል- ዛሬ! የንጹሃን ዜጎች መታሰር የሀገር መታሰር ነው፡፡ ዜጎች ያለሀጥያታቸው መታሰራቸው ሲቆም፣ ሀገር ትፈታለች!
አሁን ላይ፣ ሀገራችን እንድትፈታ፣ በርካታ ንጹሃን ዜጎቿ ከግፍ እስር መፈታት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ፤ በእኩል የዕይታ መነጽር፣ በእስር ላይ ለሚገኙ ንጹሃን ዜጎቻችንን በሙሉ፣ በአንድነት ቆመን ድምጻችንን ማሰማት፣ ብሎም መታገል ይጠበቅብናል!!! አሊያ፣ የእስር እና የጩኸት አዙሪቱ በሌሎች ላይ ይቀጥላል፡፡
