ቋንቋ፣ ባህልና ራስን በራስ ማስተዳደር ~ ሶስቱ በሮች! (የትነበርክ ታደለ)
እኔ ቋንቋ የለኝም። ማለትም ከቋንቋ ጋር አልተፈጠርኩም። ወይም ልክ እንደ ጆሮዬ፣ እንደ አፍንጫዬ ልክ እንደ አንዱ የሰውነት አካሌ አብሮኝ የተፈጠረ ቋንቋ የለኝም። (ምናልባት ይሄን የምለው ከሁለት የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ ወላጅ እናትና ወላጅ አባት ስለተወለድኩ ብቻ እንዳይመስላችሁ!)
ይህንንም “ይሄ ቋንቋ የኛ ነው!” እያሉ ስለ አንድ ቋንቋ ሲመክሩና ሲዘክሩ የሚዉሉ ሁሉ [የኛ] ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ ምንም አይነት ማስረጃ ሊያቀርቡ አይችሉም።
የስነ ቋንቋ ትምህርት [linguistics] እንዲህ ይላል። Man is not created with language but with a mind space called ‘Language Faculty’, a space that helps him learn languages differently than animals.
ሰዎች ከእንሣት በተለየ መልኩ ቋንቋን ለመማር የሚያስችላቸው [የቋንቋ ማእከል] ጋር ተፈጠሩ እንጂ ከቋንቋ ጋር አልተፈጠሩም። ይህ ሳይንሳዊ ሀቅ ነው። ላለፉት ሀያ አራት አመታት በሀገራችን ስለ ቋንቋ ያገባናል ብለው ሲደሰኩሩ የኖሩ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ይህንን ሊያስተባብል የሚችል አንዳችም ነገር ሊያቀርቡልን አልቻሉም።
በዚህም ምክንያት እኔን ጨምሮ ብዙ ወገኖች “ቋንቋህ ምንድነው?” የሚለውን ጥያቄ መመለስ ተስኖን ለብዙ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ቀውሶች ሰለባ ሆነን አሁንም ይሄው አለን ~ እንዳለን።
ትምህርቴን እንዳጠናቀኩ ስራ መፈለግ የግድ ነውና አንድ የስራ ማስታወቅያ አወጣ ወደተባለ የክልል ቢሮ ሄድኩ። እርግጥ ነው የመጀመርያው መስፈርት ቋንቋ ነበር። እኔ ደግሞ ተወልጄ ያደኩበት ብቻም ሳይሆን ከእናቴና ከቤተሰቦቿ የተማርኩት የክልሉ ቋንቋ ስለነበረ ምንም አይነት የቋንቋ ፈተና አላሰጋኝም።
ለውድድር ከመጡት ከሌሎች ጓደኞቼ ጋር እዝያው መስርያቤት ውስጥ ካለ ካፌ ምሳ በልተን ሻይ እየጠጣን እየተጨዋወትን መጠባበቅ ጀመርን። ተራዬ ደርሶ ለቃለ መጠይቅ ተጠራሁና ወደ ውስጥ ዘለቅሁ።
ስምንት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ክፍሉን በክብ ሞልተው ተቀምጠዋል። ሶስቱ ሰዎች ከኔ አካባቢ የመጡ (በተለይ ሁለቱ አባቴ ያስተማራቸው ወጣቶች) ስለሆኑ ተረጋጋሁ። ለተጠያቂዎች የተዘጋጀ ወንበር ስለሌለ በሩን ወደ ኋላ ዘግቼ እጄንም ወደ ኋላ አቆላምሜ ቆምኩ።
“ስምህ ማን ነው?” ነገርኳቸው።
“ከቋንቋው ውጭ እያወራህ መሆኑ ይታወቅሀል?” በፈተናው ቋንቋ ነው የሚያናግሩኝ። ግራ ገባኝ። እኔ እስካሁን ምንም አላወራሁም። ስሜን ተጠየኩ ተናገርኩ። “ይቅርታ አልገባኝም!” ስል በትህትና በዝያው ቋንቋ መለስኩ።
“አየህ ያንተ ችግር ከስምህ ይጀምራል!” አለኝ አንዱ። ያውም የአባቴ ተማሪ።
“ስሜን ከቋንቋው ጋር ምን ያገናኘዋል?” በአጉል ድፍረት ጠየኩ።
“በል ጊዜ አትፍጅብን፣ ስምህን አስተካክለህ ና!” ብለው እዝያው እንደቆምኩ ሌላ ተጠያቂ እንዲገባ ስም መጥራት ጀመሩ።
አቅለሸለሸኝ! ብቸኝነት ተሰማኝ! እንደ ደነዘዝኩ ከክፍሉ ወጣሁ። ቅድም ሥስቅ ስጫወት ያዩኝ ጓደኞቼ ከደጅ ቁመው “እንዴ! ምን ሆንክ?” ግራ ገባቸው። ለጥያቄ ገብቼ ውጤቴን ሰምቼ እንደወጣሁ አልነገርኳቸውም። ማንነቴን ብቻ ሳይሆን ማንምነቴን በአንዲት አረፍተ ነገር ያስረዱኝን ሰዎች በውስጤ እንደ ጭራቅ ስዬ ግቢውን ለቅቄ ወጣሁ።
ከዚያች ቀን ወዲህ እዝያ ክልል ውስጥ “ስራ ያለፈተና” ብባል እንኳ እርም ብዬ ቀረሁ። እውነቱን ለመናገር የዝያን ሰሞን እናቴ እንኳ በዝያ ቋንቋ ስታናግረኝ አልመልስላትም ነበር………
……ኖርኩ ኖርኩና ስራ አጥ መባል ሲሰለቸኝ፣ ተምሬ ቤተሰብ ላይ መቀመጥ ሲጨንቀኝ “እስኪ ወደ አባቴ [ክልል] ደግሞ ልሂድና እድሌን ልሞክር አልኩና ጉዞ ጀመርኩ። እዚህስ ስሜ ለክፉ አልሰጠኝም። ቋንቋውም እንደዚሁ። ግን የእናቴ ታሪክ ተጠይቆ ተደረሰበት። አባቴስ ይህንን ያህል ዘመን ለምን ወደ ክልሉ ተመልሶ አልኖረም? የሚል ጥያቄዎች ከዚህም ከዚያም ጎረፉ። ምንም እንኳ ቋንቋውን አሳምሬ ብችለውም “ባህሉ ይከብድህ ይሆናል!” በሚል [ተልካሻ] ምክንያት ስራ “እነሆ” የሚለኝ ጠፋ።
ይገርማልኮ! በዚህ ክልል ውስጥ እንኳን ቋንቋውን እንኳን ባህሉን ምኑንም የማያውቁ የብዙ ሀገር ዜጎችን አያለሁ። በየቢሮው ለስልጠና ይመጣሉ፣ ለረዥምና ለአጭር ጊዜ ቆይታ መጥተው ከህዝቡም ጋር ተላምደው ሲመለሱ አያለሁ። የወለዱ ፈረንጆችም አጋጥመውኛል። እና እኔ ምንድነኝና ነው ለራሴ ባህል እንደ እንግዳ የምቆጠረው? ይሄ አይን ያወጣ ዘረኝነት ነው።
አንድ ቀን ዘው ብዬ የከተማው አስተዳደር ቢሮ ገባሁና የልቤን ተናገርኩ። “ዘረኞች ናችሁ!” አልኩት። አልደነገጠም። ስንት አመት በሬዲዮና በቴሌቪዥን ሰምቼው የሰለቸኝን “ራስን በራስ ማስተዳደር” የፖለቲካ ዲስኩሩን ደሰኮረብኝ። “ማንኛውም እድል የሚሰጠው በክልሉ ላሉ ሰዎች ብቻ ነው!” አለኝ።
የኔ ክልል የት ነው? ቋንቋውን ባውቀው በስሜ እየተገፋሁ፣ ባህሉን ባህሌ ባደርግ “የራስን በራስ” በሚል በማይገባኝ ሰበብ ከኖርኩበት እያሳደዱኝ…..ታድያ እኔ ማን ነኝ?
…… እንዳልኳችሁ እኔ የራሴ ቋንቋ የለኝም። እንዲኖረኝም አልቋምጥም። ከሰብአዊው ፍጥረት ጋር አብሬ ለመኖር እንድችል፣ የሰው ሀሳብ ለመረዳትና ለማስረዳት፣ ስራዬን በአግባቡ ለመስራት……ቋንቋ እማራለሁ። የሀገሬን ሶስት ቋንቋዎች አጥርቼ እናገራለሁ፣ ሌሎች ሶስት ቋንቋዎችን ደግሞ ለመግባቢያነት ተምርያቸዋለሁ፣….. የፈረንጁን እንግሊዝኛ ከመማርም አልፌ አሳምሬ አስተምረዋለሁ፣ ፈረንሳይኛ ጀምሬ ተውኩ (ሳስበው ለጊዜው አልፈልገውም) አረብ ወይም ቻይና ሀገር መሄድ ካስፈለገኝ ቋንቋቸውን እማረዋለሁ። እዚህ ውስጥ ምንም ፖለቲካ የለም፣ “የኔ ነው! የእምዬ ነው! ቅብርጥስዮ!” የሚል ጣጣ የለበትም። ካስፈለገኝ ያስፈልገኛል ካላስፈለገኝ እንዲሁ…..
….ሌላው አለም ቋንቋውን ስትማርለት ደስ ይለዋል። የሱን ቋንቋ በመናገርህ በሌላው አለም ትከበራለህ። ተወልደህ ባደክባት፣ ተምረህ ራስህን ባወክባት ኢትዮጵያ ግን በምትሰማው ቋንቋ ትመታለህ….በምትናገረው ቋንቋ ትገለላለህ!….(ያንተ አይደለማ!)….ጥንት የነበረውን የቋንቋ [ጭቆና] እያወሩ እነሱም ዛሬ በቋንቋ ይጨቁናሉ።