አስተርጉሙልን ( ሄኖክ የሺጥላ )
አስተርጉሙልን ( ሄኖክ የሺጥላ ) —
ብዙ ያልገቡን ነገሮች አሉ ። ስለዚህ አስተርጉሙልን ። ሰሞኑን ምርጫውን 100 ፐርሰንት እንዳሸነፋቹ ሰምተናል ። ምን ማለት እንደሆነ የገንዘቤ ዲባባን አስተርጏሚ አስጠሩና አስተርጉሙልን ። ለኦባምም በደምብ አስተርጉሙለት ! መንግስት ድርቁን በቁጥጥር ስር አውለነዋል እያለ ነው ። ምን ማለት እንደሆነ ይተርጎምልን ። ጋዜጠኛ በመሆኑ የታሰረ አንድም ጸሐፊ ( ጋዜጠኛ ) የለም የሚል ነገር አይናማው ጠቅላይ ሚንስቴር ሲናገሩ ሰምተናል ፣ ይኽንንም አስተርጉሙልን!!! አማራ በመሆኑ አንድም የተፈናቀለ የለም ሲባል እንዳልነበር ፣ ዛሬ ደሞ የተፈናቀሉት አማሮች ወደ-ቀድሞ ቦታቸው እንዲሄዱ ፣ ለወደመ ንብረታቸውም ካሳ የሚያገኙበት መንገድ እንደሚመቻች ከሶስቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች አንዱ ( አቶ ደመቀ መኮንን ) ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ሰምተናል ፣ ህዝቡ የዚህን ቃለ ምልልስ ምንነት በቅጡ ስላልተረዳው ፣ እባካችሁ አስተርጉሙልን ። በያመቱ በ 11 ፐርሰንት ማደግ ምን ማለት እንደሆነ እባካችሁ አስተርጉሙልን ። የህዝቡን ውጣ ውረድ ፣ የኑሮ ውድነት ፣ ስደት ፣ ረሃብ ፣ ሥራ አጥነት እና ወዘተ ላይ ያለን አለመግባባት ፣ አሁን በቀደም የገንዘቤ ድባባን አስተርጏሚ ከሰማሁ በሗላ ፣ የችግሩ ዋና ብልት ያለው የትርጉም መዛባት ላይ እንደሆነ ገብቶኛል ገብቶኛል ፣ ስለዚህ እባካችሁ ፣ ይህንን መከራ ፣ ይህንን ስቃይ ፣ << ለሰማያዊ ፓርቲ ፣ በምርጫ ሰሞን ፣ ያለውን ሀገር አቀፍ ፖሊሲ እንዲያብራራ በሰጣችሁት ስድስት ደቂቃ ውስጥ >> ለናንተም ስድስት ደቂቃ እንስጣችሁ እና ችግሩን ከመሰረቱ አስተርጉሙልን። እባካችሁ እስክንድር የታሰረው በትርጉም ስህተት ሳይሆን አይቀርምና ፣ ድጋሚ ምን ማለት እንደፈለገ እንሰማው ዘንድ ብ ቢፈቀልንስ ? ባንድ ወቅት ሸበላው ጠቅላይ ሚንስቴር ( ሟች ) ፣ የችግሩ ስር ያለው እአርታ ዔርትራ ነው ብለው ነበር ። ከዚያ ወዲያው <<ዔርትራ አይደለም >>ም ብለው ነበር ። እሳቸውም የትርጉም ችግር እንደነበረባቸው አሁን ቆይቶ ነው የገባኝ ። ስለሳቸውም ስትሉ ስትሉ አስተርጉሙልን ። የ MIT ፕሮፈሦር Sanjay Mahajan እንዲህ ይላል ” In problem solving, as in street fighting , rules are for fools: do whatever it works don’t stand there.” ስለዚህ የፈጀውን ይፍጅ አስተርጉሙልን ። የኔ ሰው ገብሬ እብድ ስለሆነ ነው የሞተው ፣ ቀውስ ስለሆነ ሆነ ነው ሲባል በግዜው በጣም ተናደን ነበር ፣ ባንክ ዘራፊዎች ናቸው በአጋዥ ( አግዓዚ ) ጥይት የተገደሉት ሲባል ፣ ይህ ጭካኔ የተሞላበት ክህደት ነው ብለን ነበር ፣ ህጻን ነብዩ ( በ 6 ዓመቱ ) በመንግስት ወታደሮች ጥይት በአደባባይ ሲገደል ፣ ይህ አውሬነት ነው ብለን ነበር ፣ ሽብሬ ጥይት ከትምህርት ገበታዋ ሲያስነሳት ፣ አሰፋ ማሩን ድብደባ የልጆቹ አባት እንዳይሆን ሲያደርገው ፣ አንዷለም ልጆቹን እንዳያሳድግ ፣በሽብር በሽብር ተከሶ ወህኒ ሲወርድ ፣ ኡስታዝ አቡበከር እና የእምነት ጏደኞቹ ፣ መጅሊስን አትንኩ ፣ የማታውቁት ነገር ውስጥ አትግቡ ፣ ሃይማኖታችንን ለኛ ተዉ ብለው በማለታቸው ለእስር እንደታዳረጉ እናውቃለን ፣ ሳስበው የመንግስት አስተርጏሚ ጉዳዩን አዙሮ ተርጉሞት ይሆን የሚል ነገር ጭንቅላቴን ስለመታው ነው ፣ እስኪ ነገሩን በገንዘቤ ዲባባ አስተርጏሚ ድጋሚ እዩልን ? ፕሊስ !
አባይ ይገደባል ስትሉ ለሕዝቡ ነበር የመሰለን ፣ ለካ የህዝቡን ጉሮሮ ደሞዛቸውን እየቆረጠ አባይ ይ–ገድባል ነው ? ለማንኛውም እኩሌታው ሕዝብ ይህንን ነገር አያውቅምና ፣ እባካችሁ አንድዜ ይህንን የሩጫ ተርጏሚ አስቸግሩና ፣ ስለሁኔታው ፣ በየወረዳው 5 ለ አንድ ሕዝቡን ጠፍሮ ፣ የዚህ የአባይን ነገር ያስተርጉምልን ። ኦባማ የአፍሪካ መሪዎችን ሲወቅሱ ፣ አቶ ኃይለማርያም ያጨበጭቡ ነበር ፣ ይስቁ ነበር ፣ እባካችሁ የአቶ ኃይለማርያምን ጭብጨባ እና ሳቅ አስተርጉሙልን ። ጋሽ አቦማ በቦሌ አለማቀፍ አየር ማረፊያ ፣ አበባ ከበረከቱላቸው ልጆች ጋ ፎቶ ሲነሱ ፣ ሌሎች << ትላልቅ ባለሥልጣናት እሳት እንደበላው የደመራ እንጨት ተጣመው ፣ ፎቶ የሚነሳውን ሰው ለማየት ሲሞክሩ አይተናል >> ፣ እባካችሁ ፎቶ ምን ማለት እንደሆነ አስተርጉሙላቸው ።
ጋሽ ቴዎድሮስ አድሃኖም አንዳርጋቸው መጽሐፍ ጽፎ እየጨረሰ እንደሆነ ነግረውናል ። ሳስበው የትርጉም ስህተት ይመስለኛል ፣ ከተቻለ ፣ አንዳርጋቸው ማለት ምን ማለት እንደሆነ እኛ ኢንተርጉምላቸው ፣ እነሱ ደሞ መጽሐፍ ምን እንደሆነ ያስተርጉሙልን !
እስከዛሬ እንዲህ የተሰቃየነው በትርጉም ሻተት መሆኑን ሳስብ ክፍት ይለኛል። ሆድ ይብሰኛል ። እድሜ ለገንዘቤ ዲባባ አስተርጏሚ ፣ ከአሁን ወዲያ እንዲህ ያለው አለምግባባት ይኖራል ብለን አንስብም ። በሉ አስተርጉሙልን !