‹‹ታላቁን መሪ›› ‹‹ አድንቀን ›› ፊታችንን ወደየሥራችን እንመልስ// Girma Bekele
በቅርቡ የቀድሞዋ ‹‹ቀዳማይ እመቤት›› (ይቅርታ እርሳቸውም ‹‹የቀድሞው የታላቁ መሪ ባለቤት›› እንዲባሉ ስለመፈለጋቸው ስላልሰማሁ ነው) የቀድሞውን ጠቅላይ ሚ/ር ‹‹ታላቁ መሪ ›› ተብለው እንዲጠሩ መመሪያ ማውረዳቸውን ሰምተናል፡፡ ይህቺ አጭር መልዕክት እኔ ከህወኃት ጉባኤ ይህ ስም እንደሚገባቸው የተረዳሁ መሆኑን (በግሌ) አሳውቄ ስለጉባኤው የምናወራውን አብቅተን ወደየተግባራችን እንድንመለስ ለማሳሰብ ነው፡፡ መነሻዬም ወዳጄ ዳዊት ሰሎሞን ከናይሮቢ ያቀበለን መረጃ ነው፡፡ ‹‹ በግዳጅ ተገፍትረን ለተባረርነው የ‹‹መተካካት›› ሰም ተሰጠው እንጂ አምነንበት አይደለም ፡፡›› የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡ ይህንን አቶ መስፍን ይበሉትም አይበሉት እንዳልተባለ ከማመን እደዚያ እንደተፈጸመ ለመቀበል ከቀድሞው -ቀድሞ ጠ/ሚ/ር (እርሳቸው ማን ሊባሉ እደሚገባ ባለቤታቸው መመሪያ አላወረዱምና ነው) አቶ ታምራት ላይኔ ከሰጡት ምስክርነት፣ ከአቶ አሰገደ፣ ገብሩ፣ ኤርሚያስ… መጻህፍት… በቂ ማስረጃና መረጃ አግኝተናልና ታላቁ መሪ እያልን ወደ ምልከታችን እንዝለቅ፡፡አዎን በህወኃት ውስጥ የትግል አጋሮቻቸውን የቀድሞ አለቆቻቸውን ጨምሮ ከትጥቅ ትግሉ ወቅት እስከ ዕለተ ሞታቸው (ይህ ያስቀጣ ይሆን አላውቅምና በቅንፍ ውስጥ እስከ ‹‹ዕለተ መስዋዕትነታቸው ›› ማለቴ ይመዝገብልኝ) ‹‹ታላቁ መሪ›› እውነትም ‹‹ድርጅቱ/ኢህአዴግ›› እንደነበሩና የፈለጉትን ሲያሳስሩ ፣ ያልፈለጉትን ሲያባርሩ በፈላጭ ቆራጭነትና ‹‹አይተኬ ባለራዕይነት›› ህወኃትን ሲያሽከረክሩ እንደነበር ከዚህ ከአቶ ሥዩም መስፍን ‹‹አባባል›› እና ከቀድሞዋ ቀዳማይ እመቤት ‹‹ መመሪያ›› ፣ እንዲሁም ከሞቱ/ከተሰዉ ከሶስት ዓመታት በኋላም የእርሳቸው ራዕይ እየሰራ መሆኑን የቀድሞዋ ቀዳማይ እመቤት በህወኃት ጉባኤ ምርጫ ካገኙት ድምጽ እንረዳለን፡፡ ይህንንም የሚያረጋግጠው በጉባኤው በጡረታ የወጡትና ተመልሰው በድምጽ ከተሳተፉት፡ ጋር በሥልጣን ሽኩቻ ከመግባታቸውና ‹‹ቤተ መንግስቱ በቀሚስ አስተዳደር ሥር መውደቁ›› እስከተነገረን ቀን ድረስ ብዙ አይታወቁም ነበርና በሰሩት ሥራ ነው ማለት ስለሚከብድ ነው ፡፡ አዎን በ‹‹ ታላቁ መሪ›› መንፈስ የሚመራው ህወኃት ቀድሞም እነዚህን ‹‹ጡረተኞች›› በድርጅቱ/ በታላቁ መሪ እርምጃ አሽቀንጥሮ ጣለ፣ ዛሬም ‹‹ ለጡረታ አልደረስንምና ተመልሰን እንግባ ›› ጥያቄ ሲያቀርቡ ጉባኤው ተቀብሎና አስተናግዶ በ‹‹ ታላቁ መሪ ራዕይ›› መሰረት ዛሬም በድጋሚ በድምጹ ቀጣቸው፤ ራዕዩን የማስፈጸም ተልዕኮውን ይዞ ቀጠለ ፡፡ ስለዚህ ህወኃት ማለትም የአገሪቱ ገዢ ፓርቲ ( ከዚህ በቀደመው መጣጥፍ ሌሎቹን አጃቢዎች እንተዋቸው ብያለሁና ) ቢከፋፈል፣ ባይከፋፈል፣ አባይ/መቀሌ ቢያሸንፍ ፣ደብረ ጽዮን/አዲስ አበባ ቢሸነፍ … ከ‹‹ታላቁ መሪ›› ራዕይና ካስቀመጡት ‹‹ትክል›› ከፋፋይ ፖሊሲና በአብዮታዊ ዲሞክራሲ እየተመራ ከሚፈጽመው ሴራ፣ደባና ክህደት/ እንደየኢታማጆር ሹሙ በጉባኤው መገኘትና ህገመንግስቱ/ ሳንቲሜትር አይዛነፍምና ሌሎቻችን ባለፉ የገዢው ፓርቲ (ህወኃት) እና አጃቢዎቹ ጉባኤ አንዳችም የተለየ ነገር እንዳላየነው ፣ በቀጣዩ የገዢው ፓርቲ ጭምብል (ኢህአዴግ) ጉባኤም አንዳችም የተለየ ነገር እንደማናገኝ አውቀን ስለዚያ የምናጠፋውን ሃብት( ጊዜ፣ ገንዘብ/ ውድ የቴሌ የአየር ጊዜ/ እና ዕውቀት) ለራሳችን ለማዋል ከነርሱ አጀንዳ በጊዜ ተፋተን ፊታችንን ወደራሳችን የጋራ ጉዳይና ተግባር እንድናዞር በአክብሮት አሳስባለሁ፡፡ ይህን በእየጻፍኩ ባለሁበት ደግሞ የአቤል ጉዳይ በተመሳሳይ የፌስቡኩን ዐምድ እየወረረው ነውና በዚሁ መልክ ይታሰብበት፣ ያሊያም ለ‹‹መማሪያነት›› ካስፈለገ በማስረጃ፣ መረጃና ሎጂክ የተደገፈ ሙሉ ሥዕሉን በሚያሳየን ከጭፍንነት በተላቀቀ መንገድ ይቅረብልን እንጂ የሁለት ወገን ‹‹መሰረት የለሽ›› እሰጥ/አገባ አይሁንብን፡፡ በቸር ያገናኘን፡፡