ዝም ብዬ ሳስበው… ፌደሬሽኑ ራሱን ይፈትሽ ዘንድ ግድ ነው!

ዝም ብዬ ሳስበው…  ፌደሬሽኑ ራሱን ይፈትሽ ዘንድ ግድ ነው!

ዝም ብዬ ሳስበው… Yohanes Molla

ባጋጣሚ፣ ባለቀ ሰዓት በተገኘ ዕድል ሾልካ የግል ጥረቷንና ውጤታማነቷን ባታሳይ ኖሮ፥ መሰረት ደፋር የምትባል ልበ ሙሉ ጀግና አትኖርም ነበር።

አክስቷ ደራርቱ ቱሉ ቀድማት ጀግንነቷን ባታስመሰክርና እህቷ በቀሉ ዲባባ ቀድማ ሩጫው ውስጥ ባትቀላቀል ኖሮ፥ ጥሩነሽ ዲባባ የምትባል ብርቅዬ ጀግና አናውቅም ነበር።

ጥሩነሽ ቀድማቸው ሮጣ ታዋቂነቱን ባትቀዳጅና በጀግንነት፣ የተሰሚነቱንም አቅም ባታተርፍ ኖሮ፥ ገንዘቤ ዲባባ የተባለች ጀግና እርግብ አናውቅም ነበር።

ቀነኒሳ በቀለ ባይኖር ታሪኩ በቀለ ላይታይ ይችል ነበር።
.
.
ጀግኖች አትሌቶቻችን ራሳቸውን ለማሳየትና አቅማቸውን ለማሳወቅ፥ መጀመሪያ እንደምንም፣ በፋራም ባራዳም መሽሎክ መቻላቸው ቀዳሚ ሁኔታ እንደሆነ ይሰማኛል። እኔን እንደተሰማኝ እነሱን ሲሰማቸውና መገፋታቸው ሲበዛ፥ መሹለኪያቸውን ማሰባቸውና፣ ከሩጫው ጎን ለጎን እሱን ለማሳካት ላይ ታች ማለታቸው የሚቀርም ጉዳይ አይሆንም።

ሌላም ሌላም፥ አስባለሁ።

በሀሳቤ መካከልም፣ ችሎታ ሳያጡ ያልታዩ መሰረቶች፣ አቅም ሳያንሳቸው የተረሱ ጥሩነሾች፣ መሯቸው ሌላ ሌላ ሞያ ውስጥ የገቡ፣ ስራ ፈትተው የሚባክኑ ገንዘቤዎች፣ ለሌሎች አገራት ዜግነት ቀይረው የሚሮጡ ብዙ ታሪኩዎች ባይኔ ይዞራሉ።

ዝም ብዬ ሳስበው፥ ለሰው አገር የሚሮጡት ሯጮች ባይገፉ ኖሮ እዚህ ምን ጎድሏቸው ይሸሹ ነበር? እላለሁ። (በደሞዝ የሚተዳደሩ ሆነው ደሞዝ አነሰን አይሉ ነገር ሽልማቶቻቸው ሀብት ናቸው። …በጋራ ሆነው ነው የሚወዳደሩትና ሮጠው ሲልቁም ይታያል። ደግሞ የሰው ሀገር አታሏቸው እንዳይባል፥ ሰው የኢኮኖሚ ወይ የፖለቲካ ስደተኛ ካልሆነ፣ ሀገሩ መኖር አይጠላ። እነሱም ቢሆኑ፥ በሰው ማሊያ ሮጠው፣ ላባቸውን በሰው አገር ባንዲራ ጠራርገው፣ በሰው ሀገር ስኬት፥ የውሸት የውሸት ሮጠው፣ እዚሁ ቅሪት ለማኖር፣ ለአገር ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ ለማድረግ መጣራቸው አልቀረም።)

መስፈሪያና መመዘኛው ልክ ቢሆንማ፥ ሁሉም በላቡ በወዙ ለማለፍ ይበረታ፣ እላይ ታች ይጥር፣ ቀን ከሌሊት ይሰራ ነበር።

ፌደሬሽኑ ራሱን ይፈትሽ ዘንድ ግድ ነው!