ዛሬም እንደ ትናንቱ— የቃላት ጨዋታ? ያስተዛዝባል፣ ያጠያይቃል // ግርማ በቀለ

ዛሬም እንደ ትናንቱ— የቃላት ጨዋታ? ያስተዛዝባል፣ ያጠያይቃል// ግርማ በቀለ
የዛሬውን ጽሁፍ በጥያቄ መጀመር ፈለግሁ፡፡ ‹‹ ለሰው ልጅ ከትናንቱ/ከስህተቱ ለመማር ስንት ጊዜ ይፈጅበታል፣ ለመማር ስንቴ መውደቅ ይኖርበታል?›› በሚል፡፡ ይህን ጥያቄ በአገርኛ አባባል በቀላሉ መልሼ ወደ መነሻ ኃሳቤ ላምራ፡፡ ደጋግመን ወድቀናልና መልሱ ‹‹ ጠዋት ስትወጣ የመታህ እንቅፋት/ድንጋይ ማታ ስትመለስ ከደገመህ ድንጋዩ አንተ ነህ፡፡›› ሚለው ይሆናል፡፡ ይህን ጥያቄና ምላሽ ያነሳሁት ከሰሞኑ በተደረገና ሊደረግ በታቀደ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የታዘብኩትንና ሥጋቴን አንስቼ ለቀጣዩ ምን መደረግ አለበት ለሚለው የሚሰማኝን ለመግለጽ ነው፡፡

ግርማ በቀለ
ግርማ በቀለ

1. ትዝብት፡- በመድረክ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ፤
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የ ‹‹መድረክ ›› ጠቅላላ ጉባኤ ተሰብስቦ ምርጫ 2007 ን ገምግሞ የደረሰበትን ድምዳሜ ገልጾልን መነሳቱን አድምጠናል፡፡ መቼም አንድ ድርጅት (ፓርቲም ይሁን የፓርቲዎቸ ስብስብ) አቅም ጊዜና ሁኔታው ቢፈቅድለት በየሳምንቱ አባላቱን ሁሉ ወይም አመራሩን እያገናኘ ቢያወያይ አንዳችም የሚያስተዛዝብም ሆነ የሚያጠያይቅ ነገር የለውም፤የተወደደ ነው፡፡ የአንድ ድርጅት የዕለት ተዕለት ተግባር ስለሆነ ብቻ ሳይሆን በየደረጃው ድርጅቱ የወሰዳቸውን አቋሞች ያከናወናቸውን ተግባራት ከውጤትና ከግቡ አንጻር ለአጠቃላይ አገራዊ ተልዕኮው ያበረከተውን አስተዋጽኦ ለመመልከት ስለሚረዳውና በሂደቱ ከተመዘገበው ውስንነትና ጥንካሬ ባለው መልካም አጋጣሚና አስጊ/ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ለቀጣዩ ወሳኝ ትግል ግልጽ/የጠራ ኃሳብ ላይ የቆመ የትግል ስትራቴጂና ዓላማ ለመቅረጽ፣ የማስፈጸሚያ ስርዓት ለመዘርጋት እንዲያስችል ነው፡፡ከዚህ አንጻር ከመድረክ ጠቅላላ ጉባኤ ይጠበቅ የነበረው ፤ ከአጠቃላይ ነባራዊና በምርጫ 2007 ሂደት የታየውንና ምርጫውን ተከትሎ እየሆነ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በመገምገምና በማገናዘብ፡-
1ኛ/ ትናንት በመሪነት ያስፈጸመው ‹‹ለምን ደጋግመን ወደቅን›› ጥናትን በዝርዝርና ጥልቀት መርምሮ ለቀጣዩ ትግል የጠራ ኃሳብ በመቀመር ግልጽ አቅጣጫና ዓላማ ማስቀመጥ፤
2ኛ/ የግንባሩን ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ በማሻሻል በግንባሩ ውስጥ ያሉትን ፓርቲዎች ወደ ውህደት ማሸጋገር እና ሌሎችን ፓርቲዎች ወደ ግንባሩ/ውህዱ ፓርቲ የሚመጡበትን ስልት መቀየስ፤
3ኛ/ በነዚህ መሰረት ለቀጣዩ ትግል ውጤት ተኮር የሁለንተናዊ ለውጥ አደረጃጀት/መዋቅርና አመራር የሚፈጠርበትን ሁኔታ ማመቻቻትና …
ይህን ስንጠብቅ ከምንም በመነሳት በአየር ላይ አልነበረም፡፡ ከጉባኤው አስቀድሞ ‹‹መድረክ በህልውናው ጭምር ለመወሰን የሚያስችል ጉባኤ ሊያካሂድ ነው›› የሚለውን መልዕክት ስላደመጥን፣ ትናንት በገዢው ፓርቲ ላይ ሂስና ተቃውሞ በጠንካራ ቃላት ሲቀርብ እኛ ‹‹ተሳዳቢ›› አይደለንም ይሉ የነበሩ የመድረክ አመራሮች ከተለመደው በተለየ ምሬት ተቃውሞ ሲያሰሙ ስላስተዋልን፤ከምርጫው በፊት በዚህ ምርጫ ካለፈው ምርጫ የተሻለ ውጤት ካላስመዘገብን ( ይህ ማነጻጸሪያ በራሱ ችግር ቢኖረውም) ከእንግዲህ የትግሉ አመራርነት ‹‹ይበቃናል›› ዓይነት የመረረ ኃሳብ በመስማታችንና በምርጫው ቅስቀሳ ወቅት ህዝቡ በራሱ ተነሳሽነት ያሳየውን ድጋፍና ያስተላለፈውን ‹‹ተባብራችሁ ምሩን›› ጥያቄ ፣በየአባል ፓርቲዎች የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ ካሉት ወጣቶች፣ እና መድረክ ገዢው ፓርቲ ከምርጫ በኋላ ወሰደብን በሚለው የበቀል እርምጃ ደጋግሞ ካሰማው ጩሄት ጋር አገናዝበን በመመዘን ነበር፡፡
ይሁን እንጂ የጉባኤውን ውጤት ስንሰማ እንደተነገረውም እንደተጠበቀውም ሳይሆን በ‹‹ሥራ የፈታ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል›› ምሳሌያዊ አነጋገር የሚገለጽ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ የጉባኤው ተልዕኮና ውጤት ከተጠበቀው ጋር ሲተያይ ‹‹ፍዬል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ›› አድርጎታል፡፡ ማለትም-
መድረክ በዚህ ስለቀጣዩ ትግል ከማንም የሚሰማ ጠፍቶ በጉጉት በሚጠብቅበትና ህዝቡን አስተባብሮ ለሁለንተናዊ ለውጥ የሚመራ የትግል ማዕከል በእጅጉ በሚፈለግበት ሰዓት ጉባኤ ሲጠራ ይህንን ክፍተትና ውስንነት የሚሞላ እንዲሆን ከላይ በገለጽናቸው ተነስቶ ይቅርና በበጎ ምኞትና ቅን ፍላጎትም ቢሆን በማንም ላይ የሚፈረድበት አይሆንም፡፡ ይህ የሆነውም ህዝቡ የምርጫን ነገር በተለይም ከምርጫ 2007 ሂደትና ውጤት አንጻር ገምግሞ ጨርሶ የምርጫን ነገር ‹‹የውሾን ስም ያነሳ….›› ብሎ ደምድሞ በተነሳበትና በቀጣይ ምንና እንዴት፣ በማን እየተመራን ለምን ውጤት? የሚሉ ጥያቄዎችን አንስቶ መልስ በሚጠብቅበት ሰዓት ነው፡፡ ይህንን ከመድረክ ጉባኤ ከወጣው የአቋም መግለጫ አንጻር በሚመለከት ነው ትዝብታችን ፡፡
በዚህ ወሳኝ ወቅት መድረክ ትናንት የነገረንን ‹‹ ምርጫው ነጻ፣ፍትሃዊ፣ …. አይደለምና አንቀበለውም፣ ( ከዚህ በፊት ከ33ቱ፣ ከዚም በኋላ በሂደቱ በወላይታ ዞን ከ8 ፓርቲዎች ጋር ያቀረበው ጥያቄዎች ሳይመለሱ ወደ ምርጫ ለምን ገባ ? የሚለውን ሳናነሳ)፣ ፕ/ት ኦባማ ምርጫውን ዲሞክራሲያዊ ማለታቸው አግባብ አይደለም፤ … ‹‹ነጻና ገለልተኛ›› አጣሪ ኮሚሽን ተቋቁሞ ይጣራ…፣…››፣ ብሎ፣ በየጉባኤውና በየጊዜው ስለሚነሳው የውህደት ጥያቄም በገደምዳሜ ነካክቶ አልፎታል፡፡ በእውነቱ እነዚህ ሰዎች ዛሬም እዚያው ናቸው ወይስ ህወኃት/ኢህአዴግ ጽፎ የሰጣቸውን ነው ያነበቡልን ወይስ …. ? ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድድ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ከዚህ ሥርዓት ጋር 24 ዓመት የዘለቀ፣ በተደጋጋሚ ምርጫዎች የተሳተፉ ፓርቲዎችን ያቀፈ፣ በተለይ ደግሞ በምርጫ 2007 ሂደት ያለፈና ውጤቱን የተመለከተ፣ ከምርጫው ውጤት በኋላ በዕጩዎቹ፣ በታዛቢዎቹ፣ በአባላትና ደጋፊዎቹ በተፈጸመው የበቀል እርምጃ ስለደረሰው ግድያ፣እስራት፣ማፈናቀል … በየጊዜው ‹‹መርዶ›› የሚነግረን አመራር ተነስቶ ስለ ‹‹ነጻና ገለልተኛ ›› አጣሪ ኮሚሽን/ተቋም መመስረት ሲጠይቅ የጤና ነው ትሉታላችሁ? ኢትዮጵያዊ ‹‹ጨዋነት›› ይዞን ካልሆነ ከዚህ (ከጤናው) ባለፈ ብንጠረጥርስ ይፈረድብናል?
ህዝብ ይጠብቅ የነበረው ውጤቱን አንቀበልም ብለዋልና — ‹‹ ካልተቀበሉ ምን ለማድረግ አስበዋል ? እንዴትስ ይመሩናል? ›› ወደቤት አንገባም ብለውናልና ‹‹በቀጣይ ምን ዝግጅት አድረገው ሊነግሩን ነው?››… ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ሆኖ ባለበት ፖለቲካውን ቅንጣት ወደፊት የማይገፋ ወይም ስለመግፋት ምልክት የማያሳይ የ‹‹አንተኛም›› ቀረርቶ ከንቱ ድካም ነው፡፡ በገደምዳሜ ስለሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ የተነሳው ያልተፈለገ ‹‹ ማስተዛዘኛ›› በቦታው አይደለም፤ ስለሙስሊሙ ኮሚቴ ከተነሳ መባል የነበረበት ስለህዝባዊ ትግል አመራር ከ‹‹ድምጻችን ይሰማ›› ተምረን ለትግሉ ህዝባዊ መሰረት አበጅተን በቀጣይነት ተከታታይ ጥያቄኣችንና ተቃውሞኣችንን ከዳር እስከዳር ህዝቡን በማንቀሳቀስ እንመራለን የሚልና ለዚህ ተፈጻሚነት ለሁሉም የለውጥ ኃይሎች (የፖለቲካ፣ ሲቪክ፣ የኃይማኖት፣ የማኅበረሰብ … ወዘተ አደረጃጀቶች) የነጻነት ትግል ትብብር ጥሪ ነበር፡፡ ከዚህ ውጪ የሆነውና ሊሆን የተዘጋጃችሁት ‹‹እየተቃወሙ ለመኖር›› የሚደረግና እየተቃወሙ መኖር ‹‹ልዩ ጥቅም›› የሚያስገኝ ዓይነት ትዝብት ላይ ይጥላልና ለህዝብ ትዝብት ከምንዳረግ(ያውም ያልተዳረግን ከሆነ) ቆም ብለን የግንባሩን አቋም፣አካሄድ፣ አመራር፣… እንፈትሽ፡፡
በዚህ መሰረት መድረክ ከ‹‹አዛውንቶች የትዝታ ክበብነት›› ወደ ‹‹የነጻነት ትግል ማዕከልነት›› መቀየር፣ ፓርቲን ከመሪው እኩል እንዲታይ የሚያደርገውንና አመራሩንም እንደ ጎበዝ አለቃ የሚያስቆጥረውን ‹‹አይነኬውን የጽዋ ማኅበር መሰል የዙርና በአንድ ሰው ላይ የተማከለ አመራር›› በ ‹‹ውጤት ተኮር የሁለንተናዊ ለውጥ ብቃት ያለው›› (የጋራ/የቡድን አመራር ስርዓት›› መለወጥንም ከግምት በማስገባት) መተካት አለበት፤ ግንባሩም ዛሬ ዛሬ የእድር ሚናም ከ‹‹መርዶ ነጋሪነት›› ዘሏልና ወደ ‹‹ትግል መድረክነት›› ፣ በራስ ቃላት ‹‹ከመታበይ›› ወደ ‹‹ተግባር ››ይሸጋገር ብለን በግልጽ ለመነጋገር የሚያስደፍር ደረጃ ላይ ደርሰናልና ….. የህዝብ መሪ ነን ለማለት ከህዝብ አርቆ መመልከትና ቀድሞ መገኘትን ቢጠይቅም ካልተቻላችሁ ቢያንስ ቢያንስ ከህዝብ እኩል ለማየትና ከጎን ለመራመድ ወደ ህዝቡ ወርዳችሁ ለማድመጥ ሞክሩ፣… ህዝብ እየጎተታችሁ ተመልሳችሁ ልትመሩት አትችሉምና …. ፣ ትዝብቴን ቋጨሁ፡፡ በቀጣዩ ክፍል ስለሚጠበቀው የሰማያዊ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ ያለኝን ሥጋትና ማጠቃለያ ኃሳቤን ይዤ እመለሳለሁ፣ እስከዚያው በቸር እንሰንብት//