ኣብራሃ ደስታ – ቃሊቲ የታሰረው ኣንበሳ

Amdom Gebreslasie

ሰሞኑ በመድረክ ኣስቸኳይ ኣጠቃላይ ጉባኤ ለመሳተፍ ብየ ወደ ኣዲስ ኣበባ መጥቻለው።
በመድረኩ ስብሰባ በዘንድሮ ምርጫ ኢህኣዴግ “መቶ ፐርሰንት(100%) ኣሸንፍያለው” በሎ በማወጅ ለራሱ ተዋርዶ የዓለም መሳቅያ መሳለቅያ ኣድርጎን መሰንበቱ ይታወቃል።

መድረክም የዚህ ምርጫ ውጤት እንደማይቀበለው ኣስቀድሞ የገለጸ ሲሆን የኢህኣዴግ እርምጃ በሰለማዊ ፖለቲካዊ ፉክክር ህዝቡና ፖለቲካዊ ድርጅቶች ተስፋ እንዲቆርጡ ያቀደው ሴራ ለማክሸፍ ኣዲስ የሰለማዊ ትግል ስልቶችና ስትራተጂዎች ነድፎ በማውጣት ከምርጫ የዘለለ ትግል ለማድረግ እንደተዘጋጀም ያስታወቀበት ሁኔታ ፈጥሮ ኣልፏል።

በመድረክ ስብሰባ መዝግያ የኣቋም መግለጫም የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲያሰፋ፣ የህግ ልእልና እንዲጠበቅ፣ የሙስሊም ማህበረሰብ መፍትሄ ኣፈላላጊ ኮሚቴዎች ከ7- 22 ዓመት የፈረደው የኣሸባሪነት ፍርድ ውጤቱ ለሃገሪቱ ከፍተኛ ኣደጋ ያለው በመሆኑ በውይይት እንዲፈታ፣ በገዢው ፓርቲ የተገደሉ እስከ 8 የሚደርሱ የመድረክ ኣባላት ፍትህ እንዲሰጣቸውና ገዳዮቹ ወደ ህግ እንዲቀርቡ እንዲደረግ፣ እንደ ኣብራሃ ደስታ፣ እስክንድር ነጋ የመሳሰሉት ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ከእስር እንዲለቀቁ፣ በኣገራችን ተከስቶ ያለው ኣስከፊ የድረቅ ኣደጋ መንግስት ኣስፈላጊው ቱክረት በመስጠት ኣስቸኳይ እርዳታ እንዲያቀርብና ሌሎች ኣበይት ወቅታዊ ኣንገብጋቢ ጉዳዮች ትኩረት ተሰጥቷቸው መፍትሄ እንዲበጅላቸው ጥሪ ኣቅርበዋል።

ኣብራሃ ደስታና ሌሎች ፖለቲከኞች፣ ብሎገሮችና ጋዜጠኞች ያሰረው መንግስት ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ የተጠየቀው መንግስት ምላሽ ገና ኣልሰጠም።

ቃሊቲ እስር ቤት ያለው ኣብራሃ ደስታ ለመጠየቅ ህጀ ነበር።
ኣብራሃ ደስታ መጠየቅና ማግኘት የሚቻለው ከስድስት እስከ ስድስት ተኩል ሲሆን ይህም ሌሎች ታራሚዎች በማይጠየቁበት ሰኣት ነው።

የመጀመርያ ሙከራ ያደረግኩት እሮብ ቀን ነበር። የጥበቃ ሰራተኞች የተለያዩ ምክንያቶች በመፍጠር ሳላገኘው ተመለስኩ። ከመቐለ ድረስ መጥቼ ከቅሊንጦ ወደ ቃሊቲ እስር ቤት የተዘዋወረው ጀግናው ኣብራሃ ደስታ ሳላገኝ መመለስ ልቀበለው ስላልቻልኩ እሮብ 7 / 12 / 2007 ዓ/ም እንደገና በመሞከር ተሳክቶልኝ ጎበኘሁት።

ኣብራሃ ደስታ ከቅሊንጦ እስር ቤት ከተዘዋወረ በሗላ ሊጎበኙት የተፈቀዱለት ሰዎች ከኣምስት በታች ናቸው።
ይህም ከቅሊንጦ እስር ቤት ሲነፃፀር ከሰው እንዳይገናኝ የተከለከለበትና ምግብ ከውጭ እንዳይገባለት በማድረግ ኣስቸጋሪ ሁኔታ ኣጋጥሞታል።
ይህ ችግር ቢያጋጥመውም ጀግናው ኣብራሃ ደስታ ወኔ፣ ብርታትና ጀግንነት እንደ ዘውትር ሙሉ ነው።
ቃሊቲ ሁኖም ስለራሱ ሳይሆን ስለ ሌሎች ሰዎች ይጨነቃል።
ያው የተለመደው ጀግነት፣ ፅናትና ትእግስት ምንም ኣልተነካም።

በመላ ዓለም የምትገኙ ወዳጆቹ ለኣብራሃ ያላቹ ኣክብሮትና ኣድናቆት ገልጨላቹሃለው። እሱም በተራው ከጎኑ የተሰለፋቹና የምትደግፉት ሁሉ ምስጋናው እንድገልፅለት ኣደራ ብሎኝ የኸው ኣደራየ ተወጥቻለው። በቃሊቲ እስር ቤት ያለው ኣምበሳ ይወዳቹሃል።
እናንተስ ትወዱት የለም….?
የኣብራሃ ደስታ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ነሓሴ 14 / 12 / 2007 ዓ/ም ነው። በኣዲስ ኣበባ የምትገኙ ዜጎች በችሎቱ እንደምትገኙ ተስፋ እናደርጋለን።

ነፃነታችን በእጃችን ነው..!

IT IS SO…!

Amdom Gebreslasie's photo.