ተማሪዎች የጫሩትን ፍርድ ቤት አይደፍነውም (ዳዊት ሰለሞን)

ተማሪዎች የጫሩትን ፍርድ ቤት አይደፍነውም (ዳዊት ሰለሞን)

ለአጼ ኃይለ ስላሴ ስርዓት መገርሰስ ተማሪዎች የተጫወቱት ሚና የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ኃይሌ ተማሪዎች የቆሰቆሱትን እሳት የተወሰኑትን በማሰር፣የውጪ የትምህርት እድል እንዲያገኙና ራቅ እንዲሉ በማድረግ፣ወደ መንግስት ኃላፊነት በመሳብና በትዳር በማሰር የተማሪዎቹን እንቅስቃሴ ለማኮላሸት ሞክረው ነበር — አልቻሉም እንጂ፡፡
ደርግ የመጀመሪያውን ፈተና ተፈትኖ የወደቀውም በተማሪዎች ነበር፡፡ዱላውን በከተማ ትግል መቋቋም እንደማይቻል ያመኑ ተማሪዎች በረሃ ወርደው የስርዓቱን መጨረሻ ፈጠሩ፡፡የቀድሞዎቹ ተማሪዎች አራት ኪሎ ከደረሱ በኋላ የተማሪነት መነጽራቸውን በማውለቃቸው በአደባባይ የተጋጩት ከተማሪዎች ነበር፡፡ይህው ላለፉት 24 ዓመታትም ተማሪዎችና ኢህአዴግ በጎሪጥ እንደተያዩ አሉ፡፡
የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከቅርብ አመታት ወዲህ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ከራሽንና ከጎጥ ጋር የተቆራኙ ብቻ ናቸው በማለት ትችት የሚሰነዝሩባቸው አካላት ቢኖሩም ስርዓቱ በተቋማቱ ውስጥ ይስተጋቡ የነበሩ ህዝባዊነት ያላቸው ጥያቄዎች እንዲታፈኑ ተግቶ ሲሰራ መቆየቱን የሳቱት ይመስለኛል፡፡
የሆነስ ሆነና በኢህአዴግ የእስካሁን የስልጣን ቆይታ ታሪክ ከፍተኛ ተግዳሮት የፈጠረ ምናልባትም የስርዓቱን ቀብር የሚያፋጥን እንቅስቃሴ የተወለደው በተማሪዎች መሆኑ ነው፡፡ከእስካሁኑ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የአሁኑን ለየት የሚያደርገውም እንቅስቃሴው በመንፈሳዊ ትምህርት ቤት ውስጥ ይማሩ በነበሩ ተማሪዎች የተጫረ መሆኑ ነው፡፡የአወሊያ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከአራት ዓመት በፊት በግቢያቸው ተወስነው ያነሷቸው ጥያቄዎች ነገሮችን በሰለጠነ መንገድ የመፈተሽ ድፍረት በሌለው መንግስት የታየው የአወሊያን መውጫና መግቢያ በመዝጋት ጥያቄውን ከእነ ጠያቂዎቹ ማፈን እንደሚቻል ነበር፡፡
ተማሪዎቹ ከአፋኞቻቸው ብዙ ርቀት ተጉዘው ማሰብ የቻሉ በመሆናቸውም ያነሷቸውን ጥያቄዎች የሐይማኖታቸው ተከታይ የሆኑ ሁሉ እንዲያስተጋቡት ያገኙትን የግኑኝነት መንገድ ተጠቅመዋል፡፡መንግስት በጭፍን የወሰዳቸው እርምጃዎችም ጥያቄውን ያነሱትን ተማሪዎችን እንጂ ጥያቄውን ማግኘት ባለመቻሉ ጥያቄዎቹ በአጭር የጊዜ ሂደት የተማሪዎቹ መሆናቸው አብቅተው ነበር፡፡የሙስሊሙ ማህበረሰብ ተማሪዎቹ የእኔን ጥያቄ ነው ያስተጋቡት ለማለት በመድፈሩም ለሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ መፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ኮሚቴውን የፈጠረው የጥያቄው ሂደት እንጂ ኮሚቴው ጥያቄዎቹን ወይም እንቅስቃሴውን አለመፍጠሩን ያልተረዳው መንግስት በድጋሚ አይን ያወጣ አምባገነናዊ ስህተት ፈጸመ፡፡
የኮሚቴዎቹ መታሰር፣የአወሊያ አስተማሪዎች መባረርና ተማሪዎቹ ላይ የተፈጸመው አፈና ለግዜው የእንቅስቃሴው መነሻ የነበሩት ሊመለሱልን ይገባሉ የተባሉ ጥያቄዎች ተዘንግተው ‹‹ኮሚቴውን ፍቱልን›› የሚል ጥያቄ እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑ አልቀረም፡፡ህዝቡ እንዲወክሉት በተለያየ መንገድ ፊርማ በማሰባሰብ ውክልናውን የሰጣቸው መምህራኑ መልካም ስማቸው ጠፍቶ ወህኒ ሲወረወሩ የትግሉ ዋነኛ ትኩረት እነርሱን በማስፈታት ላይ ማድረጉ የሚጠበቅ ይመስለኛል፡፡
ኮሚቴዎቹ እጃቸው ከተያዘበት ቀን አንስቶ ህዝበ ሙስሊሙ በዋናነት ጥያቄውን ሲያቀርብ፣ተቃውሞውን ኢህአዴግን በማይመጥን ስልጡንና ፍጹም ሰላማዊ መንገድ ሲገልጽ፣እስረኞቹን ሲጠይቅ፣ቤተሰቦቻቸውን ሲንከባከብና ይህን በማድረጉም ሲገደል፣በአደባባይ ሲደበደብ፣ተባባሪ ተብሎ ሲታሰርና እንደ ሁለተኛ ዜጋ በአገሩ ሲቆጠር ቆይቷል፡፡
የኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ከመንግስት ተወካዩች ጋር ውክልናቸው ተቀባይነት አግኝተው ሲወያዩና የህዝቡን ጥያቄ መንግስት ጆሮ ሰጥቶ እንዲሰማ ሲታትሩ እንዳልቆዩ በማዕከላዊ ቅልቦች ሰብአዊ ክብራቸው ተዋርዶ፣የተሰባሰብነው እስላማዊ መንግስት ለመመስረትና ኢትዮጵያ በሸሪያ ህግ እንድትተዳደር ለማደረግ ነበር ብለው ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደረጉ፡፡ለመርማሪዎቹ ርካሽ እርምጃ አንገቱን ያላጠፈው የኮሚቴዎቹ ሰብሳቢ አቡበከር አህመድ ሁለት እጆቹ በካቴና እንደታሰሩ ለህዝብ እንዲታይ ተደረገ፡፡
አቡበከር በራሱ ላይ መሰከረ ተብሎ እንደ ትልቅ የምርመራ ግኝት እንዲቀርብ የተደረገው ዶክመንተሪ በአየር ላይ ከቆየ የሰዓታት ዕድሜ በኋላ መርማሪዎቹን እርቃናቸውን ያስቀረ ያልቶራረጠ ድንግል ዶክመንተሪ በእንግሊዘኛው የኢቴቪ ፕሮግራም ወቅት ሊቀርብ ችሏል፡፡
ከመነሻው ተከሳሾቹን ወንጀለኛ በማድረግ የሚጻፍለትን የመጋረጃ ጀርባ ውሳኔ ከማስተላለፍ የዘለለ ሚና እንደማይኖረው የሚታወቀው ‹‹ፍርድ ቤት››እየፈራ እየቸረ የኮሚውን አባላትና ስለኮሚቴው እንቅስቃሴ መረጃ ለህዝብ ያቀርብ በነበረ ጋዜጠኛ ላይ ከ22 – 7 ዓመት የሚደርስ የእስራት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
የኮሚቴውን እስራት ላለፉት ሶስት አመታት ሲቃወምና ጉዳያቸውን በቅርበት ሲከታተል የነበረ ህዝብ ከዛሬ ሰባትና ሀያ ሁለት አመታት በኋላ ዝዋይና ሸዋሮቢት እየሄደ እስራታቸውን ጨርሰው ሲወጡ ለመቀበል በማሰብ እስከዛው ወደ ጠርሙሱ የሚገባ አይመስለኝም፡፡ለህዝቡና እንቅስቃሴውን ይመራል ለሚባለው ‹‹ድምጻችን ይሰማ››ከፍርድ ውሳኔው በኋላ የሚኖረው አማራጭ ሁለት ብቻ ይመስለኛል፡፡እነ አቡበከር ለእስር የተዳረጉበትን ጥያቄ በድጋሚ ወደፊት በማምጣት ሌሎች አቡበከሮችን መፍጠር አልያም እነ አቡበከር ለሚፈቱበት መንገድ ትኩረት በመስጠት በመንግስት ላይ በአገር ውስጥና በውጪ ጫናዎች እንዲፈጠሩ መስራት፡፡
በእኔ እምነት እነ አቡበከርን ለእስር የዳረጉ ጥያቄዎች ላይ የሁሉም ትኩረት እንዲኖር በማድረግ ትግሉን በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ማድረግ ይህንን እንቅስቃሴ ከዳር ሆነው ሲከታተሉ የነበሩ የሙስሊም ሐይማኖት ተከታይ ኢትዮጵያዊያን፣በመንግስት ፣ሃላፊነት ውስጥ የሚሰሩ ፣የፍትህ ስርዓቱ አካል የሆኑና ኢህአዴግን ሲደግፉ ለቆዩ አቋማቸውን የሚፈትሹበትን ዕድል ሊፈጥርላቸው ይችላል፡፡
በጥያቄዎቹ ዙሪያ በመንግስት ፕሮፓጋንዳ ግራ የተጋቡ የሌሎች ሐይማኖቶች ተከታዩችም የትግሉ መነሻ ከመንግስት ፕሮፓጋንዳ ብዙ የራቀ መሆኑን እንዲገነዘቡ ሊያደርጋቸውም ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ድምጻችን ይሰማ እነዚህን ጥያቄዎች ወደፊት በመግፋትና በስርዓቱ ጭቆና እየደረሰበት የሚገኘውን ቀሪው ኢትዮጵያዊ በተከፈተ ልብ በመቅረብ የአንድዮሽ ትግሉ ሁሉን አቀፍ የሚሆንበትን ሁኔታ ሊፈጥርበትም ይችላል፡፡
እስረኞቹን ለማስለቀቅ የሚደረጉ ንቅናቄዎችም ምንም እንኳን እስረኞቹ አሁን ለሚገኙበት ሁኔታ የተዳረጉት በሐይማኖታቸው ዙሪያ ባቀረቧቸው ጥያቄዎች መንስኤ ቢሆንም የገቡባቸው ወህኒ ቤቶች ከሚያገኟቸው እስረኞች በመነሳት የአገሪቱ ችግር ላነሷቸው ጥያቄዎች ብቻ መልስ በማግኘት የሚመለሱ እንደማይሆኑ እንደሚገነዘቡ ሁሉ ድምጻችን ይሰማም ከእነ አቡበከር እኩል ነጻነታቸውን ሊቀዳጁ የሚገባቸውና በትክክለኛ ፍትህ እጦት የተነሳ ወህኒ የሚማቅቁ ለመኖራቸው እውቅና በመስጠት በአጠቃላይ ስለ ፍትህ፣ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት፣የሐይማኖት ነጻነትና ሰብአዊነት በኢትዮጵያ ነጻ እንዲወጡ ያለ ሐይማኖት ልዮነት ለሁሉም የትግል ጥሪ በማድረግ የመሪነት ሚናውን መጫወት ይችላል፡፡
ያልተሰማ ድምጽ
ኢህአዴግ ምላስ፣አድርጉ የተባሉትን ከመፈጸማቸው በፊት ለምን የማይሉ ታጣቂዎች፣ህሊናቸውን ለሆዳቸው አሳልፈው የሰጡ የይሁዳ የበኩር ልጆች በፍርድ ወንበር ያሉት መሆኑን በማረጋገጡ ላለፉት ሶስት አመታት የቀረበለትን የ‹‹ድምጻችን ይሰማ ››ጩህት ‹‹ጥቂቶች፣የአልቃይዳ ህዋሶችና ሽብርተኞች››የሚሉ ስያሜዎችን በመለጠፍ ‹‹አይሰሜነትን››ባህሪው ማድረጉን አሳይቷል፡፡የትናንቱ የፍርድ ውሳኔም በአራት ኪሎ ህዝብን የሚሰማና እስካሁን ለተደረገለት ማንኳኳት በሩን ለመክፈት የተዘጋጀ አመራር አለመኖሩን አረጋግጧል፡፡
ከፍርዱ ውሳኔ በኋላ አሁንም ‹‹ድምጻችን ይሰማ፣ፖሊስ የህዝብ ነው››የሚሉ ውትወታዎችን ከህዝቡ የሚጠብቁ የኢህአዴግ መሪዎች ተላላዎች ይመስሉኛል፡፡በርህን ለሰዓታት ሲያንኳኳ አልከፍትለት ያልከው ሰው የቀኑን ንጋት በርህ ላይ አይጠብቀውም፡፡ሌላ በር ሊያናኳኳ ወይም መስኮትህን ሰብሮ ሊገባ አማራጭ ይፈልጋል፡፡ህዝብም እንደዚህ ነው፡፡ምንአልባት ከእንቅልፍህ ትነቃና ‹‹በሬን ያንኳኳው ማን ነበር››እያልክ ልትፈልገው ተወጣለህ ያኔም የእሱን ቤት የማንኳኳት ተራው የአንተ ይሆናል፡፡
ድምጻችን ይሰማ የእንቅስቃሴውን መጠሪያ ብቻ በመቀየር እንዲመጣ ሳይሆን ሌሎች አስገዳጅነት ያላቸውን የትግል ስልቶች ነድፎም ይሁን ከሌሎች ተሞክሮ ተውሶ እንዲመጣ እጠብቃለሁ፡፡በፍርድ ቤቱ አሽከርነት የተላለፈው ንጹሐንን እንደወንጀለኛ የመቁጠር ውሳኔ ልቡን ያላደማው ፣ሐዘኑን ያልገለጸና ራሱን በእነርሱ ጫማ ያላስቀመጠ የሚኖር አይመስለኝም፡፡
ይህንን አይነት ዜና ላለፉት 25 ዓመታት በፍርድ ቤት እየሰማ ልጆቹን፣ወላጆቹን፣የትግል አጋሮቹንና የሐይማኖት መምህራኑን ያልተነጠቀ፣ መሬት ያልቀጠቀጠ፣ ብቻውን ያላጉለመለመ የለም፡፡አሁን የእነርሱ ተራ በመሆኑ ይቅመሱት በማለትም ቁስሉን ማከም አይችልም፡፡የእነዚህ ቁስል የሚታጠበው በተባበረ የትግል ስልት በአንድነት መቆም ሲችሉ ብቻ ነው፡፡እናም ድምጻችን ይሰማና የኢትዮጵያ የለውጥ ኃይሎች ከሚገኙባቸው ክበቦች በመውጣት ለማሰብ ከትናንቱ የተሻለ ግዜ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ፡፡እርግጥ ነው አንዷለም፣እስክንድር፣ከእነርሱ በፊትና በኋላም ብዙዎች ይህንን ጽዋ እንዲጨልጡ ሲደረጉ እንደሰው መጠየቅ ፣መቆምና ያገባናል ማለት ይገባን ነበር፡፡ያ አልፏል አሁን ደግሞ ሌላ ደወል በእነ አቡበከር በኩል ተደውሏል፡፡ለዚህ የምንሰጠው የተበታተነ ወይም የጋራ ምላሽ የኢትዮጵያን መጻኢ ሁኔታ ይወስናል፡፡

Dawit Solomon's photo.
Dawit Solomon's photo.