ብሪታንያ ወደ ግዛቷ የሚገቡ ህገ ወጥ ስደተኞችን ፍሰት ለማስቆም የሚያስችል አዲስ እርምጃ እወስዳለሁ አለች።
እርምጃው በህገ ወጥ መንገድ የገቡ ስደተኞችን የሚቀጥሩ ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ተነግሯል።
ህጋዊ ፈቃድ የሌላው የውጭ ሀገር ዜጎችን የሚቀጥሩ የመሬት ባለቤቶችን እስከ አምስት አመት በሚደረስ ፅኑ እስራት መቅጣት የአዲሱ እርምጃ አካል ነው።
የብሪታንያ ማህበረሰብ ጉዳዮች ሚኒስትር ግሬግ ክላርክ አዲሱ እርምጃ በቀጣዮቹ ወራት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደ ሚቀርብ ተናግረዋል።
እንደ አሶሽየትድ ፕረስ ዘገባ ባለፉት ሳምንታት ብቻ 1 ሺህ 700 ስደተኞች በብሪታንያ የዋሻ ውስጥ ባቡር መተላለፊያ ሾልከው ወደአገሪቱ ለመግባት ሞክረዋል።
…………………..
ጅቡቲ ከየመን የእርስ በርስ ጦርነት ሸሽተዉ ለመጡ ስደተኞች መርጃ ድጋፍ እንዲደረግላት ዛሬ ጠየቀች።
በአፍሪቃ ቀንድ የምትገኘዉ እና ከስምንት መቶ ሺህ በላይ የሚገመት ሕዝብ ያላት ሀገር በጦርነትና ግጭት የተመሰቃቀለች ሀገራቸዉን ለቀዉ ለተሰደዱት የመናዊያን ምድራዊ ገነት እንደሆነች ነዉ የተነገረዉ። የተመ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR ካለፈዉ መጋቢት ወር አንስቶ ጅቡቲ የገቡት የመናዉያን 10,000 ደርሰዋል።አብዛኞቹም የቆሰሉና የተጎዱ በመሆናቸዉም የሀገሪቱ ሃኪም ቤቶች እነሱን ለመርዳት ከአቅም በላይ እየጣሩ ነዉ። ባለፈዉ ሳምንትም በሁለት ጀልባ የተጫኑ ከሁለት መቶ የሚበልጡ የመናዉያን ወደሀገራቸዉ እንደገቡ የገለፁት የጅቡቲ ፕሬዝደንት ቃል አቀባይ ናጂብ አሊ ጣሂር የስደተኞቹ ጎርፍ ያባራል ብለዉ እንደማይገምቱ አመልክተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለም በተቃራኒዉ ኢትዮጵያዉያን እና የሌሎች ሃገራት ስደተኞች በጦርነት ወደምትታመሰዉ የመን ለመሰደድ በጅቡቲ መረማመድ መቀጠላቸዉን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ከስፍራዉ ዘግቧል። እንደዘገባዉ አብዛኞቹም በሕገወጥ ሰዉ አሸጋጋሪዎች የየመን ጦርነት አክትሟል በሚል የተጭበረበሩ ናቸዉ።
………………….
የየመን አማፅያን መሪ የፖለቲካ መረጋጋት ጥሪ
በኢራን እንደሚደገፍ የሚነገርለት የየመን ሁቲ አማፅያን መሪ በስደት ከሚገኘዉ መንግሥት ጋ መደራደር እንደሚቻል አመለከቱ። አብዱልማሊክ አል ሁቲ የተመድ ከሞከረዉ ድርድር ወዲህ ሌላ ሶስተኛ ወገን አረብም ይሁን ዓለም አቀፍ ሸምጋይ የየመንን ተቀናቃኝ ኃይሎች ለማግባባት ቢሞክር የፖለቲካ መረጋጋት ሊያመጣ ስለሚችል ተቀባይነት ይኖረዋል ብለዋል። ቀደም ሲል በሰኔ ወር የተመድ ጄኔቫ ላይ የየመንን ተፋላሚ ኃይላት ለማደራደር ሞክሯል። እንዲያም ሆኖ ሁለተኛዋን የየመን ትልቅ ከተማ ኤደንን በመንግስት ታማኝ ኃይሎች መነጠቃቸዉን «ጊዜያዊ» በማለት አጣጥለዉ፤ ከተማዋን መልሰዉ ለመያዝ እንደሚችሉ ገልጸዋል። የመንግስት ታማኝ ኃይሎች ዛሬም በታንኮችና መሣሪያ በተጠመደባቸዉ ተሽከርካሪዎች በመታገዝ በሰሜን ኤደን የሚገኘዉን አል አናድ የተሰኘ የአየር ኃይል የጦር ሠፈር መልሰዉ ለመያዝ የተጠናከረ ጥቃት መሰንዘራቸዉን የፈረንሳይ የዜና ወኪል ዘግቧል። ስፍራዉ ስልታዊ ጠቀሜታ ያለዉ ከሆኑ በተጨማሪ የሁቲ አማፅያን ባለፈዉ መጋቢት ወር እስኪቆጣጠሩት ድረስ የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች በየመኑ አልቃይዳ ላይ የአብራሪ አልባ አዉሮፕላን ጥቃት የሚሰነዝሩበት እንደነበር ተገልጿል። ዘግይተዉ የወጡት የሮይተርስ ዘገባዎች አል አናድ በመንግስት ታማኞች እጅ መግባቷን ያመለክታሉ።
አየለ ያሬጋል