በረከት ስምዖን ሞቶ አንዳርጋቸውን ሆኖ ተነሳ ( ሄኖክ የሺጥላ )
በረከት ስምዖን ሞቶ አንዳርጋቸውን ሆኖ ተነሳ ( ሄኖክ የሺጥላ )
አማሪካዊው ጠሐፊ ዊልያም ጀምስ ስለ ( pragmatism, radical empiricism, and pluralism) ብዙ የፍልስፍና አዲስ መሰረተ ሃሳቦችና እና የ ሃሳብ ፍሰቶችን ያመጣ ( ያመነጨ ) ፣ የጻፈ ፣ ያሳወቀ እና የሞገተ ፣ ግሩም የፍልስፍና ሊቅ ነው ። ይህ ሰው << We live forward, we understand backward >> በሚለው ሃሳቡ እና የሃሳብ ትርጉም ፣ ውስጠ ሚስጥራዊ ጥናት ይታወቃል ። ለነገሩ አብዛኛው ሰው ፣ የዚህንን አባባል ባለቤትነት ለዊልያም ጀምስ ቢሰጠውም ፣ ራሱ ጀምስ ይህንን አባባል ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማው ፣ እ ኤ አ በ 1904 ዳን ሀራልድ ሆፍዲንግ [ Dane Harald Høffding (1843-1941)] በጀምስ ተጋብዞ ፣ በጀምስ ፍልስፍናዊ አስተሳሰቦች ላይ ፣ በይበልጥም (pragmatism, radical empiricism, and pluralism) ላይ ፣ ለጀምስ ተማሪዎች ፣ በሃርፋርድ ዩኒቨርስቲ ተገኝቶ ፣ ማብራሪያ በሰጠበት ወቅት ፣ ከ ዴንሹ የፍልስፋና ሊቅ Kierkegaard ( ኪኢርክጋርድ ) እንደ ጥቅስ ወስዶ የተናገረው ነበር ። እኔም ዛሬ በዚህ ጥልቅ እና ትልቅ አባባል ዙሪያ ፣ ስለ ማህበረሰባዊ የአስተሳሰብ ክሸፍቶች ፣ ስለ ማንነት ብክነቶች ፣ ህዝቦች የሚመሩበት ንዑስ ስርዓት ሲዝግ ፣ ህገ-መንግስት በራሱ በመንግስት-ሲናድ ፣ እና ያ የምንግስት አካል ፣ በማናለብኝነት እና ምን አገባኝ ጉልበት ታጅሎ ፣ ሕዝብ አስገድዶ ለመምራት ሲያስብ ፣ ማህበረሰቡ በእውነት እና እውነት ባልሆነ ነገር መሃከል ያለውን ልዩነት ፍጹም መለየት እስከማይችልበት ደረጃ እንደሚደርስ ፣ ይህም በውሸት ላይ የተመሰረተ የለት-ተለት ኑሮ ፣ በሀገር ህልውና ላይ ስላለው ተግዳሮቶች እና የተግዳሮቶቹ መስተጋብር የሚያትት ይሆናል ። በመጨረሻም አንዳንድ የምሳሌ ዘውጎችን አነሳለሁ ።
በመጀመሪያ ጀምስ << We live forward, we understand backward >> የሚለውን አባባል ደጋግሞ የተጠቀመው በ << radical empiricism>> ትንተናው ላይ ሲሆን ፣ ይህም በ 1905 ባሳተመው መጽሐፉ ውስጥ ይመስለኛል ፣ በዚህም አተኩሮ የሚዘግበው << the relationship between reflection on a prior experience and the experience itself>> << በቀደመ ልምድ ( ገጠመኝ ) ነጸብራቃዊ ትዝታ እና በትዝታው ምንነት መሃከል >> ስላለው ዝምድና የሚያትት ሲሆን ፣ የሰው ልጅ በቀደመው ታሪኩ ያሳለፈው ማንነቱ ፣ ወደፊት ሊሄድ ሲል እየመዘዘ የሚያወጣው የማንነት መለኪያ መስፈርቱ እንደሚሆን ይናገራል ። ይህም ማለት ፣ ሰውየው ገበሬ ከነበረ እና ፣ በቀጣይ ህይወቱ ነጋዴ ቢሆን ፣ የነጋዴነቱ ስኬት ወይም ውድቀት የሚለካው ፣ ገበሬ በነበረ ጊዜ በነበረው ጥንካሬ ወይም ስንፍና ነው ወይም ይሆናል ፣ እንደማለት ነው ። ይህም <<We live forward, we understand backward>> የሚለውን አባባል በደንብ እንደሚዘክረው ያብራራል ። ከዚህ አገላለጽ ተነስተን ደሞ ፣ ስለተለያዩ ጉዳዮች ሰፋ ያለ ማብራሪያ መስጠት እንችላለን ማለት ነው ። ለምሳሌ ህውሃት ( ወያኔ ) ፣ ወደፊት እየኖረ ወደ-ሗላው ብቻ የሚረዳ ስርዓት ለመሆኑ ከበቂ በላይ መረጃ አለን ። ለምሳሌ ፣ ዛሬም ደርግን ስለመጣሉ ያወራልሃል ፣ ዛሬም እኔ ጀግና ነኝ ፣ አንተ ግን አይደለህም ይልሃል ፣ ዛሬም ነገሮችን ሁሉ በጉልበት ለመወሰን ብቻ እንደሚችል የነገሮች ሁሉ አዛዥ እና ነዛዥ እሱ ብቻ እንደሆነ ይነግርሃል ፣ ዛሬም ተራራው ፣ ደኑ ፣ ሳሩ ፣ ቅጠሉ ለሱ እንደሚንቀጠቀጡ ፣ ለሱ እንደሚረግዱ ፣ እሱ ብቻ በደሙ የታደጋቸው ተራርሮች፣ ያለሱ ቢዘሩ እንደማያበቅሉ ፣ ቢታረሱ እንደማያፈሩ ፣ ቢጎለጎሉ እንደማይለሙ ይነግርሃል ። ከምንም በላይ ፣ ታሪካዊ ውሸታምነቱን አጠናክሮ መቀጠሉ ፣ የሃውዜን ማንነቱን ትናንት በነ- አኬል-ዳማ ሲደግመው ፣ ዛሬ ደሞ- <<በአንዳርጋቸው መጽሐፍ ጻፈ>> የቅጥፈት ዜና አጠናክሮት ሊያደልበው እንደተዘጋጀ ስንረዳ ፣ ጀምስ እንዳለው << We live forward, we understand backward>> የሚለውን አባባል ያለ አንዳች ግድፈት እየፈጸመ ያለ ስርዓት ስለመሆኑ እንረዳለን ።
እውነቶችን ወይም ኩነቶችን ከራሳችን ልምድ ብቻ ተነስተን ለማርቀቅ ስንተጋ ፣ የዛሬ ማንነታችን ሙሉ በሙሉ <<የኛ ታሪክ ብቻ>> ባልነው ሲገደብ ፣ ከኛ ወዲያም ወይም ከኛ ወዲህ ያሉትን እውነቶች ስንጥል ፣ ስለ-ራሳችንም የምናወራው ወይም እኛ ነን ብለን የምንናገረው ፣ የገሃዱ ዓለም እኛ ምን እንደሆንን በአደባባይ የሚመሰክረውን ግድፈታችንን ሳይሆንን ፣ ቀባብተን ያቀረብነውን ሰባራ ሸክላ መሳይ ስብእናችንን ሲሆን ፣ የጥንካሪያችን መለኪያ ፣ የለውጣችን ማሳያ አስረጅ ሲነጥፈው ፣ ያለፈ የጦርነት ታሪካችንን ከፊት እያስቀደምን << ብትቀበል ተቀበል ፣ አለበለዚያ እኛ ደርግን የጣልን ጀግኖች ነን >> ፣ በሚል ማስፈራሪያ ለመኖር ስንተጋ ፣ እኛ እውነትም ወደፊት እየኖርን ፣ ወደ- ሗላ የምንረዳ ስለመሆናችን ምንም ነጋሪ እና ነዛዥ አያስፈልገውም ።
ኃያሉ ጎልያድን የገነደሰው ዳዊት ፣ በሐጸ- ዝሙት ተነድፎ ፣ ኃጢያት ነግሶበት ፣ የኦርዮንን ሚስት ሲቀማ ፣ ኦርዮንንም በደቂቀ አሞናውያን ሰይፍ ሲያስመታ ፣ የድሀውን ጠቦት ሲቀማ ፣ እሱንም ደግሞ ሲያስገድለው ፣ ዳዊትም ወደፊት እየኖረ ፣ ወደ- ሗላ ይረዳ ስለነበረ ነው ። ዛሬም አንዳርጋቸው በቅያፋ ፊት ሲቆም ፣ ሕግ በበደነበት ፣ እውነት በተረሳበት ፣ ታሪክ በተጨማለቀበት ፣ ይሉኝታ በፈገመበት ፣ ወደ- ፊት እየኖረ ወደ ሗላው በሚረዳ ስርዓት ፣ ሕግና ደንብ ውስጥ ፍትህ እና ፍርድ እንዲያገኝ ሲደረግ ፣ ከልብ ወለድ ፈጠራ ፣ ከሐሰት ክስ ፣ ከተምታታ መረጃ ፍርጃ ነጻ ይሆናል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው ። በይበልጥም ሐሰት ከተንዠረገገብት ፣ ቅጥፈት ኩልል ብሎ ከሚፈስበት ፣ ክህደት እንደ ሰብል በማዳበሪያ ከሚያድግበት ፣ ልቃሚነት ከሚወደስበት ፣ ተራነት ከሚወደስበት ፣ ልቅነት ከነገሰበት፣ ከህውሃት መንደር እንዲህ ያለው ዜና ሲሰማ ፣ ሰሚውንም ተሰሚውን ግራ የሚያጋባ አዲስ ነገር ይሆናል ብለን አናስብም ። የሁሉም ቅጥፈቶች በሽታ ወደፊት እየኖሩ ወደ ሗላ ከመረዳት የመነጨ ነውና ።
አልክሳንደር ዱማስ ( The Three Musketers ) በሚለው መጥሀፉ ላይ ፣ በሶስተኛው ክፍል ፣ ስለ አንድ እስረኛ ያወራል ። በምጽሐፉ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ ( The Prisoner ) በሚለው ክፍል ስር ፣ ፊቱን በብረት ከተሸፈነው እስረኛ ጋ ፣ አራሚስ የተባለው ገጸ ባህርይ ፣ ከ እስረኛው ጋ የሚያደርገውን ቃለ ምልልስ በጣም በጥቂቱ ይህንን ይመስላል
አራሚስ “Well, then, you ought, as a penitent, to tell me the truth.”
እስረኛው “My whole desire is to tell it you.”
አራሚስ “Every prisoner has committed some crime for which he has been imprisoned. What crime, then, have you committed?”
እስረኛው”You asked me the same question the first time you saw me,” returned the prisoner.
አራሚስ “And then, as now you evaded giving me an answer.”
እስረኛው”And what reason have you for thinking that I shall now reply to you?”
አራሚስ”Because this time I am your confessor.”
እስረኛው”Then if you wish me to tell what crime I have committed, explain to me in what a crime consists. For as my conscience does not accuse me, I aver that I am not a criminal.”
በነገራችን ላይ ዱማስ ይህህንን ታሪክ የጻፈው ከእውነተኛ ታሪክ ላይ ተነስቶ ነው ፣ የዱማስ የዚህን ታሪክ መጻፍ ተከትሎ ፣ ታታላላቅ ጸሐፍት ( እንደ ቮልቴር ያሉ ይህ የብረት ጭንብል ፊቱ ላይ አርጎ ( ተሸፍኖ ) ታስሮ ስለነበረው ሰው ሌሎች ታሪኮችን ጽፈዋል ። በአብዛኛው፣ የፈረንሳዩ ንጉስ የሊውስ 16ኛ ልጅ ነው ተብሎም እንደታመነ ካነበብኩት መረዳት ችያለሁ ።
ወደ ተነሳሁበት የእስረኛ እና የአናዛዥ የሃሳብ ምልልስ ስንገባ ፣ እጅግ አበክሬ፣ (በአሕጽኖት እንደሚሉት ማለት ነው ) መመልከት የምፈልገው አራሚስ ፣ << እኔ አናዛዥህ ነኝ ፣ እኔ ንስሐ አስገቢህ ነኝ >> <<“Because this time I am your confessor.”>> የሚለው ላይ ነው ። አንዳርጋቸው ጽጌ ታፍኖ ከተወሰደበት ጊዜ ጀምሮ ፣ በያንዳንዷ ደቂቃ ፣ አናዛዦቹ << በል ንገረን ፣ ይህንን አውጣ ፣ ይህንን በል ፣ ይህ አልሆነም ወይ?!>> እያሉ ሲያሰቃዩት እንደከረሙ መገመት ሳይሆን እንዳደረጉት እናውቃለን ። አንተ ወንጀለኛ ነህ ሲሉት ፣ <<በመጀመሪያ ግን ወንጀል ምንድን ነው ?>> ሲላቸው ፣ << የምጠይቅህን መልስልኝ ?!>> ሲባል ፣ << የጠየከኝን እንድመልስልህ ዛሬ ምን የተሻለ ምክንያት ኖረህ >>ሲል ፣ ዛሬ የአንዳርጋቸው ሕይወት ፣ እንደ ሞንቴ ክርስቶው እንደራሲ ፣ እንደ ቄስ ፋሪያ ፣ እንደ ቄስ ቡሶኒ ፣ የልብ-ወለድ ምልዓት ተላብሶ ፣ በህውሃት ደሴቶች ላይ የተቀበረ የምኞት እንቆዎችን ፣ የሐሰት ክብሮችን ፣ የጭብርብር እድገቶችን፣ ጽፎ እንዲያመሰግን ፣ ሀሌ-ህውሃት እንዲል ፣ ዳጎስ ባለ
መጥሃፋው የተረቺነት እና የተሸናፊነት ስነ ልቦና በሕዝቡ ልብ ውስጥ ለማስረጽ ፣ ስሙን ለማጥቆር የሚደረገው ነገር ሁሉ ፣ ህውሃት ዛሬም ወደፊት እያየ ወደ -ሗላው የሚረዳ ጨቋኝ አካል ከመሆን የዘለለ አንድም የሚያመጣው ወይም የሚነቀንቀው ስብእና እንደሌለን ይረዳ ዘንድ ፣ አራሚስ የሚጠይቀው እስረኛው መልስ ፣ የኛ አንዳርጋቸው ቃል እንደሆነም ለምናውቀው እኛ ፣ የአንዳርጋቸው መጽሐፍ ጻፈ ቅጥፈት ለ- ህውሀቶች ሌላ አኬልዳማዊ ድግስ ከመሆን አልፎ ፣ ሌላ ጅሃዳዊ ሐረካት ከመሆን አልፎ ፣ የተለየ ጭብጨባ እና መረዳት ያተርፍላቸዋል ብለን አናምንም ፣ አንጠብቅም ።
ዛሬ በረከት ስምዖን የሞተው ወይም የታመመው ፣ በአንዳርጋቸው ስም መጽሐፍ ሆኖ ሊነሳ ፣ የደደቢት ደሴቶች ግሁሣን ፣ የሞንቴክርሥቶ እንደራሲ ደራሲ ሆኖ ብቅ ልል ታስቦ እንደሆነም ሰምተናል ። በይበልጥም ፣ ለአድ ዓመት ከዘለቀው የአንዳርጋቸው ስቃይ ( ቶርቸር ) ውስጥ ምንም ያላገኙት ህውሀቶች ፣ ከሱ ጋ በርሃ ሳሉ ፣ ስለሱ በቅርብ ያውቁ ከነበሩ ሰዎች ( አንዱን እኔም በቅርብ አውቀዋለሁ ፣ በደቡብ አፍሪካ ይኖር የነበረ ልጅ አሁን ወያኔ ቪላ ቤት ሰጥቶ ፣ አቀማጥሎ የያዛቸው ሆድ አደሮችን ታሪክ በማሰናሰን ) ፣ ታሪኩ እውነት እንዲመስል ፣ በይበልጥም አንዳርጋቸው ሲያዝ ከ ላፕ-ቶፑ ውስጥ ያገኙትን መረጃዎች እንደ አንድ ትልቅ የመጽሐፉ ግብአት በመጠቀም ፣ ሕዝቡን ለማሳመን ፣ ሃያልነታቸውን ለማስያት ፣ የግንቦት ሰባት ደጋፊና አባሎችን ስም ዝርዝር በመጽሐፉ ውስጥ በማስቀመጥ ፣ ሰዎችን ይበልጥ ለማስፈራራት ፣ ከተቻለም ይቅርታ እንዲጠይቁ ለማግባባት የተጻፈ መጽሐፍ ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለንም ።
ያም ሆኖ ፣ አሁንም ወያኔ ከመውደቅ አይድንም ። በወሬ የማንፈታ ፣ ስለምንም አይናችን የማይጨፈን ቆራጦች መሆናችንን ያውቁት ዘንድ ፣ ትግሉን በመቀላቀል ፣ እና በሙሉ ልብ በመደገፍ እንብታችንን እናሳያለን ። ደሞም እናሸንፋቸዋለን ። ምክንያቱም እኛ እነሱን ለማሸነፍ የተፈጠርን ልጆች ስለሆንን ። ወደፊት እየኖረ ወደ -ሗላ እያሰበ የሚኖር ስርዓት መጨረሻው ሽንፈት እና ውርደት ስለሆነ !
ውሻ ጮኸ ተብሎ ድንጋይ አይወረወርም
July 22, 2015
ቹቸቤ ነኝ አማን ነው? የሰሞኑን ነገር ለመግለጥ የሚሆን መንደርደርያ ፍለጋ ስባጅ ቆየሁ። ዛሬ ሁሉም ተናጋሪ ቢሆንም የነገር ድግግሞሽ አታክቶናል። ገና የተተነፈሰው እንደሰሚው ተወላግዶ ወይም ጣፍጦ የበሬ ግንባር በምታክለው ፌስ ቡክ ይለጠፋል። ወሬ ብርቅ አይደለም። እንዲያውም በርካታ ተግባር አልባ የወሬ ቤቶች ተከፍተው ወሬ ሲወቁ ነገር ሲሰልቁ ቡና ቤት መለወጥ እንደሚወድ ጠጪ ከአንዱ ፓልቶክ ወደ ሌላው እየዞሩ በጉንጭ አልፋ ፍሬከርስኪ የሚያደነቁሩን አውርቶ አደሮች በዝተውብናል። ከሁሉ የሚያሳዝነው ደግሞ ከፈር ቀዳጅ ታጋዮቹ መንደር ነበርንና አንቱ በሉን የሚሉ እድሜ ጠገቦቹ ከተማሪ ረብሻ ወዲህ አርባ አመት ያስቆጥሩም ቢሆን ዛሬም እንኳ የአስተሳሰብ ጨቅላነታቸውን አለመጨረሳቸውና አሁንም በረብሻ መተዳደርን የመረጡ በሚያስመስል አፍራሽ ተግባር ተጠምደው ማየታችን ነው።
በእድሜ ዘመናቸው አንድም ሚዛን የሚደፋ ቁምነገር ሰርተው አያውቁም። በተለይ ደግሞ ወያኔ ወደስልጣን ከመጣ በሁዋላ ከኛ በላይ የወያኔ ተቃዋሚ ለአሳር እያሉ ሽንጣቸውን ገትረው የሚውረገረጉም ቢሆን የዚህን አረመኔ ወያኔ እድሜ የሚያረዝም እንጂ የሚያሳጥር ምንም ሰርተው አያውቁም። እንዲያውም ከእድር ለየት ባለ የፖለቲካ ቡድንነት የተሰባሰቡ መሆናችው ትዝ የሚላችውና ነገር ጣል ለማደረግ የሚባንኑት ሌላው ወገን የሰራው ነገር መኖሩን ሲሰሙ ነው። ያኔ አይናቸው ደም ይለብሳል እንደ ወያኔ ተለጣፊ ወይም ተመሳሳይ ነገር ሰርተው የተሰራውን ለማፍረስ ይጣደፋሉ። ገና አልባነነ ይሆናል እንጂ ጋዜጠኛውም ከፍርስራሾቹ አንዱን እየሆነ ነው። እንዲያውም ቆመጥ አድርገውት የራሱን ኢሳትን ይደበድቡበታል። እርሱም ዝናዬን ቀሙኝ ኩርፊያ የያዘ ይመስል አጓጉል መሄዱን መርጧል። ብቻ አጎቶቻችን ለማፍረስ ሲሆን እንደ ተኩላ ናቸው በጩኸት ይጠራራሉ ሳይነጋገሩ ይግባባሉ። ድርጅት በአይነት በአይነት ያቋቁሙና የመጥለፍ ጥማታቸውን ለጊዜውም ቢሆን ያረካሉ። የጀመሩትን ከምን እንዳደረሱት የሚጠይቅ ስለሌለ አዲስ ባቆሙት ላይ ያወራሉ። ትግል የሚለውን ቃል በግርድፉ እንዲያው ቃል በቃል ወስደው ነው መሰል አድማ እየመቱ ከሁሉም ሲታገሉና ሲያፈርሱ እድሜ ራሱ አፈራርሶ ሊጨርሳቸው ነው።
በመጨረሻ አንደርዳሪ ብልጥ ሃሳብ አገኘሁ እነሆ የብልህ ሰዎች ማህደር ከዊንስተን ቸርችል አባባል ላይ ወስዶ የለጠፈው ቃል ማረከኝ። “ውሻ በጮኸብህ ቁጥር ድንጋይ እያነሳህ የምትወረውር ከሆነ ካሰብክበት አትደርስም” የሚል ነው። አዎ ሩቅ ለመሄድ አልመው ድንጋይ ወርዋሪና ማዶ ለማዶ ቆሞ ተሳዳቢነትን የመረጡ ያሰቡበት አይደርሱም። ሰሞኑን የሚነፍሰው ንፋስ ግምኛ ነው ይሰነፍጣል። በርግጥ እነዚህ ሰዎች ነጻነትን ይፈልጋሉ ወይንስ እኛ ካላረግነው ሁሉም አፈር ይብላው የሚሉ ናቸው? እውን እነዚህ ሰዎች ለአፍራሽ ተልዕኮ የሚሰጣቸው ፍርፋሪ ኖሮ ነው ወይንስ ኑሮአቸው ይኸው ግርግር የመፍጠር ሆኖ ነው? ያስብላል። በተለይ የተማሩትና የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል እያሉ የሚጽፉት ምሁራኖች እነሱ ባሉብት መድረክ ላይ በጠንካራ ታጋዮችና መሪ ድርጅቶች ላይ ተራ ስድብ ሲደረደርና ትግሉን የሚጎዳ ግርድፍ ሀሳብ ሲዥጎዶጎድ በዝምታ ማለፋቸው ምን ይባላል? እኔን አንቱ እስካላችሁኝ ድረስ ሌላውን ድባቅ ብታስገቡትና ትግሉን ብትጎዱት እኔ ምን ገዶኝ ብለዋል ማለት ነው? ይሄ ከሆነ ስሌቱ ፍላጎታቸው መድረክ ላይ መኮፈስ እንጂ ሀገርን ማዳን አይደለም ብለን እኛም ለእንደዚህ አይነቶቹ የሚቸረውን አክብሮት እንሰጣቸዋለን።
በተግባራዊ ትግል የተጠመደው ወገን ደግሞ እነ ሰው ከንቱን ቁም ነገር አድርጎ አቧራ ማጨሱን ተወት አድርጎ ጊዜውን ተግባራዊው ትግል በሚፈልገው እንቅስቃሴ ላይ ቢያተርኩር ይሻላል። የእነኚህ አፍራሽ ወሬኞች ፋይል መዘጋት አለበት። እነርሱን ሰምቶ ከመንጫጫት ከግንቦት ሰባት አመራር ተምረን ለወሬኞች የምናባክነው ሰአት የለንም ብለን ወደተግባሩ እንመለስ። የግንቦት ሰባት አመራሮች ለርካሽና ተልካሻ ነገር መልስ ለመስጠት ደፋ ቀና ሲሉ አናያቸውም። ስራው ላይ በማተኮራቸው የእምነት ጽናትም በማሳየታቸው መሬት ላይ የሚታይ ስራ እየሰሩ ነው። ‘በርገር’ እየበሉ ግፋ በለው ብቻ እንደማይሉ ደግሞ በተግባርም እያሳዩ ነው። የሚበልጠው ለእናት ሀገር ለመዋደቅ የቆረጡ ወጣቶችንና አርበኞችን መደገፍና ትግሉን ማፋፋም ወይንስ የአሽሙር ጧፍ እያበሩ የእርግማን አዝማች ያለው የስድብ መዝሙር መዘመር?
ምርጫችንን ልናውቅ ልንበስልና ልንበቃ የሚገባን ጊዜ ላይ ነንና ከአመት አመት ራሳችንን እዚያው የነበርንበት ላይ ማግኘት ደካማ አቅማችንን ፀሀይ ማስሞቅ ይሆናል። ለዚህ ነው እነ ስም አይጠሬን ከቁም ነገር መድረክ ላይ ቆልለን በጮሁ መጠን ቃላት የምንወራወር ከሆነ መቼም ቢሆን ካሰብንበት አንደርስም ለማለት የወደድኩት። እንዲያውም ተጋብቶብን ቀንደኛ ተሳዳቢና አለክላኪ ተጓዥ ሆነን እርስበርስ የመነካከስ ባህርያትንም እየወረስን ነውና እነሱን ከመሆን ያድነን እንበልና ወደፊት እንገስግስ። ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር የሚል መፈክር ትዝ የሚለው ማነው? አዎ ያኔ ያለቀ ቢሆን ዛሬን ባልዘመትን ነበር።
ድል የማይቀር እውነት ነውና ዱር ቤቴ ላሉት ደጀን መሆን ምርጫችን ይሁን!
የአፍራሾች ዋይ ዋይታ (ደነባ ጉልላት)
July 25, 2015
ደነባ ጉልላት
ስንሰማ የነበረው ወያኔን በትጥቅ ትግል የሚፋለም ጠፋ ነበር ። ስንሰማ የነበረው የሕዝባዊ ሀይሉ መሪ ዶክተር ብርሃኑ በግንባር አልተገኙም የሚለውን ነበር ። ሁለቱም ቅሬታ ሲወገድ ግን ዋይ ዋይታና ኡ ኡታ የሚያሰሙ ከየስርቻው ብቅ አሉ ።
ከማንም በፊት ወደ ሻዕቢያ ሂዶ የነበረው ኤልያስ ክፍሌ የዚሁ ፊታውራሪ ሆኖ ብቅ አለ ። ወዳጅ ሲለው የነብረውን ሻዕቢያን ጠላት ብሎ ሰይሞ ተጀመረ የተባለውን የትጥቅ ፍልሚያ ሀሰት ሲል ኮነነ ። ሕዝባዊ ሀይሉን ቁጥር ከ ፲ ወደ መቶ ቢያደርሰውም የትም አልተንቀሳቀስም ብሎ አስተባበለ ።ይኽው ግለሰብ ግን የዴምህት ሀይል በኤርትራ ፵ ሺ ደርሷል ይለናል ። ለዚህ ያህል የማይንቀሳቀስ ጦር ምን ያህል ወጪ ይጠይቃልን አላሰበበትም ።ኢሳያስም የሌላ ህገር ዜጎች ያሉበት ይህን ያህል ጦር ማስተናገድስ ለደህንነቱ ይበጀዋል? ምን ገዶት ለኤልያስ!የኢትዮጵያ ረቪው የኢንተሊጀንስ ክፍል ባገኘው መረጃ መሰረት እያለ ውሸት መጠረቅ ልምዱ ነው ። ኤርትራና ሻዕቢያ ጠላት ከሆኑን ኢሳያስን የዓመቱ የኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ያለ ኤልያስ ሊወገዝ የሚገባው ይሆናል ። ኾለኔል ፍጹም ያን ሁሉ ወጣት ከረሸነ ለምን ይህንን ለማጋለጥ ዓመታት ፈጀበት ብንል መልሱ ራሱ ጠቋሚ ነው ።ኤልያስ ክፍሌ ለመሆኑ አለሁ አለሁ ማለት ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ የማንን አጀንዳ ነው በስራ ላይ እያዋለ ያለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ ዋናው ተል እኮእ ግን አርበኛ ሀይሉን/ታጋዮችን መበጥበጠ መሆኑን ታሪኩ ይመስክራል ።
ሌላው ዋይ ዋይታ አሰሚ አቶ መልኬ ሲሆኑ ወደ ኤርትራ የዘለቁት በዚያ ዋሾና ተራ ሌባ አብርሃም ያዬህ ተወስደው ነውና ያጋጠማቸው መጥፎ ተመክሮ ካለ ቅሬታቸው ቢገባንም ስለ አርበኞች ግንባር ያላቸው ዕውቀት ግን ጊዜ ያለፈበት መሆኑ የሚታይ ነው ። ደምስ የሚባለው በበኩሉ የመኢሶን ገራፊነት ታሪኩን እያነሱ ቀልቡን የሚገፉት እንዳሉ ሲታወቅ እሱም ቢሆን አርበኞች ግንባርን ደጋፊ መስሎ በተደጋጋሚ ወደ ኤርትራ የዘለቀ ነው ።ለምን መሄድ እንዳቆመ ኮለኔል ፍጹምን መጠይቅ አንገደድም —እናውቀዋለን ምክንያቱንና ነው ። እስካዛሬ ድምጹን አጥፍቶ ተደብቆ ከርሞ አሁን በግንቦት ፯ና አርበኞች ግንባር ላይ ምን አስነሳው ? በሻዕቢያም ሆነ በአርበኞች ግንባር መሪዎች ግፍ ተፈጸመ ካለስ ለምን እስካሁን ዝምታን መረጠ ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ ግልጽ ያደርጋል የእሱን አፍራሽ ተልእኮ ።
ከድረ ገጾች ደግሞ ያ የለመደበትን ኢትዮፓትርዮት የተባለውን የትምክሀት ገጽ ወደ ጎን ስንተው የኢትዮሚዲያው አብርሃም በላይና የዘሃበሻም አዘጋጅ ና ጋዜጠኛ በሉን ባዩን አበበ በለውን አጅበው በጸረ ሻዕቢያ ሰበብ ሕዝባዊ ሀይሉ ላይ ተነስተዋል ። ወያኔን የሚያስደስት ጸረ ሕዝባዊ ሀይልና ጸረ ዶክተር ብርሃኑ ዘመቻ በግልጽም በረቀቀ መንገድም እያካሄዱ መሆናቸውን ሀገር ወዳዶች ያጋለጡት ጉዳይ ነው ።ከኢትዮፓትርዮት እየለቀሙ ጸረ ሕዝባዊ ሀይል ጽሁፎችን የሚለጥፉት አሲምባ አዘጋጆች ደግም ጸረ ግንቦት 7 አቅዋማቸውን ማሰማት ከጀመሩ ውሎ አድሯል ። የፓል ቶኩ እንደራሴ (ተስፉ ፡ስድስት“) አዲስ አቅዋም አልያዘም—ጸረ ግንቦትነቱ የታወቀ ነውን ። የዚህ አፍራሽ ስብስብ ማዕክል ግልጽ ሆኖ ባይመጣም ወይም አንድ ሆኖ ላይገኝ ቢችልም ስራቸው ግን የተጀመረውን ትግል በርታ በርቱ በማለት ፈንታ ማፋለስ ሆኖ ይገኛል ።ከዚህስ ማን ይጠቀማል ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል ። ተጠቃሚው ወያኔ መሆኑ ግልጽ ነው ። መፍረክረክ ሲጀምር አይዞህ ባዮች ስለሆኑለት ባይወዳቸውም ሊያመስግናቸው ይችላል ። አንዳንዶቹም በቀጥታ ከእሱ ጋር ንክኪ የላቸውም ማለት አንችልም ። እነ አበብ በለው ወያኔ ወያኔ መሽተት ከጀመሩ ዓመታት አልፈዋል ።
ትጥቅ ትግሉ ተጀምሯል ። ያለውን አደጋ አይተው ሸብረክ ሳይሉ መሪዎቹ ወደ አስመራ አቅንተዋል ። ትግሉን በቦታው ሆነን እንመራለንም ብለዋል ። አንመለስም እስከ ድል ድረስ ብለዋል የሚለውን ግን ካፋቸው ስላልሰማሁ ማረጋጋጥ አልችልም ። ብለዋል ባዮቹ አንዳንዶቹ ምን ሞቲቭ እንዳላቸውም የሚሳት አይደለም ። ሕዝባዊ ሀይል የጀመረውን ትግል በርታ ግፋበት ሊባል ይገባዋል ። ዶክተር ብርሃኑ ውድቀታችንን ትሰማላችሁ፤ ስንነሳም ትሰማላችሁ እንዳሉት ሁሉ በዚህ መንፈስ የትግሉን ሂደት መጠበቅ መልካም ይሆናል ። ድጋፍ እየሰጠናቸው መሆኑ አስፈላጊ ነው ። ከዚህ ቀደም በጄኔራል ሃይሌ መለስ፤ በኢአግ፤ወዘተ የተደረጉ የትጥቅ ትግል ሙከራዎችን በበቂ ባንደግፋቸውም ውድቀታቸውን አልተመኘንም ። የረዱም ጥቂቶች አልነበሩም ። የሕዝባዊ ጥሪ እንደሚወገዘው በነዚህ አፍራሾች ያልተደረገ ከሆነ በአጭር ጊዜ መታወቁ አይቀርም ።እየተካሄደ ካለም (እኔ ነው ብዬ አምናለሁ) ደግሞ አፍራሾቹ ያፍራሉ ። እነ ኤልያስ፤አብርሃም፤ዘ ሀበሻ፤አበበ በለውና መሰሎቻቸው ላይም ማዕቀብ ያስፈልጋል ።
አፍራሾች ይፈርሳሉ !!
ድል ለሕዝብ !!
ጋዜጠኛ ኤልያስ ክፍሌ በኢትዮጵያ ከረንት አፊርስ ተቋም በግንቦት 22 ቀን 2009 በሰጠው ቃለ ምልልስ „ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከዳኛ ብረቱካን ይብልጣሉ! ብርቱካን ምን አላት¡ ቦንብ የላትም፤ ፕሬዚዳንቱ ግን ቦንብ አላቸው“