የማለዳ ወግ…የቢላዲን ቤተሰቦች በለንደኑ የአውሮፕላን አደጋ ! ነቢዩ ሲራክ
* በለንደን የሳውዲ ኢንባሲም አደጋ መድረሱን አረጋግጧል
* የሞቱት ቁጥር ከአብራሪው ጋር 4 ናቸው ተብሏል
ከሀገረ ጣልያን ተነስተው ለንደን አየር ክልል በሰላም የደረሰው የሸህ ኦሳማ ቢላዲን ቤተሰቦችን የያዘችው የግል ጀት አውሮፕላን ከማረፊያው እንደተቃረበ ባጋጠመው ያልታወቀ አደጋ ተከስክሶ ከተሳፋሪዎች መካከል አራት ያህሉ መሞታቸው የአለም ታዋቂ የመገናኛ ብዙሃን የዜና አውታሮች በመዘገብ ላይ ናቸው ። በለንደን የሳውዲ ኢንባሲም የሟቾችም ማንነት ባይገልጽም በቢላዲን ቤተሰብ አባላት ላይ አደጋው መድረሱን አረጋግጧል ።

በሳውዲና በባህረ ሰላጤ አቪየሽን የተመዘገበው ይህ የቢላዲን ቤተሰቦች የግል አውሮፕላን ከትናንት በስቲያ አርብ በሰሜን ለንደን በአንድ መንደር ውስጥ በሚገኝ የመኪና መሸጫ እንደወደቀ በእሳት መጋየቱም በዘገባው ተጠቁሟል። የሳውዲ ኢንባሲ በአውሮፕላኑ ስለነበሩት የቤተሰብ አባላት ማንነትና ስለ አደጋው የሰጠው ፍንጭ ባይኖርም ከቤተሰቦቹ አገኘሁ በሚል መረጃ ያሰራጨውን ታዋቂ የዜና አውታርን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስን የጠቀሰው አረብ ኒው ጋዜጣ በአደጋው የቢላዲን እናት እህቱ ሳና የእህቱ ባል ዙሄር ሀሽም አና ዮርድያኖሳዊው አብራሪ መሞታቸውን ዘግቦታል ። ያም ሆኖ የሀገር ውስጥ የፖሊስ መረጃ የግል ብራዚል ስሪት የሆነው አነስተኛ Phenom 300 የተባለው የቢላዲን ቤተሰቦች ጀት አውሮፕላን Blackbushe በተባለው አየር ማረፊያ ሊያርፍ ሲቃረብ አደጋ እንደደረሰበትና የሞቱት ቁጥርም 3 ብቻ መሆናቸውን ገልጿል ። አደጋውን ተከትሎ የሳውዲ ኢንባሲ በደረሰው አደጋ ለሞቱት የቢላዲን ቤተሰቦች የሀዘን መግለጫ በአንባሳደሩ በኩል ቲዊተር የሀዘን መግለጫ አስተላልፏል ። ከመልዕክቱ ጋር በማያያዝ ኢንባሲው የአደጋውን ምክንያት ለማጣራት ከእንግሊዝ መንግስታ ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አስታውቋል !
አለም አሸባሪ ብሎ በፈረጀው የአልቃኢዳ ጽንፈኛ ቡድን መስራችነትና የሚያውቃቸው የሸህ ኦሳማ ቢላዲን አባት ሸህ ሞሀመድ ቢላዲን እና ቤተሰቦቻቸው ሳውዲ ውስጥ የኮንስትራክሽን እና የተለያዩ ግዙፍ ተቋማት ባለቤት የናጠጡ ባለጸጎች ናቸው ።
ሽህ መሀመድ ቢላዲን 1967 በአውሮፕላን አደጋ መሞታቸው ሲጠቀስ ልጃቸው ሳልም ቢላዲንም በተመሳሳይ ሁኔታ በሀገረ አሜሪካ ሳን አንቶኒዮ San Antonio, Texas, በ1988 ዓም የኤሌቲሪክ ምሰሶ ላይ ተጋጭቶ መሞቱ ይታወቃል ። ከመካከለኛው ምስራቅ ተነስቶ መላ አለምን ባንቀጠቀጠው የተቀናጀ ጥቃት አለምን የነወጡት ሸህ ኦሳማ ቢን ላዲንም በአሳር በመከራ 2011 ዓም ፖኪስታን ውስጥ በአሜሪካ ልዩ ኮማንዶ እንደተገደሉና ሬሳቸውም ባልታወቀ ቦታ መቀበሩን ፕሬዚደንት ኦባማ በኩራት መናገራቸው ይታወሳል ። ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማና አስተዳደራቸው ይህን ይበሉ እንጅ የአልቃኢዳው ቁንጮ የሸህ ኦሳማ ደጋፊዎች በሸሁ አሟሟት ከማይወዷቸው አሜሪካኖች መረጃ ጋር ይጣረሳል ። እነሱ አንደሚሉት የኢሳና አሟሟት ተገደሉ ከመባሉ አስቀድሞ በነበረባቸው የውስጥ ደዌ ከአመታት በፊት መሞታቸውን ሲያስረዱ ሳቸው ያረፈበት ሲናገሩ አይሰማም !
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሟች የቢላዲን ቤተሰቦች ጣሊያን ለቤተሰብ ሰርግ እንደነበሩና ሰረጋቸውን ጨርሰው ለመዝናናት ወደ በሪታንያ ማቅናታቸውን በቅርብ ከሚያውቌቸው ኢትዮጵያውያን ለመረዳት ችያለሁ ! ይህ ያገንሁት መረጃ መላ ቤተሰቡ በስነ ምግባር የታነጹ እንደሆኑና ለሰራተኞቻቸው ደግና መለካም ሰብእና እንዳላቸው ጨምረው ተናግረዋል !
ነገም እኛ ሟቾች ነን ፣ ሰማያዊውን ፍርድ እኛ የመስጠት አቅሙ የለንም ፣ እኛ እንደ ፍጡር የምንለው የሞቱትን ነፍ ይማር ነው ፣ ነፍስ ይማር !
ነቢዩ ሲራክ
ሀምሌ 26 ቀን 2007 ዓም
