በዚህ ጉብኝት ኦባማ የሆነ ተዓምር ሊያመጡ ይችላሉ ብሎ የጠበቀ ከነበረ ቁርጡን የሰማ ይመስለኛል፡፡ Girma Seifu Maru
ለማነኛውም ጋዜጣዊ መግለጫ የሚመስለው ነገር አብቅቶዋል፡፡ ፕሬዝዳንት ኦባማ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን መንግሰት (እንደ ኢትዮጵያ መንግስት ያለውን) በኃይለ ለመጣል የሚደረግ ሙከራን አይደግፉም፡፡ በሀይል ብንጥለው ግን ምን ያደርጉን ይሆን ብዬ በማሰብ ላይ ነኝ!!!! እግዚር ያክብራቸው ስለ ግብረ ሰዶም ለወንድም እና እህቶች ኬኒያ የመከሩትን እዚህ ቢያንስ በይፋ ምንም አላሉም፡፡ ትኩረት ከሚሰጧቸው አራት ነገሮች አንዱ ጉዳይ የመልካም አስተዳደርና ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ቢሆኑም ይህን ለማሳካት ዋናው መራቅ ሳይሆን መሳተፍ ነው ብለዋል፡፡ ተሳትፎዋቸው ደግሞ በዋነኝነት በሚስማሙባቸው ጉዳዮች ላይ ይመስረታል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖር ግንኙነት ከቻይና ጋር ካለው ምንም አይለይም፡፡ ከቻይና ጋር እንደምንሰረው ከኢትዮጵያም ጋር ጥቅማችንን መሰረት አድርገን እንሰራለን፡፡ የእናንተን ሰብዓዊ መብት ተኛ በሉት እንደማለት ነው፡፡ አጭር ነው መልዕክቱ ኢትዮጵያዊያን በእርግጥም ጥሩ ተዋጊዎች ናቸው (እግር መንገድም ሌሎች ኡጋንዳ፣ ኬኒያ) በዚህ ጉዳይ የአሜሪካን እግረኛ ጦር አያሰፈልግመ፡፡ የአሜሪካ ጉዳይ ዶላሩን መግፋት ላይ ነው፡፡ እኛ ገንዘብ የማይገዛውን ደምና ነፍስ እነርሱ ደግሞ ገንዘብ፡፡ ተመሳሳይ ነው የቢቢሲ ዘጋቢ ጠዋት ያስደመጠችን፡፡ ለማነኛውም በዚህ ጉብኝት ፕሬዝዳን ኦባማ የሆነ ተዓምር ሊያመጡ ይችላሉ ብሎ የጠበቀ ከነበረ ቁርጡን የሰማ ይመስለኛል፡፡ ኦባማ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ናቸው፣ የአሜሪካን ጥቅም እስከ አልተነካ ድረስ የሌሎች ጉዳይ ብዙ አይገዳቸውም፡፡ አቁ ይህ ነው፡፡
በዛሬው ጋዜጣው መግለጫ ወሳኝ እና አንደኛ የነበረው ጥያቄ ግን ግንቦት ሰባት እርሶ ቤት ጓዳ ምን ይሰራል? የሚለው ነበር፡፡ እኛ ቤት አሸባሪ ነው የሚል መረጃ የለንም አጭር መልሳቸው ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ በመረጃ ትንተና ላይ ከኢትዮጵያ መንግሰት ጋር ልዩነት አለን ብለው ተናግረዋል፡፡ አሁንም አንድ ሀቅ አለ መቼም ቢሆን የአሜሪካ ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑ ነው ….. ይህን መዘርዘር አይጠበቅብኝም፡፡ በጣም ያዘንኩት ግን ለጋዜጠኞች የሚጠይቅላቸው ቢኖርም በእስር ላይ ለሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች ጥያቄ እንኳን የሚያቀርብ ወዳጅ ማጣታችን ነው፡፡ ፖለቲከኞች ስንታሰር ዳፋው ለቤተሰብ ብቻ የሚሆን መሆኑን አውቀን ከወዲሁ ከዘመድ ወዳጅ ጋር ያለንን ግንኙነት ማጥበቅ ነው፡፡ ለማነኛውም ፖለቲከኞቹ እስር ቤት የሚገኙት ለውጥ የምናመጣው እኛው እራሳችን ለነፃነታችን ስንቆም ነው በማለታቸው ስለሆነ፣ ከኦባማ ምንም የሚጠብቁ አይመስለኝም፡፡ የተቃዋሚ መሪዎች ነን ብለው መድረክ ይሰጠን የሚሉት እነ አቶ ተሻለ ሰርቦ፣ እነ አቲ አበባው መሃሪ፣ ወዘተ አሁን ኦባማን ቢያገኙት ምን ይጠይቁ ይሆን? በእኔ እምነት ማንም ተቃዋሚ ኦባማን የሚጠይቀው ጥያቄ ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡ ኦባማ መልሱ ህዝቡ እንደህ ሲታፈን ለምን ዝም ይላል? ብሎ ድጋሚ ቢጠይቃቸው ምን ይመልሳሉ፡፡ አሁን አጉል ቦታ ጀመርኩ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመጥነው መሪ ነው ያለው የሚል ሀሳብ ከብዙዎች እየሰማሁ ነው፡፡ እኔም እጋራዋለሁ፡፡ ካልመጠነው ገፍትሮ መጣል ይጠበቅበታል፡፡ መገፍተር ከፈራ ደግሞ የፍርሃት ውጤት የዚህ ዓይነት ገዢ ነው፡፡ ተጎንብሶ መጫን!!!
ለማነኛውም ኦባማ እንኳን በሰላም ሀገረችን ኢትዮጵያ መጡ (ለጉርፍም መጥተው ስለነበር) በሰላም ወደ ሀገሮ ይመልሶት ዘንድ ምኞቴ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ለውጥ የሚመጣው ሶማሊያ ውስጥ በምናደርገው የተሳካ አልሻባብን የማቆም ዘመቻ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሰብዓዊ ልማት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ነፃነት በሌለበት ሀገር ጥሩ ወታደር ማፍራት ቢቻለም ጥሩ የልማት ሰራዊት ማፍራት አይቻልም፡፡ ወታደሩም ቢሆን ነፃነት ሲኖር ነፃነት ያምረዋል …..